Monday, March 23, 2015

ቀጣይ መዝ.89 እንደ ቅዱስ ጀሮም

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 

14/07/2007

“የዘመኖቻችን እድሜ ሰባ ዓመት ነው…” አለን…. ግፋ ቢል ሰማንያ ብሎ ጨመረበት  ከሰማንያ ዓመት በላይ ብንኖር ግን ሕይወታችን ሕይወት ተብሎ የሚቆጠር አይሆንም፡፡ እንዲያም ቢሆን በጤና ሰማንያ ብንደርስ እድለኞች ነን፡፡ ከስምንት ዐሥር ዓመታት በኋላ ማን ነው ጤናማ ሆኖ የሚቀጥል?  ግሪካዊያን አንድ አባባል አላቸው፡- “እርጅና በራሱ አንድ የሕመም ዓይነት ነው” ይላሉ። ከሰማንያ ቢበዛ ግን ዳዊት “ድካምና መከራ ነው” እንዳለው ሃዘን ነው፡፡ 
እሰካሁን ድረስ ግን የመዝሙሩን ቀጥተኛ የሆነውን ትርጉም ነው የተመለከትነው፡፡ አሁን ደግሞ የቃሉን ምሥጢር እንመለከተው፡፡ ቢሆንም ሁሉን አንድ በአንድ አንመለከተውም እንዲያ ቢሆን ግን ጊዜ ባልበቃን ነበር፡፡ ስለዚህ ሌሎችን አልፈን ለምን የዘመናችን እድሜ ሰባ ዓመት ነው” አለ የሚለውን መንፈሳዊ ምስጢር ወይም መንፈሳዊ መልእክቱን ማየት እንጀምር፡፡ 
“የዘመናችን እድሜ ሰባ ዓመት ነው” አለ፡፡ ሰባ ቁጥር በሦስት እጥፍ አሥር ዓመታት ላይ አንድ ዐሥር ዓመት ያክላል፡፡ ዐራት እጥፍ ዐሥር ዓመታት ማለት ሰማንያ ዓመት ነው፡፡ ስለዚህ ቃሉ በሰባትና በስምንት ቁጥሮች ላይ ትኩረት መስጠቱን እንመለከታለን። እንዲሁ “አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን፡፡" ብሎ ትውልድ ያለው ብሉዩንና ሐዲስ ኪዳንን መሆኑን አስቀድመን እንዳስተማረንም ልብ በሉ፡፡ ልጁ ጠቢቡ ሰሎሞን  በመክበቡ “እንጀራህን በውኃ ፊት ጣለው ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህ፡፡
ለሰባት ደግሞም ለስምንት እድል ፈንታ ክፈል፡፡”(መክ.11፡2) ይለናል፡፡ ቤተመቅደሱንም ሲሠራ ሰባትና ስምነት ደረጃ አድርጎ ነበር፡፡ ይህም የራሱ መልእክት ያለው ነው፡፡  ጌታችንም በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብጹአን ናቸው፣ የዋኀን ብፁዓን ናቸው፣ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብጹአን ናቸው እያለ ስምንት ጊዜ ብፁዓን እንዳለም ልብ በሉ፡፡ እነዚህም ወደ ሊቀ ካህናቱ ክርስቶስ የሚያወጣጡን ከእኛ የሚጠበቁ ተግባራት ናቸው፡፡ እነዚህ ግን ሙሉ የሚሆኑት ወደ ቤተመቅደሱ በገባውና በወጣው ሊቀካህናት ክርስቶስ ነው። ይህን አስመልከቶ ሕዝቅኤል በራእይ ያየው የቤተ መቅደስ አሠራርና ግለጋሎት በምዕራፍ 40 ላይ በሰፊው ተንትኖታል፡፡ … እናም ይህ ሰባትና ስምንት ተብሎ የተገለጸው መንፈሳዊው ምስጢሩ ምንድን ነው ? ሕዝቅኤል እንዲህ ይላል፡- “ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶ ነበር፡፡”(ሕዝ.44፡1) ይለናል። ይህ በር ስምንት መወጣጫ ደረጃዎች እንዳሉት ሲገልጥ “በምስራቅ በኩል አገባኝ ….. ወደ እርሱ የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት፡፡”(ሕዝ.40፡32-34)ብሎ ጻፈልን፡፡ ወደዚህ የገባው እርሱ ልዑል እግዚአብሔር እንደሆነም  “እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል አንጂ አይከፈትም  ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፡፡” ብሎ  ገለጠልን፡፡ በእርግጥ ወደ እርሱዋ የገባባት መቅደሱ አድርጎ የሠራት ቅድስት ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል እናቱ ናት፡፡ ሌላም ትርጉም ግን አለው፡፡ ወደ መቅደሱ የገባና የወጣ የጽድቅ ፀሐይ የተባለው ከእውነተኛ ብርሃን የተገኘ እውነተኛው ብርሃን እርሱ ከርስቶስም ነው፡፡ መቅደስ የተባሉት ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን ናቸው። ለምን? የቃሉ በር የሚከፍተውና የሚዘጋው እርሱ ብቻ ነውና። "በሩ ተዘግቶ ይኖራል" የሚለው ቃል በእርግጥም ስለድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና የሚናገር ቢሆንም የመጽሐፉ ቁልፍ ያለው የሚከፍተው የሌለውን የሚከፍት የሚዘጋውም የሌለውን የሚዘጋው የተባለው እርሱ ክርስቶስም ነውና ለእርሱም ይተረጎማል፡፡ ብሉይና ሐዲስ ኪዳናት ማንም ሊከፍታቸው የማይችላቸው የተዘጉ በሮች ናቸው፡፡ የሚዘጋውና የሚከፍተው እርሱ ነው።“እርሱ የከፈተውን ማንም ሊዘጋው አይችልም እርሱ የዘጋውን ማንም ሊከፍተው አይችልም፡፡  ለእነዚህ ኪዳናት ቁልፉና  መግቢያ በሩ እርሱ ነው፡፡ እርሱ ካልገለጠልን በቀር የመጻሕፍትን ምስጢራት ማንም ሊረዳቸው አይቻለውም፡፡
ይቀጥላል........

No comments:

Post a Comment