በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
16/07/2007
ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በትርጓሜ አስታካ አንድ ተረት ጽፋ ዓለሙን እያመሰችው ትገኛለች፡፡ ይህን ትርጓሜ ይዘው ያልሆኑትን ሆነናል በማለት ደማችን የተቀዳው ከመላእክት ወገን ከሆኑት በድሮ ጊዜ ኃያላን ከተባሉት ኔፊሊም ወገን ነው የሚሉ ወገኖች ተነሥተዋል ፡፡
እነርሱም በአሁኑ ጊዜ ብዙ የሚባልላቸው ራሳቸውን ብሩሃነ አእምሮ የሚሉት ኢሉሚናቴዎች ናቸው፡፡ የሚደንቀው ግን ይህ ልብ ወለድ እውነት መስሎአቸው የታወኩ ከእኛም ወገን አልጠፉም፡፡ የጸናው መሰረቱን ሳይለቅ ንፋስ እንደሚያላጋው ሸንበቆ በአፍጢሙ እየተደፋ አፈር ልሶ ሲነሣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የእንግልል ከመሬቱ እየተጣጋ መልሶ እየተነሣ ሲቆም እያየን ነው፡፡ ያልጸናው ግን ነፋሱ እንዳነፈሰው ሲነፍስና ከዚያም እልፍ ሲል የነፋሱ አገልጋይ በመሆን በሌሎች ዓይን ላይ አዋራውን እየሞጀረና እያሳወረ ይገኛል፡፡ ባናስተውለው ነው እንጂ ይህ እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ የሚመጣው ሃሳዊው መሲህ ሰዎችን ሆን ብሎ ለማጥመድ የዘየደው ዘዴ መሆንኑ ማንም በቀላሉ የሚረዳው ነው፡፡
እንዴት በሉኝ? መጽሐፍ ቅዱስ አንድም ቦታ ላይ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ የሚነሣው ተቃዋሚው እኔ ሰይጣን ነኝ እኔን አምልኩኝ እያለ እንደሚመጣ ተጽፎልን አናገኝም፡፡ እርሱም ሆነ ነቢያቱ የሚነሡት በክርስቶስ ስም ነው፡፡ ሲነሡም ራሳቸውን የጽድቅ አገልጋዮች በማድረግ እንጂ የሰይጣን አገልጋዮች ነን በማለት አይደለም፡፡
ነቢያቶቹ ክርስቶስ በዚህ አለ፤ በበረሃ ነው፤ በዚያ ነው፤ እያሉ ዓለሙን ሲያስቱት እርሱ ደግሞ እኔ ክርስቶስ ነኝ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ በክርስቶስ ስም ይመጣል።(ማቴ.24፡23-28) ሰይጣን ለጊዜውም ቢሆን መንግሥቱን እስኪያጸና ድረስ ማንነቱን ፈጽሞ አይገልጥም፡፡ ነቢያቱም ራሳቸውን የክርስቶስ አገልጋዮች እንጂ የሰይጣን አገልጋዮች ነን ብለው በፍጹም አይመጡም፡፡ እነዚህ በአመጻ ደስ ይላቸው የነበሩ እግዚአብሔር ለስህተት አሠራር አሳልፎ የሰጣቸው ወገኖች ናቸው፡፡ እነዚህ በክርስቶስ ስም ልዩ ልዩ አስተምህሮዎችን ይዘው የተነሡና የሚነሱ ናቸው፡፡
ተመልከቱ ሰይጣን ዓለሙን እንዴት እያሳተ እንዳለ፡፡ በአንድ በኩል የእርሱ አገልጋዮችን በግልጥ ሰይጣንን እናመልካለን ብለው እንዲነሡ አደረገ። በሌላ በኩል ደግሞ ራሳቸውን የጽድቅ አገልጋዮች በማስመሰል ልዩ ልዩ የኑፋቄ ትምህርቶችን የሚዘሩ ወገኖችን አስነሣ። እነዚህንም ወገኖች በግልጥ ሰይጣንን የሚያመልኩትን የሚቃወሙ መስለው እንዲገኙ አደረጋቸው። በተዘዋዋሪ ግን ሁለቱም የሚሰብኩት እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ ስለሚነሣው የጥፋት ርኩሰት ነው፡፡ በዚህ መሃል ዓለሙ ሰይጣንን ይቃወማሉ ወደሚሉት ነገር ግን በተዘዋዋሪ እርሱን ወደሚሰብኩት ይወግናል፡፡ ከእነርሱም ሰይጣን እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ ይነሣል ዓለሙ ሁሉ እርሱን ተከትሎ ይስታል።
ተመልከቱ ወገኖቼ ሰይጣን ዓለሙን በእጁ ለማድረግ ምን ያህል እየተጠበበ እንዳለ፡፡ ለዚህ አሠራሩ እንዲመቸው ነው እንግዲህ በአሁኑ ጊዜ እኛ አብረቅራቂዎቹ ነን ዘራችን ከመላእክት የሚመዘዝ ነው የሚሉትን ያስነሣው፡፡ ለዚህም እንደግባት የተጠቀመበት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን የተዛባ ትርጓሜን ነው።
በእውኑ ይህ የካቶሊክ የፈጠራ ተረት ምንድን ነው ? እንዲህ ይሉናል፡- በኖህ ዘመን በሰማይ መኖሪያቸውን ያደረጉ መላእክት ለምን እንደ እግዚአብሔር የሰማይና የምድር ገዢዎች አንሆንም በማለት አሰቡ፥ መከሩ ፥ ዶለቱ እንዲህም አሉ፡ - ሰማይ ግዛታችን ናት ሰው ደግሞ ምድርን ይገዛት ዘንድ ተሰጥቶታል፥ ከእነርሱ ጋር በጋብቻ ብንተሳሰር የሰማይና የምድር ገዢዎች አንሆንምን? አሉ፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉ መላእክት ወደ ሰዎች ልጆች መጥተው ለየራሳቸው ሚስቶችን ወሰዱና ኔፊሊሞችን በድሮ ጊዜ ኃያላን የተባሉትን ወለዱ ይሉናል፡፡ ለዚህ ተረታቸው መሠረት የሚያደርጉት ዘፍ.6 ፡1-4 ያለውን ኃይለ ቃል ነው፡፡
ቃሉ “እንዲህ ሆነ ሰዎች በምድር ላይ መብዛት በጀመሩ ጊዜ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው የእግዚአብሔርም ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ”(ዘፍ.6፡1-2)ይላል። እንደ እነርሱ ትርጓሜ የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉት የሰማይና የምድር ገዢዎች መባልን የቋመጡ የወደቁት መላእክት ናቸው፡፡ እነዚህ ከመናፍስት የተዳቀሉ ሰዎችን ወለዱ። እነርሱም በድሮ ጊዜ ኃያላን የተባሉት ኔፍሊሞች ናቸው ይሉናል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ለአሁኖቹ እኛ ኢሉሚናቴዎች ነን ለሚሉት መመጻደቂያቸው የሆነው ተረት ምንጩ፡፡
እውነታው ግን ከዚህ በፍጹም የተለየ ነው፡፡ ቅዱሳን አባቶች እንዳስተማሩንና መጽሐፍም እንደሚነግረን ተፈጥሮም እንደሚያስተምረን ይህ የሙሴ ቃል የሚናገረው ስለ መላእክትና ስለ ሰዎች ግቢ ሳይሆን በሴት ወገኖችና በቃየን ወገኖች መካከል ስለተደረገ ጋብቻ ነው፡፡ይህ ጋብቻ በሰውና በሰው መካከል የተፈጸመ ጋብቻ እንጂ በመላእክትና በሰዎች መካከል የተደረገ ጋብቻ አይደለም። ይህ ተፈጥሮ እንኳ የሚፈቅደው አይደለም ፡፡
የቃሉ መሠረት ይህ ነው ፡- ቃየን አቤልን በመግደሉ ምክንያት ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፡፡ (ዘፍ.4፡16) ይህች ቃየን ለቅቆአት የወጣባት ስፍራ በእኛ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ደብር ቅዱስ ትባላለች። መጽሐፍም “ኤደን” ይላታል፡፡ ቃየን ከዚህች ስፍራ ተለየ፤ ”ምድርን ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይሏን አትሰጥህም በምድርም ላይ ኮብላይና ተቅበዠባዠ ትሆናለህ” (ዘፍ.4:12) ብሎ በእርሱ ምክንያት የሚያርሳት ምድር ዳግምኛ ተረገመች፡፡ ከአቤል ሞት በኋላ ግን አዳምና ሔዋንም በአቤል ምትክ ሴትን ወለዱ፤ በእርሱ ዘመን መጽሐፍ እንደሚነግረን በእግዚአብሔር ስም መጠራት ተጀመረ (የእግዚአብሔር ልጆች ትብሎ መጠራት ተጀመረ)፡፡(ዘፍ.4፡26)
በዚህ መልክ የሴትና የቃየን ልጆች ተለያይተው እየኖሩ ሳለ አንድ ወቅት የሴት ልጆች ማለትም የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉት የቃየን ልጆች ማለትም የሰው ልጆች የተባሉትን ሴት ልጆች ተመለከቱ፤ ውበታቸው ማረካቸው፤ ስለዚህ ለራሳቸው ሚስቶች ይሆኑአቸው ዘንድ ወሰዱ፡፡ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ትርጓሜ በእነዚህ ሁለት ወገኖች መካከል የተደረገው ጋብቻ ተገቢ ያልሆነ ጋብቻ ነበር፡፡ ምክንያቱም የሴት ልጆች ሚሰቶች እያሉዋቸው ሌሎች ሚስቶችን ከቃየን ወገን በመውሰዳቸው ምክንያት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ነው እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የተቆጣው በማለት ቃሉን ተርጉሞልናል፡፡ በእርግጥ በጋብቻ ላይ ጋብቻ ኃጢአት ነው፡፡ በዚያ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ሆነው እግዚአብሔርን እያወቁ በድፍረት የፈጸሙት ኃጢአት ነውና የድፍረት ኃጢአት ነበረ፡፡
ቃሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ ነው እንጂ የሚለው ከእነርሱ ጋር በቃየን ምድር ተቀመጡ አይልም፡፡ ስለዚህ የሴት ልጆች የቃየን ሴት ልጆችን የወሰዱት ወደ አልተረገመችው ምድራቸው ነበር፡፡ ምድሪቱ ለም ነበረች፡፡ ከእነርሱም ልጆችን ወለዱ እነርሱም ለም ከሆነችም የምድር ፍሬ እየተመገቡ እጅግ ግዙፋን ሆኑ፡፡ እነዚህን መጽሐፍ ቅዱስ ኔፍሊም ይላቸዋል፡፡ እጅግ ግዙፋን ነበሩና፡፡ ይህን እንረዳ ዘንድ እስራኤላዊያን ኢያሪኮን ሰልለው በተመለሱ ጊዜ የተናገሩትን ቃል እንመልከት እንዲህ ይላል፡-- “በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን ኔፊሊም፥ የዔናቅን ልጆች፥ አየን እኛም በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን፥ ደግሞም እኛ በዓይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን አሉ”(ዘኁል.13፡33) እነዚህ ወገኖች በኖህ ዘመን የተነሡ ኔፊሊምና ኃያላን ለተባሉት አምሳያዎች ናቸው፡፡ እስራኤላዊያንም እንዲህ ማለታቸው ከአባቶቻቸው ከተነገራቸው ቃል ተነስተው ነው እንጂ በእውነት እነዚህ በኖህ ዘመን ለሴት ልጆች የተወለዱላቸው ኔፊሊሞች ሆነው አልነበሩም፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ እንደሚል እግዚአብሔር እነዚያን ወገኖች ኖህንና ቤተሰቡን አድኖ ፈጽሞ እንዳጠፋቸው ይናገራልና፡፡ እንዲህ እንዲል “በምድር ላይ ሥጋ ያለው የሚንቀሳቀሰው ሁሉ ወፉም እንስሳውም አራዊቱም በምድር ላይ የሚርመሰመሰውም ተንቀሳቃሹም ሁሉ ሰውም ሁሉ ጠፋ፡፡ በየብስ የነበረው በአፍንጫው የሕይወት እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ፡፡”(ዘፍ.7፡21-22)
እንዲያ ከሆነ ታዲያ እነዚህ ኔፊሊም የተባሉ እስራኤላዊያን በፍልስጤም ምድር ያገኙአቸው እጅግ ግዙፋን ሰዎች እነማን ናቸው? የሚል አይጠፋም፡፡ እነዚህ ሰዎች በኖህ የእጣ ድልድል ለሴም የሆነውን ለም ምድር በጉልበት የወረሱ የከነዓን ወገኖች ናቸው፡፡ ይህን አስመልከቶ ግን በ66 መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መረጃ ማቅረብ ቢያስቸግርም በመጽሐፈ ኩፋሌ ላይ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ቢሆንም ግን ይህ እውነት መሆኑን መረዳት የሚቻለው እግዚአብሔር ከነዓናዊያኑን አጥፍቶ ምድሪቱን ለእስራኤላዊያን በመስጠቱ ነው፡፡ነገር ግን ይህቺ ምድር ለም በመሆኑዋ ምክንያትም እነዚህም እንደ ኔፊሊሞች ግዙፋን እንደሆኑ መረዳት እንችላለን፡፡ እንዲህ የሚል ቃል አለና “ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጡ፥ ከዚያም ከወይኑ አንድ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፥ ሁለቱም ሰዎች በመሎጊያ ተሸከሙት”(ዘኁል.13፡23) ይላል። ተመልከቱ የወይን ዘለላን በአንድ እጅ ብቻ ማንጠልጠል ሲቻል እነዚህ ግን በመሸከሚያ ሁለት ሰዎች መሸከማቸውን እንመለከታለን። በዚህም የወይኑ ፍሬ ምን ያህል ግዙፉ እንደነበረ መረዳት እንችላለን፡፡ ከዚህ ተነስታችሁ ምድሪቱ ምን ያህል ለም እንደሆነች ማስተዋል ትችላላችሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህች ምድር ፍሬ ይመገቡ የነበሩ የምድሪቱ ሰዎች ምን ያህል ግዙፎች መሆናቸውን መገመት የሚሳነው ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህም ነው ለስለላ የተላኩ ሰዎች ኔፊሊሞችን አየን ማለታቸው እንጂ እስከ እነርሱ ዘመን ድረስ በኖህ ዘመን የተወለዱ ኔፊሊም የተባሉ ወገኖች ኖረው አይደለም፡፡ እነዚያ ወገኖችን በውሃ ሙላት ፈጽመው ጠፍተዋል። ስለዚህ ከመላእክት የተዋለዱ ከሰው ወገን የሉም። አሉም ቢባል እንኳ በጥፋት ውሃ ፈጽመው ተደምስሰዋል። ስለዚህ እነዚህ ራሳቸውን ከመላእክት ወገን ነን የሚሉ ብዙ የሚባልላቸው ወገኖች ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተገኝን ልብ ወለድ ለራሳቸው ተርጉመው የጠፉ ወገኖች እንጂ ከመላእክት ወገን አይደሉም። በእርግጥ እንደ ይሁዳ ራሳቸውን ለዲያብሎስ መጠቀሚያነት ስለሰጡ የዲያብሎስ ልጆች ልንላቸው ብንችልም ከመላእክት ጋር የተዳቀለ ዘር ግን ፈጽሞ የላቸውም።
Let make some fun here. Nice to meet you Mr. 'god' ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ......
ReplyDelete"የሴትና የቃየን ልጆች ተለያይተው እየኖሩ ሳለ አንድ ወቅት የሴት ልጆች ማለትም የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉት የቃየን ልጆች ማለትም የሰው ልጆች የተባሉትን ሴት ልጆች ተመለከቱ፤ ውበታቸው ማረካቸው፤ ስለዚህ ለራሳቸው ሚስቶች ይሆኑአቸው ዘንድ ወሰዱ፡፡" My qQQQQ here gave me Proof from Bible the children of ሴት called " the Sons of God" and the children of ቃየን "daughters of men".....Hope I am clear and sound!!
ReplyDeletethat is my question too.
Deletethank you its clear
ReplyDeleteSo why Bible mention nephilim at all?
ReplyDelete