Tuesday, May 22, 2012

“ዕንቁ ክርስቶስ በቅዱስ ኤፍሬም”



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/09/2004

ከዕለታት በአንዱ ቀን ከወንድሞቼ በስጦታ ዕንቁ ተቀበልኩኝ፤ በዚህ ዕንቁ ውስጥ ታላቅ የመንግሥቱን ምሥጢርንና የገዢው የክርስቶስን ምሳሌ ተመለከትኩ፡፡ ዕንቁ ለእኔ ጥሩ የውኃ ምንጭ ሆነልኝ ፤ከዚህም ምንጭ የእግዚአብሔር ልጅን ምሥጢር ጠጥቼ ረካሁ፡፡
ወንድሞቼ ሆይ የሰጣችሁኝን ዕንቁ እመረምረው ዘንድ በማሃል እጄ ያዝኩት ፡፡ ወደ ዐይኖቼም አቅርቤ ዙሪያውን ተመለከትኩት እናም ይህ ዕንቁ በሁሉም አቅጣጫ ዐይኖች እንዳሉት አስተዋልኩ፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስን ብርሃን ነው ብንልም ፈጽሞ ልንመረምረው እንደማንችል ተረዳሁ፡፡
በዕንቁ ብሩህነት በባሕርይው ምንም ጨለማ የሌለበትን የእግዚአብሔር አብ ብቸኛ ልጁን ተመለከትኩ፡፡ በእርሱም ውስጥ ግሩም የሆነውም ንጽሕናውን አስተዋለኩኝ፤ ከእኛም የነሣውንም ሥጋ ቅድስናውንና ንጽሕናውን ተረዳሁ፡፡ በዚህ ዕንቁ ውስጥ ያየውትን ያለመከፈል አንድ የሆነውን የሥጋንና የመለኮትን ተዋሕዶ ተመለከትኩ፡፡
በዕንቁው ውስጥ እንዲሁ የእርሱን ንጹሕ የሆነውን ፅንሰት አስተዋልኩ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በምትሰኘው ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን የተፈጸመውን የእግዚአብሔር ልጅ ፅንሰትን ተረዳሁ፡፡ እርሱዋ እርሱን የተሸከመችው ደመናው ናት፡፡ የእርሱዋም ምሳሌ ሰማይ ነው፡፡ ከእርሱዋም የጽድቅ ፀሐይ በመውጣት ለዓለም አበራ፡፡


ሠርግ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እይታ



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ 
14/09/2004
ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች በላከው መልእክቱ ም.፬፥፲፪ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል  ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በተረጎመበት ፲፪ኛው ድርሳኑ በዘመኑ የሚፈጸመውን የሰርግ ሥርዐት መሠረት በማድረግ ሰርግን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ትምህርትን ሰጥቶአል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሰርግ ምክንያት የሚወጡትን ወጪዎችንና ሁካታዎችን አጥብቆ የሚቃወም አባት ነው ፡፡ በዚህም ጽሑፍ ይህን ወደማስተዋል ልንመጣም እንችላልን ፡፡    
"...ትዳር ምንድን ነው? ትዕይንት(ትያትር) ነውን? አይደለም፡፡  ምንም እንኳ እናንተ ለትዳርና ለምሳሌው አክብሮት ባይኖራችሁ እንኳ ትዳር ግሩም ምሥጢርና የታላቅ መንፈሳዊ ምሥጢር ምሳሌ ነው ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስተምር “ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው” ይልና ጨምሮ “እኔ ግን ስለ ክርስቶስና ስለቤተክርስቲያን እላለሁ” ይላል፡፡(ኤፌ.፭፥፴፪) ጋብቻ የቤተክርስቲያንና የክርስቶስ ምሳሌ ነው ፤ እንዲህ በከበረ ምሥጢር ላይ ዳንኪረኞችን በመጋበዝ ዝሙትን ታስተዋውቃላችሁን ? ነገር ግን ከእናንተ መካከል አንዱ እኔን፡- እንዲህ ስትል ደናግላን ወይም ያገቡት አይጨፍሩ እያልክ ነውን ? እንግዲያስ እነርሱ በዚህ ሠርግ ላይ ካልጨፈሩ ማን ሊጨፍር ነው ? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል ፡፡ የእኔ መልስ ማንም አይጨፍር የሚል ነው ፡፡