በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
11/02/2006
ክርስቲያን በክርስቶስ እንደሞተ ሊያምን ሕይወቱም ከክርስቶስ ጋር እንደተሰወረ
ወይም ሕይወቱ ከሕያዋን ቅዱሳን ጋር አንድ እንደሆነ ሊያምን ይገባዋል፡፡ በክርስቶስ ያለው ሕያውነት በፈቃድ በሚሆን ሞት ማለትም
ጥምቀት የመጣ ነው፡፡ በፈቃዳችን በእምነት ከክርስቶስ ጋር ሞተን የትንሣኤውም ተካፋይ በመሆን በክርስቶስ ሕያዋን ሆነን እንኖራለን፡፡ አሁን ያለን ሕይወት ከሕያዋን ጋር አንድ የሚያደረገን
ሕይወት ነው፡፡ በሥጋ ሞት ሞትንም አልሞትንም በክርስቶስ በተነሣነው ትንሣኤ ሁሌም ለዘለዓለም ሕያዋን ሆነን እንኖራለን፡፡ ስለዚህ
ለአንድ ክርስቲያን የሥጋ ሞት ከሕያዋን ጋር የሚያቆራርጠው ወይም እነርሱ በሥጋ ስለተለዩት ከእርሱ የሚለዩት አይደለም ይልቅ በክርስቶስ
አንድ ቤተሰብ በመሆን የአንድ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነው የሚኖሩበት ነው፡፡ ይህ በክርስቶስ ሞቼ ከክርስቶስ ጋር ተነሥቼለሁ አሁን
ያለሁት ቅዱሳን በከተሙበት በሰማያዊ ሥፍራ ነው፡፡ እንዲያም ቢሆን በሥጋ ስላልሞትሁ በዚህ በሰማያዊ ሥፍራ ሆኜም ውጊያ አለብኝ
በውጊያዬ ደግሞ ሰማያዊያን መላእክት እንደሚራዱኝ እንዲሁ በሰማያዊ ሥፍራ ፍጹም ዕረፍትን ያገኙ ቅዱሳን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ
ካህናት ሆነዋልና እድን ዘንድ በጸሎታቸው ይራዱኛል የሚለው እምነት ከክርስቶስ ጋር ሞቼ በትንሣኤው ሕይወት ሕያው ሆኜ እኖራለሁ
ብሎ ማመንን በብርቱ የሚጠይቅ እምነት ነው፡፡
አሁን የምንኖርበት ሕይወት ጨለማ የሌለበት ቀን የሆነ እኛም የቀን
ልጆች የተባልን ከቀን ልጆች ከሆኑት ጋር የምንኖርበት ሕይወት ነው፡፡ ያም ማለት ሞት የሌለበት ከጊዜ ልኬት ከቦታ ወሰን በላይ
ሆነን የምኖርበት ሕይወት ነው፡፡ ባጠቃላይ በሰማያዊ ሥፍራ ነው ያለነው፡፡ በዚህ ሥፍራ ውስጥ ሕያዋን ቅዱሳን አሉ፡፡ እነርሱ በእረፍት
እኛ ደግሞ በክርስቶስ መንፈሳዊ ትጥቅን ታጥቀን ከእነርሱ ጋር ሆነን በክርስቶስ ድል የተነሣውን ዲያብሎስን ድል በመንሳት እንደ
እነርሱ የክርስቶስ ካህናት መሆን ነው ግባችን፡፡ ይህ ግን እምነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ከክርስቶስ ጋር ለዚህ ዓለም ተሰቅያለሁ ሞቻለሁ
ብሎ የሥጋ ሞት ከሕያዋን ጋር ይለያየኛል ብሎ ማሰብ ክርስትና በምትጠይቀው እምነት ውስጥ አለመኖር ወይም በክርስቶስ ያገኘነውን
ሕያውነት እንደ መጠራጠር ነው፡፡ በእርግጥ ክርስትና በምትጠይቀው እምነት ውስጥ ካለን በምድር ሳለን በሰማያዊ ሥፍራ ነን በሥጋ
ተለይተን በመንፈስ ከቅዱሳን ጋር አንድ ነን፡፡ ምክንያቱም በክርስቶስ ሞተናልና በትንሣኤውም በሰማያዊ ሥፍራ ካሉ ቅዱሳን ጋር
አንድ ቤተሰብ ሆነናልና፡፡
አሁን የምኖረው በክርስቶስ በሆነው ታላቅ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ
ነው ቅዱሳን መላእክት ያለእረፍት ክርስቶስን ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ አምልኮታቸውን ያቀርባሉ፡፡ በዚሁ በምድር ግን ሰማያዊ ሥፍራ
ላሉት ታናናሾች ለተባሉት ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ፡፡ እንዲሁ ቅዱሳንም ለወገኖቻቸው ከክርስቶስ ባገኙት የክህነት ሹመት
ከዲያብሎስ ጋር በፍልሚያ ላይ ላሉት ጸሎትንና ምልጃን እንዲሁም ልመናን ያቀርባሉ፡፡ ይህም ካህናት ሆነው ስለተሾሙ ነው፡፡ በሥጋ
ሞተዋል እኮ ከዚህ ዓለም ወጥተዋል ለሚል ሰው በእርግጥ አዎ በሥጋ ሞተዋል እኛም እኮ ከክርስቶስ ጋር ሞተናል በትንሣኤውም ተካፋዮች ሆነናል፡፡ ሕብረታችን
ከሕያዋን እንጂ ከሙታን ጋር አይደለም ስለዚህ ከእነርሱ ጋር በሰማያዊ ሥፍራ ነን፡፡ ታዲያ ስለምን ከእኛ ፈጽሞ እንደራቁ ይቆጠራል?
ይህ እኔ እንደምረዳው ክርስትና በምትጠይቀው እምነት ውስጥ ያለመኖር ውጤት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በክርስቶስ ባገኘሁት ሕይወት ሕያው
ነኝ ብሎ የሚያምን ቢሆን ኖሮ ቅዱስ ጴጥሮስ አሁንም ከእኔ ጋር ነው፡፡ጳውሎስም እንዲሁ ከእኔ ጋር ነው ቅድስት ማርያምም እንዲሁ
ከእኔ ጋር ናት ምክንያቱም በክርስቶስ ባገኘሁት ሕይወት ከእነርሱ ጋር ሕብረት ፈጥሬአለሁና ብሎ ባመነ ነበር፡፡
No comments:
Post a Comment