Tuesday, May 22, 2012

“ዕንቁ ክርስቶስ በቅዱስ ኤፍሬም”



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/09/2004

ከዕለታት በአንዱ ቀን ከወንድሞቼ በስጦታ ዕንቁ ተቀበልኩኝ፤ በዚህ ዕንቁ ውስጥ ታላቅ የመንግሥቱን ምሥጢርንና የገዢው የክርስቶስን ምሳሌ ተመለከትኩ፡፡ ዕንቁ ለእኔ ጥሩ የውኃ ምንጭ ሆነልኝ ፤ከዚህም ምንጭ የእግዚአብሔር ልጅን ምሥጢር ጠጥቼ ረካሁ፡፡
ወንድሞቼ ሆይ የሰጣችሁኝን ዕንቁ እመረምረው ዘንድ በማሃል እጄ ያዝኩት ፡፡ ወደ ዐይኖቼም አቅርቤ ዙሪያውን ተመለከትኩት እናም ይህ ዕንቁ በሁሉም አቅጣጫ ዐይኖች እንዳሉት አስተዋልኩ፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስን ብርሃን ነው ብንልም ፈጽሞ ልንመረምረው እንደማንችል ተረዳሁ፡፡
በዕንቁ ብሩህነት በባሕርይው ምንም ጨለማ የሌለበትን የእግዚአብሔር አብ ብቸኛ ልጁን ተመለከትኩ፡፡ በእርሱም ውስጥ ግሩም የሆነውም ንጽሕናውን አስተዋለኩኝ፤ ከእኛም የነሣውንም ሥጋ ቅድስናውንና ንጽሕናውን ተረዳሁ፡፡ በዚህ ዕንቁ ውስጥ ያየውትን ያለመከፈል አንድ የሆነውን የሥጋንና የመለኮትን ተዋሕዶ ተመለከትኩ፡፡
በዕንቁው ውስጥ እንዲሁ የእርሱን ንጹሕ የሆነውን ፅንሰት አስተዋልኩ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በምትሰኘው ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን የተፈጸመውን የእግዚአብሔር ልጅ ፅንሰትን ተረዳሁ፡፡ እርሱዋ እርሱን የተሸከመችው ደመናው ናት፡፡ የእርሱዋም ምሳሌ ሰማይ ነው፡፡ ከእርሱዋም የጽድቅ ፀሐይ በመውጣት ለዓለም አበራ፡፡


በዚህ ዕንቁ ውስጥ የእርሱን ተዋጊነት፣ ድል አድራጊነትና አክሊሎቹን ተመለከትኳቸው፡፡ የእርሱን ቸርነትንና እንደ ጅረት ሞልቶ የሚፈሰውን የጸጋ ስጦታውን ተመለከትኩ፡፡ የእርሱ ሕቡዕ የሆነው ማንነቱ እርሱ ለእኛ በገለጣቸው መገለጦች እንደታዩ አስተዋልኩ፡፡
ከመርከብ ይልቅ የዚህ ዕንቁ ነገር በእጅጉ አስገርሞኛል፡፡ በውስጡ አንዳቸው በሌላው ላይ የተነባበሩ ጥላ የሌለባቸው የብርሃን ልጃገረዶችን ተመለከትኩ፡፡ አንደበት ሳይኖራቸው ከውስጣቸው ድምፅን ያወጣሉ፡፡ ከንፈር ሳይኖራቸውም ምስጢራትን ይናገራሉ፡፡ ድምፅ የማያወጡ በገናዎች ሆነው ጣዕም ያለው ዝማሬን ያዜማሉ፡፡
በእርሱ ዘንድ ዋሽንት ጣዕም አልባ ነው፤ ነጎድጓድም ድምፅ የለውም፡፡ የተገለጠልንን ከማድነቅ ባለፈ ለምን ብለን የምንመረምረው አይደለም፡፡ ከሰማያት ሰማያዊው  ምሥጢር እንደ ዝናብ ዘንቦ የእኛም ጆሮዎች እንደ መሬት ንቃቃት  ተከፍተው ከደመናው ከሚወርደው ትርጓሜ ጠጥተው ረኩ፡፡
ከመና ይልቅ ቃሉ ብቻውን የሰማውን ሁሉ ያጠግባል፡፡ ደስ ከሚያሰኙ ምግቦች ይልቅ ይህ ዕንቁ በመጽሐፍ ቅዱስ ቦታ ሆኖ ከእርሱ የማነባቸውና የማገኛቸው ማብራሪያዎች ደስ አሰኙኝ፡፡
ይህን ዕንቁ "ሌላ አንተ ያልገለጥክልኝ ተጨማሪ ምሥጢራት አሉን? ብዬ ብጠይቀው ለእኔ ይመልስልኝ ዘንድ አፍ የለውም፤ እኔን ይሰማበትም ዘንድ ጆሮ የለውም፡፡ ሌሎች የስሜት አካላቶች እንዳሉህ የተረዳሁ አንተ ግኡዝ ፍጥረት ሆይ እንዴት የምትደንቅ ነህ!!
ይህ ግኡዝ ፍጥረት ለእኔ እንዲህ ብሎ መለሰልኝ “እኔ እጅግ ጥልቅ ለሆነው ባሕር ሴት ልጁ ነኝ፤ በዚህም ምድር የተገለጥሁ  እኔ በሆዴ ታላላቅ ምሥጢራትን ይዣለሁ፡፡ነገር ግን እንዲህ ብዬ እመክራችኋለሁ ባሕር ውስጥ ያለውን ፍጥረት መርምሩ ነገር ግን የባሕሩን ጌታ አትመርምሩት፡፡
  እኔም ይህን ዕንቁ እጅግ ተደንቄ በመረመርኩት ጊዜ ልዩ ልዩ ሃሳቦች በአእምሮዬ ውስጥ ተመላለሱብኝ፡፡ ዕንቁ አሳሾች ከጥልቁ ባሕር በመጥለቅ አስሰው በማግኘት ወደ ምድር ያመጡታል፡፡ ነገር ግን ባገኙት ስለማይረኩ ተመልሰው ወደ ጥልቁ ባሕር ወርደው ያስሱታል፡፡ በባሕር ውስጥ ያለውን መዛግብት ፈትሸንና መርምረን ልንደርስበት ካልተቻለን እንዴት ጥልቅና እጅግ ሰፊ የሆነውን የእግዚአብሔርን ባሕርይ ተመራምረን ልንደርስበት እንችላለን?
የልጁ የምሥጢሩ ማዕበላት በበረከቶች ሁሉ የተሞሉና የማይመረመሩ ናቸው፡፡ ይህን አስተውለህ ካላወቅህ አሁን የምነግርህን ልብ በል፡፡ የባሕሩ ማዕበላት ምንም እንኳ መረከቡ ከእነርሱ ይልቅ ጠንካራ ቢሆንም በነውጣቸው ወደ ስብርባሪነት ይለውጡአታል፡፡ ነገር ግን እነርሱ አውቀው ለመርከቢቱ ሲሸነፉላት በደኅንነት ትጓዛለች፡፡ ይህቺው ባሕር ግብፃውያንን አንዳች ሳይገምቱት ውጦ አጠፋቻቸው፡፡ ለእስራኤላውያን ግን ለሁለት ተከፍላ በደረቅ ምድር እንዲሻገሩ አደረገቻቸው፡፡ይህን ሁሉ እግዚአብሔር ደካማ በምትባለው ውኃ አሳየን፡፡ ይህች ባሕር በላዩዋ ያሉትን ወደ እርሱዋም የገቡትን እንዲህ የምታድርግ ከሆነ ሁለመናህ በእርሱ እጅ የተያዝክ አንተ በኃጢአት ጨክነህ በመኖርህ አንተ ከእርሱ እጅግ ልታመልጥና በሕይወት ልትቆይ ትችላለህን?
 “በባሕር ውስጥ የሚመላለሰው ዓሣትና ሌዋታንም በእነዚህ ሰዎች ላይ ያንጎራጉራሉ” (ሆሴ.4፡3፤ሶፎ.1፡3)በእርሱ ምክንያት መጥፋትን አይፈቅዱምና፡፡ ይህን ሰምቶ ወደ ስህተት የሚገባ እንዲህ ዓይነት ድንጋይ ልብ ያለው ሰው አይተህ ታውቃለን?  ምንም እንኳ ፍርዱ ቢዘገይ በተገለጠ ጊዜ ግን እንዴት የሚያስፈራ ነው!!!
ለሦስት ቀናት ዮናስ የእኔ ጎረቤት ሆኖኝ ነበር፡፡ በባሕር ውስጥ ያሉ ዓሣት ስለእርሱ ክፉ እንዳያገኛቸው ብለው በፍርሃት ርደው እንዲህ አሉ “ከእግዚአብሔር ፊት መኮብለል የሚቻለው  ማን ነው? ዮናስ ሸሸ ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን ሙግታቹሁ ሁሉ ከንቱ ይሆንባቸዋል፡፡ አለኝ ይህ ዕንቁ!!! ግሩም ነው ግሩም ነው!!!

3 comments:

  1. ከመርከብ ይልቅ የዚህ ዕንቁ ነገር በእጅጉ አስገርሞኛል፡፡ በውስጡ አንዳቸው በሌላው ላይ የተነባበሩ ጥላ የሌለባቸው የብርሃን ልጃገረዶችን ተመለከትኩ፡፡ አንደበት ሳይኖራቸው ከውስጣቸው ድምፅን ያወጣሉ፡፡ ከንፈር ሳይኖራቸውም ምስጢራትን ይናገራሉ፡፡ ድምፅ የማያወጡ በገናዎች ሆነው ጣዕም ያለው ዝማሬን ያዜማሉ፡፡
    በእርሱ ፊት ዘንድ ዋሽንት ጣዕም አልባ ነው፤ ነጎድጓድም ድምፅ የለውም፡፡ የተገለጠልንን ከማድነቅ ባለፈ ለምን ብለን የምንመረምረው አይደለም፡፡ ከሰማያት ሰማያዊው ምሥጢር እንደ ዝናብ ዘንቦ እኛም እንደ መሬት ንቃቃት ጆሮዎችህ ተከፍተው ከደመናው ከሚወርደው ትርጓሜ ጠጥተው ረካን፡፡

    ReplyDelete
  2. kemerkeb yilk yezih enqu neger be ejugu asgeremeg sitl algebagim bichalh tinsh btabraralg yikrta wendm...

    ReplyDelete
  3. ወንድሜ ወይም እኅቴ መርከብ የክርስቶስ፣ የቤተክርስቲያንና የመስቀል ምሳሌ ነው፡፡ በተለይ የኖህ መርከብ፡፡ ዕንቁ ግን ለቅዱስ ኤፍሬም በልጦበታል፡፡ ምክንያቱም ዕንቁ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግልና ስለመወለዱ፤ ስለልደቱ፣ ስለንጽሐ ባሕርይው ስለአዋቂነቱ ለማስረዳት የሚጠቅም ሆኖ ስላገኘው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባለፈ የቃሉ ምሳሌም ነው፡፡ እኛም በጥምቀት ያምናገኘውን ሰብእና በዕንቁ መስሎ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ ከውኃና ከመንፈስ ስንወለድ ያለንን ተፈጥሮ በዕንቁ ተፈጥሮ መረዳት እንችላለን፡፡ እንዲሁም ገና ያልደረስኩባቸው ቅዱስ ኤፍሬም ዕንቁን ከሌሎች ምሳሌዎች ይልቅ ገላጭ ሆኖ ስላገኘው ይሆናል ከመርከብ ይልቅ ያስደነቀው፡፡

    ReplyDelete