Saturday, February 18, 2012

ጸሎት ዘቅዱስ ኤፍሬም (በዐቢይ ጾም የሚጸለይ)


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
11/06/2004
“የሕይወቴ ገዢ የሆንክ ጌታዬ ሆይ! ከስልቹነትና ከተስፋ መቁረጥ መንፈስ እንዲሁም ከንቱ ከሆነ ልፍለፋ ጠብቀኝ፡፡ ከዚህ ይልቅ  መንፈሳዊ ሙላትን ፣ ትሕትናን ፣ ትእግሥትን ፣ ፍቅርን አድለኝ፡፡ ንጉሤና አምላኬ ሆይ በወንድሜ ላይ በከንቱ ከመፍረድ ተከልክዬ የራሴን ኃጢአት ብቻ የማስተውልበትን ጸጋህን አድለኝ፡፡ ለአንተ ክብር ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን !!  

ጦምን አስመልክቶ የቅዱሳን አባቶች አስተምህሮ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
10/06/2004
“በጦም ወቅት አንድ ክርስቲያን  በፈቃደኝነት አንድ በጎ ሥራን  ጎን ለጎን ቢፈጽም መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ከሰዎች ምስጋናን ወይም አንዳችን ነገር ሽቶ የሚጦም ከሆነ ግን ጦሙ በእግዚአብሔር ዘንድ የማይወደድ ጦም ይሆንበታል፡፡ ማንኛውም በጎ ሥራ ስንሠራ ለእግዚአብሔር አምላካችን ካለን ፍቅር የመነጨ ይሁን፡፡ እንዲያ ካልሆነ ግን እግዚአብሔርን ደስ ልናሰኝ አይቻለንም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን ጌታችን በመንጎቹ ላይ ሲሾመው ለእርሱ ያለውን ፍቅር ተመልከቶ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን የሚያፈቅር ሰው የሚፈጽማቸው የትኞቹም በጎ ምግባራት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደዱለት ይሆኑለታል፡፡ ፍጹማንም ናቸው፡፡ ስለዚህም ማንኛውንም በጎ ሥራዎቻችንን ስንሠራ እርሱን በማፍቀር ላይ የተመሠረተ ይሁን፡፡”
“አንድ ሰው ምንም እንኳ መላ የሕይወት ዘመኑን በትህርምት ሕይወት መምራት ያለበት ቢሆንም በዚህ በዐቢይ ጦም ግን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኃጢአቱን  ለካህን ተናዝዞ ለድሆች ምጽዋትን በማድረግ በአግባቡ ሊጦም ይገባዋል፡፡ እነዚህን ዐርባ የጦም ቀናት በአግባቡ በጎ ሥራዎች አክለንባቸው የጦምናቸው እንደሆነ ቸሩ ፈጣሪያችን ዓመት ሙሉ ባለማወቅ የፈጸምናቸውን ኃጢአቶቻችንን ይደመስስልናል፡፡ (ዮሐንስ አፈወርቅ )

"በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም"(ካለፈው የቀጠለ)


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
10/06/2004
ይህ እንዲሆንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ስለመንጎቹ በመስቀል ላይ ሠዋ፡፡ ሙሽሪት ምዕመናንንም በደሙ ገዛት፡፡ ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ አንጽቶ ከጎኑ በፈሰሰውም ደሙ ቀድሶ የራሱ አደረጋት፡፡ እንዲያም ስለሆነ ለሰማያዊው ንጉሥ ሰማያዊት ሙሽራው ሆነችው፡፡ ሙሽሪት የተባልነው እኛ ነን፡፡ አሁን እኛ በክርስቶስ አምላክነት አምነን በሥላሴ ስም የተጠመቅን ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ የታደሰ ሰማያዊ ሰብእናን ገንዘባችን በማድረጋችን የእግዚአብሔር ልጆች ተሰኝተናል፡፡ስለዚህም የእግዚአብሔርን ጥልቅ የሆነ አሳብን እንኳ በመንፈስ ቅዱስ ታግዘን ለመረዳት እንችላለን፡፡ እንደ መንፈስ ቅዱስም ፈቃድ በመመላለስ ሰይጣንን ድል የምንነሣበትን የጽድቅ ጥሩርን ለብሰናል፡፡
አሁን አባታችን አዳም ሳይሆን እግዚአብሔር ሆኖአል፡፡ እንዲህም ስለተደረገልን አባ ብለን እርሱን ለመጥራት አናፍርም፡፡  ሆኖም የእግዚአብሔር ልጅነትን ሥልጣን በማግኘታችን ተረጋግተንና ተዛንተን መኖርን አግኝተናል ማለት ግን አንችልም፡፡ ምክንያቱም የአዳምን ንጽሐ ጠባይን ያልወደደውና ከክብሩ ያዋረደው ሰይጣን በቅናት ተነሣስቶ እኛን ለማሰናክል  መትጋቱ አይቀሬ ነውና፡፡ ይህም እንዲገለጥ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ በሰይጣን ይፈተን ዘንድ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ፡፡ ይህ የሚስተምረን ነገር አለ፡፡ እርሱም እኛ በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅነት ሥልጣን በማግኘታችን ዲያብሎስ በጠላትነት እንደሚነሣብንና ከልጅነት ክብራችን ለማሳነስ እንደሚተጋ ነው፡፡ ስለዚህም አባ አባ የምንልበትን የልጅነት መንፈስ በጥምቀት በማግኘታችን እኛን ለማሰናከል በእጅጉ እንደሚተጋ አውቀን እኛም በጦምና በጸሎት ጌታችንን መስለን ሰይጣንን ድል ልንነሣው ይገባናል፡፡ ነገር ግን እንዳው በልማድ ለምን እንደምንጦም ሳንረዳ የምንጦም ከሆነ በአዲሱ አቁማዳ አሮጌውን የወይን ጠጅ እንደመጨመር ይቆጠርብናል፡፡ እነዚህ እርስ በእርሳቸው አይጠባበቁምና አቁማዳው ይፈነዳል ወይኑም ይፈሳል፡፡ ስለሆነም ከጦማችን አንዳች ጥቅም ሳናገኝ የሰይጣን መሳለቂያ ሆነን እንቀራለን፡፡ እንዲያ እንዳይሆን መጪው የጦም ወቅታችን ራስን መግዛት የምንለማመድበትና የእግዚአብሔርን አሳብና ፈቃድ የምናቅበት ጦም እንዲሆን እንትጋ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ መጪውን ጦም እንዳው በልማድ ሳይሆን ሰይጣንን እንዴት ድል መንሳት እንደምንችል የምንማርበት ጦም ያደርግልን ዘንድ ፈቃዱ ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡