Monday, October 21, 2013

ጌታችን የእግዚአብሔር ምሥጢር የመባሉ ምክንያት



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

ቀን 11/02/2006
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለልደቱ ጥንት ለሕይወቱ ፍጻሜ የሌለው አልፋና ኦሜጋ ነው፡፡ በሥጋ ከመገለጡ በፊት ቅዱስ ዮሐንስበዓለምም ነበር ዓለሙ አላወቀውም ነበርእንዲል በዓለሙ ሙሉ ሆኖ የሚኖር እግዚአብሔር ነው፡፡ አንዳንዶች በዓለም ነበር ሲባሉ ለምድር መነሻ እንዳላት ለእርሱም መነሻ አለው እንዳይሉ  ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊውብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበርብሎ አስቀድሞ ጻፈልን፡፡
 በዓለም ነበር ሲልም ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛት እርሱ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ነገር ግን በሥጋ ማርያም አስኪገለጥ ድረስ ዓለም አላወቀችውም ነበር፡፡ አይደለንም እኛ መላእክት እንኳ አላዩትም፤ ነገር ግን ለእነርሱ በሰው አምሳያ ይታያቸው ነበረ፡፡ እነርሱም ለእርሱ አምልኮትን በአምሳያው ፊት ይፈጽሙ ነበር፡፡ እርሱ በሰው አምሳል ለመላእክት ተገልጦ ይታያቸው ነበር እንጂ በፍጹም እርሱነቱ ያልተገለጠ ማንም በማይቀርበው መለኮታዊ ብርሃን ውስጥ የሚኖረው ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱ ስሙ እውነተኛ ብርሃን የሆነ እኛን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ፡፡ ያም ማለት ሰው ሆነ፤ ለእርሱ አንድ ነገርን ለማድረግ መውጣት መውረድ የሚገባው አይደለም፤ ነገር ግን ሰው መሆኑን እንድንረዳ “ወደ ዓለም ይመጣ ነበር” ተብሎ ተጻፈልን፡፡

 ይህ ከፍጥረታት መፈጠር  አንስቶ ለፍጥረቱ በእርሱነቱ ተገልጦ የማያውቅ አብ ወልድ መንፈስ በተለየ አካሉ በወልድ ሲገለጥ የማይታየው ታየ የማይታወቀው ታወቀ ያልተገለጠው ተገለጠ፡፡ ሥጋ በመልበስ እግዚአብሔር ለእኛ ሙሉ ለሙሉ ተገለጠልን፡፡ እርሱ እግዚአብሔር ነውና እርሱን በእግዚአብሔርነቱ አወቅነው ማለት እግዚአብሔርን አወቅነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ስለጌታችን ሲናገር እርሱ የእግዚአብሔር ምሥጢር ነው ማለቱ፡፡
ረቆ(ረቂቅ ሆኖ) ይኖር የነበረ እግዚአብሔር ለእኛ ተገለጠ ከእኛ ጋር በላ ጠጣ በሰው ቋንቋ ተነጋገረ አሁንም ቢሆን ፍጥረት በማይመረምረው መለኮታዊ  ማንነቱ ውስጥ ይኖራል፡፡ ስለዚህም ነው ወንጌላዊው ማንም ከማይደርስበት ብርሃን ውስጥ ይኖራል ማለቱ ፡፡ እንዲህም ስለሆነ ነው እርሱን አወቅን ማለት እግዚአብሔርን አወቅን ማለት የሆነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ እርሱን አየን ማለት አብን አየን ማለት የሆነው ፤እርሱን አወቅን ማለት መንፈስ ቅዱስን አወቅን ማለት የሆነው፡፡ አብ በእርሱ ሕልው ሆኖ ይኖራል፣ በወልድም መንፈስ ቅዱስን እናውቀዋለን፤(ዮሐ.16፡17)  ምክንያቱም በባሕርይ አንድ ናቸውና በሥልጣንም የተስተካከሉ ናቸውና፡፡


No comments:

Post a Comment