Monday, October 21, 2013

ጌታችን የእግዚአብሔር ምሥጢር የመባሉ ምክንያት



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

ቀን 11/02/2006
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለልደቱ ጥንት ለሕይወቱ ፍጻሜ የሌለው አልፋና ኦሜጋ ነው፡፡ በሥጋ ከመገለጡ በፊት ቅዱስ ዮሐንስበዓለምም ነበር ዓለሙ አላወቀውም ነበርእንዲል በዓለሙ ሙሉ ሆኖ የሚኖር እግዚአብሔር ነው፡፡ አንዳንዶች በዓለም ነበር ሲባሉ ለምድር መነሻ እንዳላት ለእርሱም መነሻ አለው እንዳይሉ  ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊውብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበርብሎ አስቀድሞ ጻፈልን፡፡
 በዓለም ነበር ሲልም ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛት እርሱ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ነገር ግን በሥጋ ማርያም አስኪገለጥ ድረስ ዓለም አላወቀችውም ነበር፡፡ አይደለንም እኛ መላእክት እንኳ አላዩትም፤ ነገር ግን ለእነርሱ በሰው አምሳያ ይታያቸው ነበረ፡፡ እነርሱም ለእርሱ አምልኮትን በአምሳያው ፊት ይፈጽሙ ነበር፡፡ እርሱ በሰው አምሳል ለመላእክት ተገልጦ ይታያቸው ነበር እንጂ በፍጹም እርሱነቱ ያልተገለጠ ማንም በማይቀርበው መለኮታዊ ብርሃን ውስጥ የሚኖረው ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱ ስሙ እውነተኛ ብርሃን የሆነ እኛን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ፡፡ ያም ማለት ሰው ሆነ፤ ለእርሱ አንድ ነገርን ለማድረግ መውጣት መውረድ የሚገባው አይደለም፤ ነገር ግን ሰው መሆኑን እንድንረዳ “ወደ ዓለም ይመጣ ነበር” ተብሎ ተጻፈልን፡፡

በክርስትና ያለ እምነት እስከዚህ ድረስ ይረቃል


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
11/02/2006
 ክርስቲያን በክርስቶስ እንደሞተ ሊያምን ሕይወቱም ከክርስቶስ ጋር እንደተሰወረ ወይም ሕይወቱ ከሕያዋን ቅዱሳን ጋር አንድ እንደሆነ ሊያምን ይገባዋል፡፡ በክርስቶስ ያለው ሕያውነት በፈቃድ በሚሆን ሞት ማለትም ጥምቀት የመጣ ነው፡፡ በፈቃዳችን በእምነት ከክርስቶስ ጋር ሞተን የትንሣኤውም ተካፋይ በመሆን በክርስቶስ ሕያዋን ሆነን እንኖራለን፡፡ አሁን ያለን ሕይወት ከሕያዋን ጋር አንድ የሚያደረገን ሕይወት ነው፡፡ በሥጋ ሞት ሞትንም አልሞትንም በክርስቶስ በተነሣነው ትንሣኤ ሁሌም ለዘለዓለም ሕያዋን ሆነን እንኖራለን፡፡ ስለዚህ ለአንድ ክርስቲያን የሥጋ ሞት ከሕያዋን ጋር የሚያቆራርጠው ወይም እነርሱ በሥጋ ስለተለዩት ከእርሱ የሚለዩት አይደለም ይልቅ በክርስቶስ አንድ ቤተሰብ በመሆን የአንድ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነው የሚኖሩበት ነው፡፡ ይህ በክርስቶስ ሞቼ ከክርስቶስ ጋር ተነሥቼለሁ አሁን ያለሁት ቅዱሳን በከተሙበት በሰማያዊ ሥፍራ ነው፡፡ እንዲያም ቢሆን በሥጋ ስላልሞትሁ በዚህ በሰማያዊ ሥፍራ ሆኜም ውጊያ አለብኝ በውጊያዬ ደግሞ ሰማያዊያን መላእክት እንደሚራዱኝ እንዲሁ በሰማያዊ ሥፍራ ፍጹም ዕረፍትን ያገኙ ቅዱሳን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ሆነዋልና እድን ዘንድ በጸሎታቸው ይራዱኛል የሚለው እምነት ከክርስቶስ ጋር ሞቼ በትንሣኤው ሕይወት ሕያው ሆኜ እኖራለሁ ብሎ ማመንን በብርቱ የሚጠይቅ እምነት ነው፡፡