Monday, March 23, 2015

መዝ.89 እንደ ቅዱስ ጀሮም ቀጣይ ክፍል


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

12/07/2007

አሁን ወደ መዝሙሩ ቃል እንመለስ፡- የእኛ የሕይወት ዘመን ለምሳሌ የሁላችን አባት የሆነው አዳም 930 ኖሮ ሞተ፡፡ ማቱሳላ ደግሞ 969 ዓመታት በሕይወት ቆይቶ ሞተ፡፡ እኚህ አባቶች አንድ ሺህ ዓመት ኖሩ ብንል እንኳ ለእኛ ከተሰጠን ዘለዓለማዊነት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ኢምንት ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ፍጻሜ ያለው ነገር እንዴት ታላቅ ሊባል ይችላል? ኃጢአትን ሳንፈጽም እንድንኖር የተሰጠን 1000 ዓመት በአንተ ዘንድ እንደ አንዲት ቀን ነበረች፡፡  እንደ አንዲት ቀን ብቻ አለን? እንደ ሌሊት ትጋት ናት ብሎ ይበልጥ ኢምነት አደረጋት እንጂ፡፡ ስለሆነም ጌታችን ሆይ በአንተ ዘንድ ዘመኖቻችን የተናቁ ናቸው!! ስለዚህ ጌታ ሆይ ወደ አንተ እናጋጥጣለን፤ ሰውን ወደ ኅሳር አትመልሰው እንልሃለን፤ ጌታ ሆይ እኛን ለማዳን ወደ ምድር መምጣትህን፣  ደምህንም ስለእኛ መዳን ማፍሰስህን አስብ፡፡ ጌታ ሆይ አንተ ራስህ  “እኔ ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ”(ዮሐ.12፡32) ብለኸናልና  ጌታ ሆይ ! ራስህን ከፍ ከፍ አድርገህ እኛን ወዳንተ ሳብኸን እንጂ ወደ ላይ እንወጣጣ ዘንድ እኛ ወደ አንተ አልቀረብንምና አቤቱ ይህን አስብ፡፡
“ዘመኖች የተናቁ ይሆናሉ በማለዳ እንደ ሣር ያልፋል ማለዶ ያብባል ያልፋልም በሰርክም ጠውለጎ ይደርቃል” አለ ዳዊት፡፡ በወንጌል ደግሞ ጌታችን ዛሬ አምሮና ለምልሞ የሚታየው የሜዳ ሣር ነገ ደርቆ ወደ እቶን እሳት እንደሚጣል አስተምሮናል፡፡ የሜዳ ሣር በአንድ ቀን እድሜ ወስጥ ለምልሞና አብቦ ይታያል፤ በቀትር ጊዜ ግን አበባው ረግፎና ቅጠሉ ጠውልጎ አመሻሹ ላይ ይሞታል፡፡ የእኛም ዘመን እንዲሁ ነው፡፡ ሕይወታችን ዛሬ ታይታ ነገ እንደምትጠፋ እንደ ሜዳ አበባ ናት እንደ ሕልም ጨርሶኑ ላትታወስ ትጠፋለች፡፡ እንደዚህች አበባ ገና በልጀነትና በወጣትነት ዘመናችን ሞት የማይነካን አፍላዎች እንደሆንን እናስባለን፡፡ በእድሜአችን አመሻሽ ላይ ያ ሁሉ ውበት ረግፎና ጠውልጎ ወደመቃብር እንወርዳለን፡፡ 
አንድ የምናውቀው ሰው ይኖረን ይሆናል ፡፡ እድሜው ዐሥር ዓመት ሳይሞላው በፊት አፍላ በሆነው እድሜው እዚም እዚያም እያለ እንደ ጥጃ ሲፈነጭ ስናየው ዉበቱን ስናስተውለው እንደ እርሱ የተዋበና ብርቱ ከምድርም ፊት ፈለገን  ማግኘት ተስኖን ይሆናል፡፡ አሁን በእርጅናው እድሜው ስናየው ግን እንደ ሞተ ሰው ሆኖ ስናገኘው ይደንቀናል፡፡ ይህ ሰው ምንም እንኳ በሕይወት  ቢሆንም በእርጅናው ምክንያት ወጣትነቱ ከእርሱ ላይመለስ እጅግ ርቋል፡፡ በማለዳ ታይቶ አመሻሽ ላይ እንደሚጠወልገውና እንደሚጠፋው የሜዳ አበባ ሕይወቱ  እንዲሁ ሆኖአል፡፡  ይህ ሲታሰብ ጌታ ሆይ  በእውነትም በአንተ ቁጣ አልቀናል በመዓትህም ደንግጠናል፡፡ 
“በደላችንን በፊትህ አስቀመጥህ” ከአንተ አንዳች የሚሰወር ነገር የለም፡፡ ኃጢአታችንን ሌሊት ሊሰውረው ጨለማም ሊጋርደው ፈጽሞ አይቻለውም፡፡ በፊትህ ብርሃን ሁሉ የተራቆተ ነው፡፡ ምንም እንሥራ ምንም እናስብ ሁሉም በዓይንህ ፊት የተገለጠ ነው፡፡ ከአንተ አንዳች ሊሠወር የሚችል ድርጊትም ሆነ ሃሳብ የለም፡፡  
“ዘመናችን ሁሉ አልፎአልና” አለን መዝሙረኛው፡፡ የሕይወት ዘመናችን ወደ ፍጻሜዋ ለመድረስ እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ትቻኮላለች፤ ሳናጣጥማትም በሞት እንወሰዳለን፡፡ አስከትሎም ዳዊት ዘመናችንን  ከሸረሪቷ ድር ጋር በማነጻጸር “ዘመናችን እንደ ሸረሪት ድር ይሆናል” አለን፡፡ እስቲ የዚህችን ታናሽ ፍጥረት ሕይወት እናስተውለው፡- ይህቺ ታናሽ ፍጥረት ድሯር ለማድራት ቀኑን ሙሉ እዚያም እዚህም ስትል፥ ላይ ስትወጣ ታች ስትወርድ ቀኑን ሙሉ ትውላለች፤ ድሮቹዋን ትታታለች ትታታለች … ይህ ቀኑን ሙሉ ያለመታከት የምትፈጽመው ድካሟ ነው፡፡ ድካሟ ሁሉ ግን በአንድ ጊዜ ተበጣጥሶ እንደምናምንቴ ይሆናል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ይህችን ከፉ ጥረት ይላታል፡፡  የሰውም የሕይወት ዘመኑ እንዲሁ ነው፥  ቀኑን ሙሉ ሕይወቱን ለማቅናት ሲል ያለ እረፍት፥ ያለ እርካታ ሲወጣ ሲወርድ ይውላል፡፡ ሀብትን ለማግኘት ይማስናል፥ ሲያገኝ ያከማቻል፥ ልጆችን ይወልዳል ይወጣል ይወርዳል ይወጣል ይወርዳል….. ፤ በስልጣን ላይ ስልጣንን በሹመት ላይ ሹመትን ይደራርባል ይነባብራል፥ ፍጻሜ ግን እንደ ሸረሪቷ ድር ይሆንበታል በከንቱ ባክኖ ባክኖ ያለአንዳች ፍሬ ባዶ እጁን ወደ መቃብር ይወርዳል፡፡ ለዚህም ይሆናል ጌታችን አስቀድማችሁ ጽድቁንና መንግሥቱን እሹ ሌላው ይጨመርላችኋል ያለው። ምክንያቱም እነዚህ ሁሉ ድካሞች በእርሱ ፊት እንደ ሸረሪት ድር ናቸውና፡፡ ይቀጥላል መዝሙረኛው 
የዘመኖቻችን እድሜ ሰባ ዓመት ነው ይለናል… ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment