Friday, April 13, 2012

“ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ”?(በሳልማሱ ኤጲፋንዮስ)


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/08/2004
በዛሬይቱ ቀን እንግዳ የሆነ ነገር ተከሰተ፡፡ እነሆ በዛሬይቱ ቀን ምድሪቱ በታላቅ ዝምታ ተዋጠች፡፡ ንጉሡዋ ክርስቶስ በውስጡዋ ተኝቶአልና በምድር ውስጥ ታላቅ ጸጥታ ሰፈነ፡፡ እንዲሁም በዛሬይቱ ቀን ምድር ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ሰምታ የማታውቀው ታላቅ የሆነ ንውጽውጽታ በውስጧ ተሰማ፡፡ ምክንያቱም በሥጋ በውስጡዋ ያደረው አምላክ በነፍሱ ወደ ሲኦል በመውረድ በሲኦል ያሉትን ነፍሳት በማስነሣት ወደ ገነት አፍልሶአቸዋልና፡፡ እግዚአብሔር በሥጋ በመሞቱ ሲኦል ታወከች፡፡ እርሱ በነፍሱ የጠፋውን የእግዚአብሔርን በግ አዳምን ሊፈልግ በዛሬይቱዋ ቀን ወደ ሲኦል ወርዶአልና፡፡
አምላክና የዳግማዊቱ ሔዋን ልጅ የሆነው ክርስቶስ አዳምንና ሔዋንን ከታላቅ ሃዘን ለማውጣት በዛሬይቱ ቀን በነፍሱ ወደ ሲኦል ወረደ፡፡ በዛሬይቱ ቀን ጠላቱን ድል የሚነሣበትን መስቀሉን ተሸከሞ ሞትን በሥጋው ተቀበለ፡፡ እርሱን የፈጠረው አምላክ በእርሱ አርአያ በሲኦል ተገኝቶአልና አዳም በፊቱ ክርስቶስ በነፍሱ ቆሞ ሲመለከተው በታላቅ ፍርሃትና መደነቅ ተሞልቶ በዙሪያው ላሉት ነፍሳት “የጌታችን ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን"ብሎ በታላቅ ድምፅ የምስራች አላቸው፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስም “ከመንፈስህ ጋራ” ብሎ መለሰለት፡፡