03/04/2006
በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
(በዚህ በፊት በማኅበረ
ቅዱሳን ድኅረ ገጽ የተለቀቀ ጽሑፍ)
ሰይጣን በእባብ አካል
ተሰውሮ ሔዋንን፤ በእርሱዋም አዳምን በማሳት በእነርሱ ላይ ሞት እንዲሠለጥንባቸው ስላደረገ “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና
በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደረጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኮናውን ትነድፋለህ”በማለት የፍቅር አምላክ እግዚአብሔር
ፈረደበት፡፡ “በአንተ” የተባለው ሰይጣን ሲሆን ፣ “በሴቲቱ” የተባለችው
ቅድስት ድንግል ማርያም ናት (ገላ.4፡4) ፣ “በዘርህ” ሲል የዲያብሎስ የግብር ልጆችን ሲሆን(ዮሐ.8፡49)፣ “በዘርዋ” የተባለው ክርስቶስ ነው(ገላ.3፡16)፡፡
ትርጉሙ እንዲህ አንደሆነም ወንጌላዊው ዮሐንስ “ዘንዶው በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የጠበቁትን የኢየሱስም ምስክር
ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ በባሕርም
አሸዋ ላይ ቆመ”አለን፡፡(ራእ.12፡17) እባብ የተባለው ሰይጣን ስለመሆኑም “ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና
ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ”(ራእ.12፡9) ብሎ ጻፈልን፡፡
አዳም በዚህ ፍርድ
ቃል ምክንያት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ምን እንደሆነ ተረዳ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክ በሔዋንና በእርሱ ላይ የፈረደው ፍርድ
እነርሱን ከማዳን አንጻር የርኅራኄ ፍርድ እንደሆነ ፤ እርሱና ሔዋን በክፉ ምርጫቸው ምክንያት ያጎሳቆሉትን ተፈጥሮአቸውን ወደ ቀደሞው
ክብሩ ይመልሰው ዘንድ ንጽሕት ዘር ከሆነች ታናሽ ብላቴና እንደሚወለድና በመስቀሉ ሞት በእነርሱ ላይ የተላለፈውን የሞት ፍርድ እንደሚሽረው፣
አዳምና ሔዋን የተመኙትን የአምላክነት ስፍራ በክርስቶስ በኩል እንደሚያገኙት እንዲሁም በእርሱ የማዳን ሥራ የመለኮቱ ተካፋዮች እንዲሆኑ
አስተዋለ ፡፡ ይህም እውን እንደሚሆንም “አዳም ከእኛ እንደ አንዱ
ሆነ” በሚለው አምላካዊ ቃሉ አረጋገጠ፡፡ ስለዚህም ለመሰናከሉ ምክንያት የሆነችው ሴት ለትንሣኤውም ምክንያት እንደሆነች ተረዳ ፡፡
በዚህም ምክንያት አስቀድሞ ከሥጋዬ ሥጋ ከአጥንቴ አጥንት የተገኘሽ ክፋዬ ነሽ ሲል “ሴት” ብሎ የሰየማትን ሚስቱን “ሔዋን” ብሎ
ስም አወጣላት፡፡ ትርጓሜውም የሕያዋን ሁሉ እናት ማለት ነው፡፡ እንዲያ ባይሆንና አባታችን አዳም ይህንን የእግዚአብሔርን አሳብ
ባይረዳ ኖሮ እንዴት በሰው ዘር ላይ ሞት እንዲሠለጥን ምክንያት ለሆነችው ሚስቱ ሔዋን የሚል ስምን ያወጣላት ነበር? ነገር ግን
በእርሱዋ ሰብእና ውስጥ እርሱንና ወገኖቹን ከሞት ፍርድ ነጻ የሚያወጣቸውንና ወደ ቀደመው ክብራቸው የሚመልሳቸውን ጌታ በሥጋ የምትወልድ፣
የሕያዋን ሁሉ እናት የሆነች ንጽሕት ዘር እንዳለች ከእግዚአብሔር የፍርድ ቃል አስተዋለ፡፡
አዳም ይህን ሲረዳ ክፋዩ ለሆነች ሚስቱ ያለው ፍቅርና አክብሮት ከፊት ይልቅ
ጨመረ፡፡ ከእርሱም በኋላ ለሚነሡ ወገኖቹም ለመዳናቸውና ለመክበራቸው ምክንያት ከሴት ወገን የሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም እንደሆነች
አስተውለው ወንዶች ለእናቶቻቸውና ለእኅቶቻቸው እንዲሁም ለሴት ልጆቻቸው ተገቢውን አክብሮትና ፍቅር እንዲያሳዩ ለማሳሰብ ሲልም ሚስቱን
ሔዋን ብሎ መሰየሙንም መረዳት እንችላለን፡፡ እንዲህም ስለሆነ ነቢዩ ኢያሳይያስ “ዐይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ እነዚህ
ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሟቸዋል”(ኢሳ.60፡4)ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ ቅድስት
ድንግል ማርያም ራሱዋን የጌታ ቤተክርስቲያን በማድረጓ ቤተክርስቲያን በልጁዋ ክቡር ደም ተዋጅታ እንድትመሠረት ምክንያት ሆናለች፡፡
ስለዚህም አባታችን አዳም እንዳደረገው ነቢዩም እንደተናገረው ለእርሱዋ ያለንን ፍቅርና አክብሮት በጾታ ለሚመስሎአት እናቶቻችን፤
እኅቶቻችን፣ እንዲሁም ሴቶች ልጆቻችን በማሳየት እንገልጠዋለን፡፡
ከአዳም በኋላ የተነሡ
ቅዱሳን አበው በአዳምና በሔዋን መተላለፍ ምክንያት በእነርሱ ላይ የሠለጠነባቸው ሞት የሚወገድላቸውና ወደ ገነት የሚገቡት እግዚአብሔር
አምላክ ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለድ እንደሆነ ከአዳም አባታቸው ተምረው ነበር፡፡ ስለዚህም ከክርስቶስ የማዳን ሥራ ተካፋይ
ለመሆን እሾኽና አሜካላ በምታበቅለውና ሰይጣን በሠለጠነባት በዚህች ምድር የመዳን ተስፋቸው የሆነችውን የቅድስት ድንግል ማርያምን
መወለድ በተስፋ እየተጠባበቁ ቅዱስ ጳውሎስ “ማቅ፣ ምንጠፍና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፣ ተቸገሩ፣ መከራ ተቀበሉ፣ ተራቡ፣
ተጠሙም፣ ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ዱር ለዱርና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ”(ዕብ.11፡33-38)እንዳለው ቅዱሳን በጽድቅ ተጉ፡፡
ጌታችንም እንደተስፋ ቃሉ ከንጽሕት ቅድስት እናቱ ተወልዶ በመስቀል ላይ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በመቅረብ ወደ ገነት አፈለሳቸው፡፡
ስለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዳ ጌታችንን መድኀኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እስክትወልድ ድረስ የተስፋ
ቃሉ እንዳልተፈጸመ ለማስዳት ሲል ጨምሮ “እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙም፡፡ ያለ
እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ የምትበልጠውን አስቀድሞ በይኖአልና፡፡” ማለቱ(ዕብ.11፡39-40)
አባቶቻችን ከሐዋርያት
በትውፊት አግኝተው እንደጻፉልን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልክ እንደ ይስሐቅ፣ እንደ ነቢዩ ሳሙኤል እና እንደ መጥምቁ
ዮሐንስ፣ መካን ከነበሩ ወላጆች የተገኘች ናት፡፡ እናቱዋ ሐና በአባቱዋ በኩል ከአሮን ቤት ስትሆን በእናቷ በኩል ከይሁዳ ወገን
ነበረች፡፡ አባቱዋ ኢያቄም ግን ከይሁዳ ወገን ነበር፡፡ እነዚህ ወላጆች በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ ነገር ግን ልክ እንደ
አብርሃምና እንደ ሣራ እስከ እርጅናቸው ድረስ ልጅ አልወለዱም ነበር፡፡ በአይሁድ ዘንድ መካንነት የእርግማን ምልክት ተደርጎ ይወሰድ
ነበርና ኢያቄምና ሐና እግዚአብሔር አምላክ ልጅ በመስጠት ይህን ስድብ ያርቅላቸው ዘንድ በቅድስናና በንጽሕና በመጽናት ምጽዋትንም
በማብዛት በጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ ጸሎታቸውንና ምጽዋታቸውን እግዚአብሔር ስለተቀበለላቸው አምላክን በሥጋ በመውለድ ለዓለም መድኅን
የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምን በእርጅና ዘመናቸው ግንቦት አንድ ቀን ወለዷት፡፡ ማርያም ማለት የእግዚብሔር ስጦታ ማለት ነው፡፡
ሐናም እግዚአብሔር አምላክ ስድቤን ከእኔ አርቆልኛልና ከእግዚአብሔር እንዳገኘዋት ለእግዚአብሔር መልሼ እሰጣታለሁ ብላ የተሳለቸውን
ስለት አሰበች፡፡ ሦስት ዓመት ሲሞላትም ስለቷን ትፈጽም ዘንድ ከኢያቄም ጋር ልጇን ቅድስት ድንግል ማርያም ይዛ ወደ ቤተመቅደስ
አመራች፡፡ በጊዜው ሊቀ ካህናት የነበረው ካህኑ ዘካርያስም ሕዝቡን ሰብስቦ በታላቅ ደስታ ተቀበላቸው፡፡ ነገር ግን ካህኑን ዘካርያስን
የምግብናዋ ነገር አሳስቦት ነበረና ሲጨነቅ ሳለ ነቢዩ ኤልያስን ይመግበው ዘንድ መልአኩን የላከ እግዚአብሔር አምላክ(1ነገሥ.19፡6)
እናቱ የምትሆነውን ቅድስት ድንግል ማርያምን ይመግባት ዘንድ ሊቀ መላእክትን ቅዱስ ፋኑኤልን አዘዘላት፡፡ ካህኑ ዘካርያስም የምግቡዋ
ነገር እንደተያዘለት ሲረዳ በቤተ መቅደስ ውስጥ እንድታድግ አደረጋት፡፡ ይህ ዕለት በሁሉም ኦሬንታልና የሐዋርያት የሥልጣን ተዋረድ(Apostolic
succession) በተቀበሉ የሚታወቅና የሚከበር ክብረ በዓል ሲሆን በአታ ለማርያም ወይም የቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተመቅደስ መግባት በመባል
ይታወቃል፡፡ በዚህም “ልጄ ሆይ ስሚ፣ ጆሮሽንም አዘንቢዪ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፤ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፤ እርሱ ጌታሽ
ነውና፡፡”(መዝ.44፡10) የሚለው ቃል መፈጸሙን እናስተውላለን፡፡
የጌታን መወለድ በተስፋ
ሲጠባበቁ ለነበሩ ቅዱሳን አበው ይህች ቀን እጅግ ታላቅ ዕለት ነበረች፤ ምክንያቱም የመዳናቸው ቀን መቃረቧን የምታበሥር ቀን ነበረችና፡፡ ለእኛም ለክርስቲያኖች ይህች ቀን ታላቅ
የሆነ በረከት ያላት ናት፡፡ ሙሴ የመገናኛ ድንኳኗንና በውስጡ ያሉትን ነዋያተ ቅዱሳት የጥጃና የፍየሎች ደምን ከውኃ ጋር በመቀላቅል
በቀይ የበግ ጠጉርና በሂሶጵ በመንከር ረጭቶ ቀድሶአት ነበር፡፡(ዘጸ.24፡7-8፤ዕብ.9፡18-22) ንጉሥ ሰሎሞንም እርሱ ያሠራውን
ቤተመቅደስ እርሱና ሕዝቡ ባቀረቡት የእንስሳት መሥዋዕት ቀደሶ ነበር፡፡(1ነገሥ.8፡23) እነዚህ ሥርዐታት ግን ክርስቶስ በደሙ
ለሚዋጃት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነበሩ፡፡
በዚህች ቀን ቅድስት እናታችን ራሱዋን የጌታ ቤተ መቅደስ በማድረግ
የብሉዩዋ ቤተመቅደስ ክርስቶስ በደሙ በዋጃት ቤተክርስቲያን ልትተካ መቃረቡዋን ለማብሠር ወደ ቤተ መቅደስ ያመራችበት ቀን ነው፡፡
ጌታችንም ከእርሱዋ የነሳውን ሥጋና ነፍስ በተዋሕዶ የራሱ ቤተመቅደስ በማድረግና እኛንም በጥምቀት የአካሉ ሕዋሳት እንድንሆን በማብቃት
ሥጋችንን የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ስለዚህም እኛ ክርስቲያኖች የቅድስት ድንግል ማርያምን ወደ ቤተመቅደስ
መግባት ባሰብን ቁጥር እግዚአብሔር ቃል ከእርሱዋ በሥጋ በመወለዱ ያገኘነውን ድኅነትና ብዙ ጸጋዎችን እናስባለን፡፡ አሁን እኛ ክርስቲያኖች
በጥምቀት ከእርሱዋ የተወለደውን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለብሰነዋል፤ (ገላ.3፡27) ከእርሱዋ በነሣው ተፈጥሮ በኩል
ሞትን በመስቀሉ ገድሎ ሲያስወግደው፣ እኛም በጥምቀት ከእርሱ ሞት ጋር በመተባበራችን ሞትን ድል የምንነሣበትን ኃይልን ታጥቀናል፡፡
በጥምቀት ያገኘነውን ጸጋ ሠርተንበትና አብዝተነው ብንገኝ ከትንሣኤው ተካፋዮች መሆንን እናገኛለን፡፡ ይህ ሁሉ የተፈጸመልን እግዚአብሔር
ቃል ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለዱ ምክንያት ነው፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም ብሉይን ከአዲስ ያገኛኘች መንፈሳዊት ድልድይ ናት፡፡
በብሉይ ያሉት ቅዱሳን በሐዲስ ኪዳን ካለነው ጋር አንድ ማኅበር የፈጠሩትና ከቅዱሳን መላእክትም ጋር እርቅ የወረደው ከእርሱዋ በነሳው
ሰውነት በኩል ነው፡፡ ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህስ ወዲህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች
እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም”(ኤፌ.2፡19) ብሎ አስተማረ፡፡ ራሷን የጌታ ቤተ መቅደስ በማድረግ እኛንም በልጁዋ በኩል
የመንፈሱ ቤተ መቅደስ እንድንሆን ምክንያት ሆናልናለችና የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተመቅደስ መግባት ለእኛ ክርስቲያኖች
ልዩ ትርጉም አለው፤ ስለዚህም ይህቺን እለት በታላቅ ድምቀት እናከብራታለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ
ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
Amen tebarek !
ReplyDelete