በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/07/2007
መቼም ጦምን ከጸሎት ጋር አስተባብሮ የያዘና ራሱን በእግዚአብሔር ፊት አቁሞ ስለ መተላለፉ በአምላኩ ፊት የሚያነባ ክርስቲያን የንስሐ እንባው የኃጢአት እድፉን ጠርጎ ስለሚያስወግድለት በሰዎች ላይ የማይፈርድ፥ እንደ ግብዝ ጦመኞች ልታይ ልታይ ማለት የሌለበት፥ ለሰው ልጅ ያለው ፍቅር የበዛለት፥ አንደበቱም ይሁን ልቡ ከጸሎትና ከልመና እንዲሁም ከምልጃ የማያርፍ ፥ ቃሉን ማንበብ የሚወድ፥ በቃሉ መመሰጥ የሆነለት፥ የራሱን እንጂ የሰዎችን ነውር ለማየት የማይፈቅድ፥ ስለራሱ ኃጢአት በአምላኩ ፊት በመንፈስ ሆኖ የሰማይን ፊት እንኳ ለማየት የማልበቃ ኃጢአተኛ ነኝ እያለ ደረቱን የሚደቃ ሰው መሆንን ገንዘቡ እንደሚያደርግ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።
ብቻ ይህን ከሚያጠፋ ከከንቱ ውዳሴ ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባናል። ይህ ከሰዎች ምስጋናን ከመስማትና በልብም ይገባኛል ብሎ ተቀብሎ የደስታ ስሜት ከመሰማት ይጀምራል። ከዚያም ስለኃጢአት ማንባቱ ይቀራል። በራስ ላይ መፍረዱ ይተውና ራስን እንደ ጻድቅ በመመልከት ሌሎችን ወደ መኮነን ይመጣል። ምስጋናን ያልሰጠውን ሰው ወደመጥላትና ከሰው ምስጋናን ለማግኘት ሲል ወደ መቅበዝበዝ ይደረሳል።
ይህ ክፉ ደዌ ነው ወገኖቼ ። ብዙዎች በዚህ ደዌ ተይዘው ሥራ ፈት ሆነው አእምሮአቸውን እንዳጡ ሰዎች ከሰዎች ምስጋናን ለማግኘት ሲሉ ተቅበዝባዥ ሆነዋል። የአምልኮ መልክ ይታይባቸዋል ነገር ግን አእምሮአቸው የተቀማባቸው ሰዎች ናቸው።
ይህን ነው ጌታችን የግብዞች ጦም ያለው። እናም ወገኖቼ ራሳችንን ከከንቱ ውዳሴ እንጠብቅ ከሰዎች ምስጋና ሲቀርብልን ምስጋና ለጌታ እንጂ ለእኔ አይገባኝም ብለን በልባችን አጥብቀን እንቃወመው ። ሰይጣን በጦምና በጸሎት የተጋን ክርስቲያንን የሚያሰናክልበት ዋነኛው መሳርያ ይህ ነው። ስለዚህ በትሕትና ጸንታችሁ በጸጋ ላይ ጸጋን ጨምራችሁ በመንፈሳዊ ሕይወት አዋቂዎች እንድትሆኑ ከከንቱ ውዳሴ ራሳችሁን ጠብቁ ወገኖቼ ።
No comments:
Post a Comment