Tuesday, May 22, 2012

ሠርግ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እይታ



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ 
14/09/2004
ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች በላከው መልእክቱ ም.፬፥፲፪ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል  ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በተረጎመበት ፲፪ኛው ድርሳኑ በዘመኑ የሚፈጸመውን የሰርግ ሥርዐት መሠረት በማድረግ ሰርግን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ትምህርትን ሰጥቶአል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሰርግ ምክንያት የሚወጡትን ወጪዎችንና ሁካታዎችን አጥብቆ የሚቃወም አባት ነው ፡፡ በዚህም ጽሑፍ ይህን ወደማስተዋል ልንመጣም እንችላልን ፡፡    
"...ትዳር ምንድን ነው? ትዕይንት(ትያትር) ነውን? አይደለም፡፡  ምንም እንኳ እናንተ ለትዳርና ለምሳሌው አክብሮት ባይኖራችሁ እንኳ ትዳር ግሩም ምሥጢርና የታላቅ መንፈሳዊ ምሥጢር ምሳሌ ነው ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስተምር “ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው” ይልና ጨምሮ “እኔ ግን ስለ ክርስቶስና ስለቤተክርስቲያን እላለሁ” ይላል፡፡(ኤፌ.፭፥፴፪) ጋብቻ የቤተክርስቲያንና የክርስቶስ ምሳሌ ነው ፤ እንዲህ በከበረ ምሥጢር ላይ ዳንኪረኞችን በመጋበዝ ዝሙትን ታስተዋውቃላችሁን ? ነገር ግን ከእናንተ መካከል አንዱ እኔን፡- እንዲህ ስትል ደናግላን ወይም ያገቡት አይጨፍሩ እያልክ ነውን ? እንግዲያስ እነርሱ በዚህ ሠርግ ላይ ካልጨፈሩ ማን ሊጨፍር ነው ? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል ፡፡ የእኔ መልስ ማንም አይጨፍር የሚል ነው ፡፡

በአሕዛብ ዘንድ ይህን በመሰሉ ሥርዐቶቻቸው ዳንኪረኞች ዳንኪራቸውን ያቀርባሉ፡፡ በእኛ ግን ማንኛውም ምሥጢራት ሲከወኑ በጸጥታ፣ በትሕትናና በጥሩ ሥነምግባር እንዲሁም በመልካም ሥርዐት ነው፡፡ ይህ የጋብቻ ሥርዐት አመንዝሮች ከተጠሩበት፣ እግዚአብሔርን የማይፈሩ ከተጋበዙበት እንዴት ብለን ነው መንፈሳዊ ጋብቻ ብለን ልንጠራው የምንችለው ? እንዲህ ከሆነ እንዴት ተብሎ ነው ሁለቱ አካላት አንድ ሆነዋል ልንል የምንችለው ?
 ክርስቶስ በተገኘበት ጋብቻ ግን ዳንኪራ የለም የእምቢልታም ድምፅ አይሰማበትም ፡፡ ነገር ግን ግሩም የሆነ ጸጥታ የሰፈነበት፣ በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዐት የሚከወን ነው፡፡ በዚህ ሥርዐት አንድ አካል ወደ መሆን ሲመጡ አንድነታቸው ሕይወት አልባ ፍጥረታት እንደሚኖራቸው አንድነት ወይም በዚህ ምድር የሚታየውን ዐይነት አንድነት አይደለም፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ሆነው አንድ ይሆናሉ ፡፡ ይህ ታላቅ የሆነ ምሥጢር በሚከወንበት ሥፍራ እንደ አራዊት ታላቅ ሁካታና ረብሻ እንዲሁም ነፍስን የሚያሳድፉ ታላላቅ የሆነኑ በደለሎቸች ይፈጸማሉን?
ሁለቱ አንድ አካል በመሆናቸው በዚህ ያለውን የፍቅርን ምሥጢር አስተውል፡፡ እነዚህ ሁለት አካላት ሁለትነታቸውን ይዘው የሚቀጥሉ ከሆነ ሊበዙ አይችሉም ፡፡ ነገር ግን አንድ ወደ መሆን ሲመጡ ይበዛሉ፡፡ ከዚህ ምን እንማራለን ? የትዳርን ታላቅነት አይደለምን? ሥላሴ በመጀመሪያ ባደረገው ሸንጎ ሁለት የሆኑትን  አካላት አንድ አድርጎ ፈጠራቸው ስማቸውንም  ሰው አለው ፡፡ በኋላ ደግሞ እነዚህን አንድ አድርጎ የፈጠራቸውን አካላት ሁለት በማድረግ ገለጠው፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ አካላት ሁለት ቢሆኑ የእግዚአብሔር ፈቃድ  ግን አንድ ይሆኑ ዘንድ ነበርና በትዳር መልሶ አንድ አደረጋቸው፡፡
 የእርሱ ፈቃድ ይገለጥ ዘንድም አንዱ አምሳሉን ለመውለድ ብቻውን ብቁ እንዲሆን አላደረገውም፡፡ ስለዚህ ከተቃራኒው አካል ጋር አንድነትን ላልመሠረተ ሰው አንድ አካል የሚባለው ስያሜው አይሰጠውም ነገር ግን የሌላኛው ግማሽ አካል ይባላል፡፡ ለዚህም ምስክሩ ልጅ መውለድ አለመቻሉ ነው ፡፡ ይህ እግዚአብሔር አስቀድሞ የሠራው ሥርዐት ነው ፡፡ የጋብቻን ምሥጢር አስተዋላችሁን ? አስቀድሞ አንድ አድርጎ ፈጠራቸው በኋላም ነጣጠላቸው ፤ እንደገና ሁለት የነበሩትን እነዚህን ወገኖች ወደ አንድነት አመጣቸው ፡፡ እንዲህም እድርጎ ስለሠራው ሰው በትዳር አንድ ከሆኑ ወገኖች እንዲፈጠር ሆነ፡፡
 ባልና ሚስት ሁለት አካላት አይደሉም ነገር ግን አንድ አካል ናቸው ፡፡ ይህ በብዙ መረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል ፡፡ በያዕቆብ ወይም በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናት በድንግል ማርያም ወይም እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር “ሰውን በአርዓያችንና በአምሳላችን እንፍጠር …ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍ.1፡27) በሚለው ቃሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ባል ራስ ከሆነ ሚስት ደግሞ ቀሪው አካሉ ትሆናለች፡፡ ስለዚህ አንዱ የደቀመዝሙርነት ማዕረግ ሲኖረው አንዱ የመምህርነት ቦታ ይይዛል አንዱ መሪ ሲሆን ሌላውን ደግሞ ታዛዥ አደረገው፡፡ ሔዋን ከአዳም ጎን ትገኝ እንጂ ወደ ኋላ መለስ ብለን የእርሱዋን ልደት ስንመረምረው በአንድ አካል እንደነበሩ ማስተዋል እንችላለን፡፡ …
በዚህ ምክንያት አንድ አካል እንደሆኑ ለማስረዳት ሲል እግዚአብሔር አምላክ ሴቲቱን ረዳት አላት፡፡(ዘፍ.218) እርሱ እግዚአብሔር አምላክ በአንድነትመኖራቸውና አባትና እናት ከመሆን ባለፈ አንድ አካል በማድረግ አከበራቸው፡፡ (ዘፍ.224)
 በሌላ መልኩ ደግሞ አባት ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ የራሳቸውን አካል አግኝተው በመጣመራቸው እጅግ ደስ ይሰኛል ፡፡ አባት ምንም ሀብት የተረፈው ባለጠጋ ቢሆን ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ ያላገቡ  ከሆኑ ውስጡ ምንም ዐይነት መረጋጋት አይኖረውም ፡፡ ይህን ታግሦ መኖርም አይቻለውም ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ልጅ ከእናቱ አካል ተከፍሎ የተወለደ ቢሆን በዚህ ምድር ዘሩ እንዲቀጥል ብቻውን በቂ አይደለም ፡፡ ስለዚህም በራሱ ሙሉ አይደለም ማለት ነው ፡፡ ስለዚህም ነቢዩ ሚልክያስእግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን ? እርሱም የሚፈልገው ምንድን ነው ? ዘር አይደለምን ? (ሚል.፪፥፲፭) አለን፡፡
እንዴት ነው ታዲያ አንድ ሥጋ ወደ መሆን የሚመጡት ? እጅግ ንጹሕ የሆነን ወርቅ ማግኘት ከፈለግህ ወርቅህን ከሌላ ወርቅ ጋር ትቀይጠዋለህ፤ ከእነዚህም አንድነት ልዩ የሆነ ወርቅ ይገኛል ፡፡ በዚሁ መልክ እናት በደስታ ዘርን ተቀብላ ከራሱዋ ጋር በማዋሐድ ፅንሱን በመመገብና እንክብካቤ በማድረግ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም እንዲመጣ የራሱዋን ድርሻ ትወጣለች ፡፡
 ልጅ እንደ ድልድይ ነው ፡፡ በእርሱም ምክንያት ሦስቱ አካላት አንድ ሥጋ ይባላሉ ፡፡ ልጅ ሁለቱ አካላት ፍጹም አንድ እንዲሆኑ ያደረጋቸዋል ፡፡ በመካከላቸው ባለው ታላቅ ወንዝ ምክንያት የተለያዩ ከተሞች በወንዙ ላይ በሚሠራው ድልድይ ምክንያት ሁለት መሆናቸው ቀርቶ አንድ እንዲሆኑ እንዲሁም ልጅም በባልና በሚስት መካከል ፍጹም የሆነ አንድነትን ያመጣል፡፡(ቅዱስ አምብሮስ ወንድን አእምሮ(mind) ሲለው ሴትን ደግሞ ስሜት(sense) ይላታል፡፡ይህ በእርግጥ "ወንድ የሴት ራስ ነው ሴትም አካሉ ናት" ከሚለው የወንጌል ቃል የወጣ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡  ሁለቱ የሚጣጣሙ አይደሉም፤ ስሜት ደስ በሚያሰኘውና በሚታየው ነገር ላይ የሚተጋ ሲሆን አእምሮ ግን ነገሮች ከመፈጸማቸው በፊት ጥቅምና ጉዳታቸውን መለየትና ረቂቁን መንፈሳዊ የሆነውን ዓለም ለመረዳት መጣር ይታይበታል፡፡ነገር ግን አንዱ አንዱን ይፈልገዋል፡፡ እነዚህ አንድ ሲሆኑ ምድራዊውንም ሰማያዊውንም ነገር በአግባቡ መከወንና መገልገል ይቻላል፡፡ ስለዚህም ደስተኛ የሆነ ኑሮ ይኖረናል፡፡ ወንዱ ለጽንሰ ሃሳቦች እንጂ ለምድራዊው ነገር እምብዛም ስለሆነ እግዚአብሔር ከሰጠው ከምድራዊው በረከት ሳይጠቀምበት ይቀራል፡፡ ሴት ልጅ ደግሞ ተጨባጭ ባልሆነው መንፈሳዊ በሆነው አስተሳሰብ መማረክ ዝንባሌዋ ስላልሆነ ብቻዋን በመሆኑዋ ይህን በማጣት ትጎዳለች፡፡ አንድ ሲሆኑ ግን ሁለቱ አንዱ ያንዱን ገንዘቡ ስለሚያደርግ ሕይወታቸው ሙሉ ይሆናል፡፡ ልጅ ደግሞ ይህን ውሕደት ፍጹም ያደርገዋል፡፡)  
ልጅ በፊት በባልና በሚስት መካከል የተፈጠረውን አንድነት ይበልጥ ያጠናክረዋል ፡፡ ለባልና ሚስት ድልድይ የሆነው ልጅ የሁለቱ ተዋሕዶ ውጤት ነውና ፡፡ ራስና ቀሪው አካል በአንገት አንድ እንዲሆን እንዲሁ ልጅም በባልና በሚስት መካከል ሆኖ በእነርሱ መካከል ያለውን አንድነት ይበልጥ ያጠብቀዋል ፡፡ ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸውን በልጅ ምክንያት ይበልጥ እየጠበቀ ይመጣል ፡፡
እንዲሁም ዘማርያን በአንድነት ሲዘምሩ ዝማሬው አንድ ሆኖ ይወጣል ፡፡ ወይም ሁለት ወገኖች እጃቸውን እርስ በእርሳቸው ቢያቆላልፉ ከእንግዲህ አንድ እንጂ ሁለት አይደለንም ማለታቸው እንደሆነ እንዲሁ ባልና ሚስትም በአንድነታቸው በሚፈጥሩትልጃቸው በኩል ፍጹም የሆነ አንድነትን ይመሠርታሉ ፡፡ ስለዚህ ጌታች ግሩም በሆነ ቃሉሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ አለበተለይ በልጆቻችው፡፡ እንዲህ ሲባል ባልና ሚስት ልጅ ካልወለዱ ሁለት እንደሆኑ አይቀጥሉም ማለት ነውን ? በፍጹም አይደለም ሁለቱ በሥጋ ሲተባበሩ አንድ አካል ወደ መሆን ይመጣሉ፡፡ የሽቶ ዘይትን ከሌላ የሽቶ ዘይት ጋር ሲደባልቁት አንድ እንዲሆኑ ከተቀየጡም በኋላ አንድ የሽቶ ዘይት እንዲሆኑ እንዲሁ በዚህም እንዲሁ ነው፡፡
 እኔ አሁን እንዲህ በግልጽ ስለዚህ ጉዳይ በመናገሬ አንዳንዶች ነውር ነው በማለት ትምህረቴን እንደሚጠየፉት እረዳለሁ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው ? ይህን አሁን የምናገረውን እንደ ብልግና ንግግር ስለሚቆጥሩት ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች በትዳር ውስጥ የሚፈጠረውን እንደዚህ ላለው አንድነት ልዩ የነቀፋ ስም ይሰጡታል (ብልግና ይሉታል)፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስመጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን”(ዕብ.፲፫፥፬) ብሎ አስተምሮናል፡፡
ስለምን እናንተ ክቡር የሆነውን እንደ ነውር ንጹሕ የሆነውን እንደ ርኩስ ትቆጥሩታላችሁ ? ይህ ጋብቻን እንደ ርኩሰት የሚቆጥሩትና በራሳቸው አካል ላይ ዝሙትን የሚፈጽሙከሃድያን አመለካከት ነው ፡፡ ስለዚህም ነው ይህን ክፉ አስተሳሰብ ለማጥራትና ወደ ቀድሞው ክብሩ ለመመለስ ስል በዚህ መልክ ያስተማርኩት ፡፡ በዚህም አስተምህሮ የከሃድያን አፍ ይዘጋል፡፡
 እነርሱ የእግዚአብሔርን ድንቅ ስጦታንና የልደታችን መሠረት የሆነውን ተራክቦን ሲነቅፉት ይሰማሉ፡፡ ይህን የመገኛችን ምንጭ የሆነውን ተራክቦ እንደ ቆሻሻና እንደማይጠቅም ረብ የለሽ ከንቱ ነገር አድርገው ይቆጥሩታል ፡፡ ስለዚህ እኛ ይህን አስተምህሮ ከዚህ ዓይነት አመለካከት ንጹሕ ልናደርገው ይገባናል ፡፡
ተወዳጆች ሆይ ይህ ጉዳይ ሲነሣ እንደሚጠየፉት ከሃዲያን እንድትሆነ አልሻም ይልቁንስ ከእነርሱ አጸያፊ ሥራ ትሸሹ ዘንድ እመክራችኋለሁ ፡፡ ነገር ግን በዚህ እነርሱን የምትመስሉዋቸው ከሆነ በቀጥታ እግዚአብሔርን እየተሳደባችሁ ነው፡፡
ትዳር ለቤተክርስቲያን የተፈጸመላት ምሥጢር ምሳሌ እንደሆነ ላስረዳችሁን ? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን የራሱ ሲያደርጋትና በመንፈሳዊ ተዋሕዶ ከእርሱዋ ጋር አንድ ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ “እንደ ንጽሕት ድንግል” ይልና “እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለውና” ይለናል ፡፡(፪ቆሮ.፲፪፥፪) ታዲያ እኛ ምን ሆንን ? የእርሱ የአካል ሕዋሳቶችና “ሥጋው” አልሆንምን? ይህን ሁሉ በማስተዋል ታላቅ ምሥጢር የሆነውን ትዳርን ከማቃለል እንቆጠብ፡፡ ሠርግ ማለት የክርስቶስ በሰዎች መካከል ሰለመገኘቱ የሚመሰልበት ታላቅ ምሥጢር ነው ፡፡ ታላቅ የሆነው ይህ ምሥጢር በሚፈጸምበት ቦታ ስካር የሚገባ ነውን ? ንገረኝ የንጉሥ ምስል በቆመበት ስፍራ ሆነህ እርሱን ማዋረድ ትጀምራለህን ? ይህን ፈጽሞ አታደርገውም ፡፡
አሁን ግን ሰርግ ሲሰረግ ሰርጉ ለተመሰለበት ምሳሌ ተገቢውን አክብሮት ከመስጠት ይልቅ ቦታውን የኃጢአት መፍለቂያ ምንጭ አድርገነዋል፡፡ ሥርዐቱ ሙሉ ለሙሉ ተለውጦ ሕገወጥ ሥራዎች የሚፈጸሙት ሆኑዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸው” አላለንምን ? እንዲሁም “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ ፡፡”(ኤፌ.፭፥፬፤፬፥፳፱) ብሎ አላስተማረንምን ? አሁን ግን በዚህ ታላቅ በሆነ ምሥጢር ላይ የስንፍና ንግግር፣ ዋዛ ፈዛዛ ነገሮች፣ ፌዝና ቀልዶች ሞልተውበታል ፡፡
እነዚህ ከንቱ ነገሮች በቀላሉ የሚቀርቡም አይደሉም እኮ፤ እነዚህ ከንቱ ነገሮች እንደ ጥበብ ተቆጥረው በአቅራቢዎቻቸው ተቀናብረው በሰርጉ ለታደሙት ይቀርባሉ፡፡ ይህንንም ለሚያቀርቡ ሰዎችም ታላቅ ክብርና  ምስጋና ይሰጣቸዋል ፡፡ ይገርማል ኃጢአት እንደ ጥበብ ተቆጠረች፡፡ ከዚህም በላይ ኃጢአትን ለእኛ የሚያስተዋውቁትን ትዕይንት የምንከታተለው በተመስጦና በጸጥታ ሆነን ነው ፤ ከአንደበታቸው የሚያወጡትንም ቃል በማድነቅ እንሰማቸዋለን እንጂ እንዲያው በከንቱ አናዳምጣቸውም፡፡ ስለዚህ ለዲያብሎስ በዚህ የሰርግ ቤት ለእርሱ ወታደሮች የሚሆኑትን ለመመልመል ተመቸው፡፡ ስካር ባለበት ቦታ ዝሙት አለ፡፡ ከንቱ ንግግር ባለበት ቦታ ሰይጣን ሥራውን ለመሥራት ይመቸዋል፡፡ እስቲ ንገረኝ እንዲህ በሆነ ቦታ ሰይጣን እንዲገኝ እየጋበዝህ ክርስቶስ የሚገኝበትን ምሥጢር እየፈጸምኩ ነው ትላለህን?
አንተ እኔን ለዚህ ነገር ጠንካራ ተቃዋሚ እንደሆንኩ አድርገህ ትቆጥረኛለህ ፡፡ ከዚህ ጥመትህ ትድን ዘንድ አንተን በጽኑ የሚገሥጽህንም ሰው እንዲህ እንድትመለከተው አውቃለሁ ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ አንተን “የምትበሉም የምትጠጡም ብትሆኑ ወይም ማናቸውም ተግባር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት”(፩ቆሮ.፲፥፴፩) አላለህምን ? አንተ ግን ሥራዎችህን ሁሉ ራስህን ለማዋረድና የሰው ልጅን ለሚጎዱ ነገሮች ታውላዋለህ፡፡ ነቢዩስ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ በረዓድም ደስ ይበላችሁ”(መዝ.፪፥፲፩) አላለህምን ? አንተ ግን ሥርዐት አልባ ሆነህ ትመላለሳለህ ፡፡
በአንድ ጊዜ ደስታውንና ጥንቃቄውንም ማስኬድ ትፈልጋላችሁን ? አጥንትን የሚያለመልም መዝሙርን መስማትስ ትሻላችሁን ? በእርግጥ ከመዝሙሮች ሁሉ የሚልቅ መዝሙርን ልትሰሙ ትችላላችሁ ፡፡ እናንተ ግን አትፈቅዱም ፤ ብትፈቅዱ ግን  ሰይጣናዊ ዘፈኖች ከመስማት ይልቅ መንፈሳዊ ዝማሬን ለመስማት ትበቃላችሁ ፡፡ የመዘምራንን ግሩም የሆነ ሽብሻቦ መመልከት ትሻላችሁ ? እነሆ የመላእክት ዝማሬና ሽብሻቦ ፡፡ እንዴት ሆኖ ነው የእነርሱን ዝማሬን መስማት ሽብሻቦአቸውንም መመልከት የሚቻለው ብሎ የሚጠይቀኝ ካለ “እነዚህን ግሳንግሶችን ከነአካቴው ከተውክና በሰርግህ ክርስቶስ እንዲገኝ ከፈቀድክ ብቻ ይሆናል፡፡ ክርስቶስ በሰርግህ የታደመ ከሆነ መላእክትም ከእርሱ ጋር በሰርግህ ይገኙልሃል ፡፡
ከአንተ ዘንድ ፈቃዱ ካለ እርሱ በአንተ ሰርግ መገኘት ብቻ አይደለም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት በመቀየርም ሰርግህን ያደምቅልሃል፡፡ እንደ ውኃ ቀዝቃዛና ወራጅ የሆነውን የዚህን ዓለም ደስታና ፈንጠዝያ አጥፍቶ መንፈሳዊ ደስታን ከሚያጎናጽፈው ከዚህ ተአምር በላይ ምን ድንቅ ተአምር አለ!! ይህ ነው ውኃውን ወደ ወይንነት የመቀየሩ ትርጉም ፡፡ እንቢልታ ነፊዎች ባሉበት ክርስቶስ ፈጽሞ አይገኝም ፡፡ እርሱ በዚህ ሰርግ ቢገኝ እንኳ መጀመሪያ ይህንን አስወግዶ ነው ፡፡ ከዚያም የራሱን ተአምርን ይፈጽማል፡፡ ከዚህ የሰይጣን መሳሪያ ከሆነ እቢልታ በላይ ምን የሚጠላ ነገር አለ ? ሁሉ በሥርዐት ካልሆነ ምንም ነገር ያለጥቅም ይሆናል፡፡ ድካማችን ሁሉ ያለፍሬ ይቀራል እኛንም ወደ ውርደት ይጥለናል ፡፡ 
ከመልካም ሥነምግባር የበለጠ አስደሳች ነገር የለም ፣ ሥርዐት ወዳድ ከመሆን የበለጠ ጣፋጭ የሆነ ነገር የለም ፣ ጽድቅ ለመፈጸም ቆራጥ ከመሆን የበለጠ ተወዳጅ ነገር የለም ፡፡ ሁሉም ሥርዐቶቻችን ልክ እኔ ስለጋብቻ ሥነ ሥርዐት ባስተማርኩት መልክ ይሁኑ ፡፡ እንዲህ ከሆነ ደስተኛ ልንሆን እንችላለን ፡፡
 ነገር ግን ጋብቻን ሊያደርግ የሚሻ ሰው ከማን ጋር ጋብቻውን መፈጸም እንዳለበት ይጠንቀቅ ፡፡ ሴት ልጅ ያለችው ሰው አስቀድሞ እውነተኛና እርሱዋን ሊንከባከባት የሚችል ባልን ሊፈልግላት ይገባል ፡፡ እንዲህ ዓይነት ወንድ ለአካል ራስ እንዲሆን ሊመረጥ ይገባዋል ፡፡ ለእርሱ ስትሰጥም እንደ ባሪያ አድርጎ ሊይዛት ሳይሆን እንደ ልጁ ሊያያት ሊሆን ይገባል ፡፡
ሀብት ስላለው ወይም ከከበረ ቤተሰብ በመሆኑ ወይም ሰፊ ግዛት ስላለው እርሱን ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ አትምረጡ ፡፡ ነገር ግን በነፍሱ ትሑት፣ አስተዋይ ፣ ቅንነት ያለውና እግዚአብሔርን የሚፈራ የሆነን ሰው ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ምረጡ ፡፡ እንዲህ ከሆነ የምታፈቅሩዋት ልጃችሁ በደስታ ልትኖር ትችላለች ፡፡ ባለጠጋ ሆኖ በምግባሩ ግን ብልሹ የሆነን ሰው ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ያጫችሁት ከሆነ እርሱዋን አለመጥቀማችሁ ብቻ ሳይሆን እርሱዋን ነጻ ሰው ከማድረግ ይልቅ የእርሱ ባሪያ በማድረግ ትጎዱአታላችሁ ፡፡ ልጃችሁ የእርሱ ሚስት በመሆኑዋ ምክንያት በምታገኛቸው ሀብት ደስ ከመሰኘት ይልቅ እርሱዋን እንደ ባሪያ ቆጥሮ በእርሱዋ ላይ የሚያደርስባት በደል የከፋ ይሆናል ፡፡
እንዲህ ዐይነት ድርጊትን ከመፈጸም ትቆጠቡ ዘንድ እለምናችኋለሁ ፡፡  ነገር ግን ከእርሱዋ ጋር ተቀራራቢ ኑሮ ያለውን ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ታጩ ዘንድ እመክራችኋለሁ ፡፡ ይህ ባይሆን ምንም ሀብት ለሌለው ነገር ግን በጎ ሕሊና ላለው ሰው ትድሩዋት ዘንድ አሳስባችኋለሁ ፡፡ እንዲህ በማድረጋችሁ ልጃችሁን ሌላው ቢቀር ለአንድ ጌታ ልጃችሁን እንደባሪያ ከመሸጥ ተቆጥባችሁ በትክክለኛው ትርጉም እንደ ባል ሊሆናት ለሚችል ሰው መስጠት ይቻላችኋል ፡፡  
ለልጅህ ባል የሚሆናትን ጥሩ ሥነ ምግባር የተላበሰውን ሰው በጥንቃቄ መርምረህ በማግኘት  ልትድራት ስትዘጋጅ ክርስቶስ ኢየሱስ በጋብቻው ሥነ ሥርዐት ላይ  እንዲገኝልህ ጥራው፡፡ በዚህ የደስታ ቀንህ እርሱን በእንግድነት እንዲገኝ  ስለጋበዝከው ቅር አይሰኝም ፡፡ ምክንያቱም እርሱ የሚገኝበት ምሥጢር ነውና ፡፡ አዎን ከዚሀ ይልቅ ግን አስቀድመህ ለልጅህ ባል አድርገህ ያጨኸውን ሰው  እርሱ እግዚአብሔር ተወዳጅ ባል ያደርገው ዘንድ ለምነው ፡፡
የአብርሃም ባሪያ እንኳ ያላደረገውን አስከፊ ድርጊት ከማድረግ ግን ራስህን ጠብቅ ፡፡ እርሱ በጌታው በአብርሃም በተላከ ጊዜ እግዚአብሔርን መንገዱን ያቀናለት ዘንድ ለምኖት ነበር ፡፡ እንዲህ በማድረጉም ሁሉ ነገር ሰመረለት ፡፡ እንዲሁ አንተም ለልጅህ ባልን በመፈለግ አእምሮ ቢባክን ወደ እግዚአብሔር  “ጌታ ሆይ አንተ የፈቀድከውን አድርግ”  ብለህ ጸልይ ፡፡ ለእርሱ እንዲህ በማለት ፈቃድህን አሳልፈህ ስጠው፡፡ በዚህ መልክ ለእርሱ ክብርን ስጥ ፤ እርሱም በምላሹ ፈቃድህን በመፈጸም ያከብርሃል ፡፡
በእርግጥ አንተን ሁለት ሥራዎች ይጠብቁሃል፡፡ እነርሱም ፈቃድህን ለእርሱ ሙሉ ለሙሉ መስጠትና ፣  እርሱ የመሰከረለትን በጥሩ ሥነ ምግባር የታነጸውን ሰው መሻት ናቸው፡፡
የልጅህን ሰርግ ለመሰረግ በምትዘጋጅበትም ጊዜ እቃዎችንና ልብሶችን ለመዋስ ስትል ቤት ለቤት አታዙር፡፡ ምክንያቱም ሰርጉ የሚፈጸመው ትዕይንትን ልታቀርብ ወይም የልጅህን ቁንጅና ልታሳይበት አይደለምና ፡፡ በመሆኑም ሰርጉህን ልትፈጽም በምትዘጋጅበት ጊዜ ባለህ ነገር ብቻ ቤትህ ለማስዋብ ሞክር ፡፡ በመቀጠል ጎረቤቶችህን ወዳጆችህንና የቅርብ ዘመዶችህን ጥራ ፡፡ እንዲሁም ጥሩ ባሕርይ አላቸው የምትላቸውን ሰዎች ከሰርጉ እንዲታደሙልህ ጋብዝ ፡፡ ሙዚቀኖችን ግን ፈጽመህ አትጥራ ለእነርሱ የምታወጣው ወጪ በራሱ ከፍተኛና ሊሆን የማይገባ ነው ፡፡  
ከእነዚህ ሁሉ አስቀድሞ ግን ክርስቶስን በሰርግህ እንዲገኝ ጋብዘው ፡፡ እርሱን እንዴት አድርገህ እንደምትጋብዘው ታውቃለህን ? “ንጉሡም መልሶ፡- እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላችዋል”(ማቴ.፳፭፥፵) እንዲል ድሆችን በሰርግ እንዲገኙ በማድረግ ክርስቶስን በሰርግህ እንዲገኝ ማድረግ ይቻልሃል ፡፡ ስለክርስቶስ ብለህ ድሆች በሰርግህ እንዲገኙ ስላደረግህ ሰርግህ የተበላሸ አድርገህ አትቁጠር ፤ ነገር ግን ሴሰኞችን በሰርግህ ብትጋብዝ ሰርግህ በእርግጥ የረከሰ ይሆናል፡፡ ድሆችን ወደ ሰርግህ መጥራትህ ሀብት ወደ ቤትህ እንዲገባ መጥራትህ ነው፡፡ ቅምጥሎችን ከሰርጉ እንዲታደሙ የጠራ እንደሆነ ግን ውርደትን እየጠራህ ነው ፡፡
ሙሽሪትን በወርቅ ጌጣ ጌጦች አታስጊጣት ነገር ግን በጥሩ ሥነ ምግባርና በጭምትነት አስጊጣት እነዚያን ነገሮች ፈጽመህ አትፈልጋቸው፡፡ ግርግርና ሁካት በሰርግህ ፈጽሞ አይኑር ፡፡ ሙሽራውን ጥራና ሚስቱን ይዞ ወደ ቤቱ ይግባ ፡፡ በምሳና በራት ግብዣህ ላይ አስካሪ መጠጦች አይገኙ፡፡ ነገር ግን ሰርግህ ደስታ የሞላበት ይሁን፡፡
እንዲህ አድርገህ ሰርግህን በመከወንህ ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሆንክ ለማስተዋል እንድትችል በዘመኑ ሰርግ ተብለው ከሚቆጠሩት ጋር ያንተን የሰርግ ሥነ ሥርዐት አስተያይ፡፡ ሌላው ይቅርና ያንተን ሰርግ የተመለከተ ሰው ሁሉ የቁንጅና ውድድር ሳይሆን በእውነተኛ ትርጉም ሰርግን እንዳየ ምስክርነትን ይሰጥሃል፡፡ በዘመኑ ሰርግ ተብለው ከሚጠሩት ውስጥ ግን እጅግ የበዙ ክፋቶች ታጭቀው ይገኙበታል፡፡
 በአዳራሽ የሚፈመው ሰርግ በጥንቃቄና እግዚአብሔርን በመፍራት ከሚደረገው ጋር ሲነጻጸሩ በቶሎ የሚጠናቀቁ ሰርጎች አይደሉም፡፡ ከዚህም ባለፈ በውሰት የመጡት እቃዎች ሊጠፉም ስለሚችሉ ፍጻሜው ከደስታ ይልቅ ሊቋቋሙ ከማይችሉት ከከባድ ሃዘን ውስጥ ሊጥል ይችላል ፡፡ ይህ የከበደ ሃዘን በአማች ላይ የሚታይ ነው ፡፡ ነገር ግን ሙሽሪትም ከዚህ ሃዘን ነጻ ልትሆን አትችልም፡፡ በሰርጉም ፍጻሜ የቤቱ ውበቱ ጠፍቶ በሃዘን ተወሮ ይታያል፡፡
በጥንቃቄና እግዚአብሔርን በመፍራት በሚከናወነው ሰርግና በአሕዛብ ልማድ በሚፈጸመው ሰርግ መካከል ሰፊ የሆነ ልዩነት አለ፡፡ በዚያ ክርስቶስ ሲገኝ በዚህ ግን ሰይጣን ነግሦ የታይበታል፡፡ በዚያ ፍጹም የሆነ ፍስሐ ሲታይ በዚህ ደግሞ ጥቅ ያጣ አለባበስ ይተዋወቅበታል፡፡ በዚያ ፍጹም ደስታ ሲኖር በዚህ ግን ሕማምና ሰቆቃ ይተርፈዋል ፡፡ በዚህ የወጣው ወጪ ታላቅ ሲሆን በዚያ ግን እዚህ ግባ የማይባል ወጪ ብቻ ያስተናግዳል፡፡ በዚህ ግርግርና ሁካታ ሲታይ በዚያ ግን ግብረ ገብነት ጎልቶ ይንጸባረቅበታል፡፡ በዚያ ኃጠአት ሠልጥና ስትታይ በዚህ ግን ጽድቅ ነግሣ ትታያለች፡፡ በዚያ ሰካሮች ሲኖሩባት በዚህ ግን ሰላም ወዳዶች ይታዩባታል፡፡ በዚያ ሁካታና ጠብ ሲኖር በዚህ ግን ጸጥታና ሰላም ሰፍነው ይታዩበታል፡፡
እነዚህን ሁሉ ልብ በሉ፡፡ እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘት እርሱን ለሚያፈቅሩት ካዘጋጀው ከመንግሥቱ ተካፋዮች እንድንሆን ከዚህ ቀን ጀምረን ይህን ክፉ ልማድ ከራሳችን አርቀነው እናስወግደው፡፡ የሰውን ልጅ ከመውደዱ የተነሣ ሰው በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር አብ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም እስከዘለዓለሙ አሜን !!   

2 comments:

  1. wenidima yihn timihiri bezi zemen magignet mechal metadel new segawin yabizalihi yabatochin bereke yiderbibh yiderebin

    ReplyDelete
  2. በጣም አመሰግናሁ!
    አቤቱ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አምላክ ሆይ እንዲህ የሚመክሩንን ወንድሞችና እህቶች አታሳጣን!
    ዲ/ን ሽመልስ በጋብቻ ዙሪያ የጻፍከውን መጽሐፍ የት ማግኘት እችላለሁ?

    ReplyDelete