Thursday, April 19, 2012

“…በተቀደሰው ተራራህ ማን ይኖራል?”(በቅዱስ ጀሮም)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
12/08/2004
መግቢያ
ቅዱስ ጀሮም የላቲን አባቶች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ሲሆን የታሪክ ጸሐፊ፤ የቅዱሳት መጻሕፍት ተርጓሚ፤ እና የቤተክርስቲያን ጠበቃዎች ከሚባሉት ውስጥ የሚመደብ ቅዱስ ነው፡፡ ለዛሬ ከእርሱ ሥራዎች ውስጥ የዳዊት መዝሙር 14ን ከሞላ ጎደል የተረጎመበትን ጽሑፍ ተርጉሜ አቅርቤላችኋለሁ፡፡
መዝሙር 14(15)
“የዳዊት መዝሙር”
1.      አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል?
በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?
2.     በቅንነት የሚሄድ፣ ጽድቅንም የሚያደርግ፣
በልቡም እውነትን የሚናገር፡፡
3.     በአንደበቱ የማይሸነግል፣
በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ፣
ዘመዶቹንም የማይሰድብ፡፡
4.    ኃጢአተኛ በፊቱ የተናቀ፣
እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን የሚያከብር፣
ለባልንጀራው የሚምል የማይከዳም፡፡
5.     ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፣
በንጹሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል፡፡
እንዲህ የሚያደርግ ለዘለዓለም አይታወክም፡፡
 ጀሮም ትምህርቱን እንዲህ ይጀምራል፡- ከርእሱ እንደምንመለከተው “የዳዊት መዝሙር” ይላል፡፡ ዳዊት የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡(ይህን አስመልክቶ የሰጠውን ትርጓሜ ወደፊት እጽፈዋለሁ) ከዚህ በተጨማሪ ግን ዘጸአትን ስናነብ እስራኤላውያን በዐሥራ ዐራተኛው ዕለት ከግብጽ ባርነት የተላቀቁበትን ዕለት ቀንዱ ያልከረከረ ጥፍሩ ያላረረ በግ እንዲሠው መታዘዛቸውን እናስታውሳለን፡፡(ዘጸአ.12፡6) በዐሥራ ዐራተኛው ቀን ጨረቃ ሙሉ በሆነችበት ዕለት ምድሪቱን በብርሃኑዋ በምታበራበት ጊዜ መሥዋዕቱን እንዲያቀርቡ እስራኤላውያን ታዘዋል፡፡ በዚህም በሙሉ ቅድስና ሕይወት ተገኝተን ከመሥዋዕቱ ልንቀበል እንዲገባን ያስተምረናል፡፡

ነቢዩ “አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል?ብሎ ይጠይቃል፡፡ እኛ ደግሞ በእግዚአብሔር ድንኳን ውስጥ ማደርን እንናፍቃለን፡፡ አስከትሎም “በተቀደሰውም ተራራ ማን ይኖራል? ብሎ በድጋሚ ይጠይቃል፡፡ ነቢዩ “በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል? ማለቱ ምን ለማለት ፈልጎ እንደሆነ ልብ በሉ፡፡ ይህ ነቢይ አስቀድሞ የተቀደሰውን ተራራ በኋላም ድንኳኑን አላነሣም፡፡
እንደሚታወቀው ድንኳን ቋሚ የሆነ መኖሪያ ቤት አይደለም፡፡ ለድንኳንም መሠረት አይቆፈርለትም፡፡ ነገር ግን ዘላኖች ከአንድ ቦታ ለቅለው በሌላ ቦታ ደግሞ የሚተክሉት ጊዜአዊ መጠለያ ነው፡፡ ስለዚህም ተወዳጆች ሆይ አስቀድመን የድንኳኑንና የተራራውን ምሳሌ እንረዳ፡፡
አስቀድመን እንደተነጋገርነው ለድንኳን መሠረት የለውም ጊዜአዊ መጠለያ ነው፡፡ በድንጋይ የምናንጸውና በጭቃ የምንሠራው ቤት ግን ቋሚ መኖሪያችን ነው፡፡ ለእኔ የድንኳኗ ምሳሌዋ በዚህች ምድር ያታነጸችው ሕንፃ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በዓለም ዙሪያ ለታነፁ አቢያተ ክርስቲያናት ሁሉ ምሳሌአቸው የነበረችው የምስክሩዋ ድንኳን ነች፡፡ እኛ በዚህ ምድር ቋሚ ነዋሪዎች አይደለንም፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ የምንፈልስ ነጋዲያን(ስደተኞች) ነን፡፡ ይህቺ ዓለም የምታልፍ ከሆነ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች ሰማይና ምድር እንደሚያለፉ የተጻፈልን ከሆነ፤ከእነዚህ ጋር በአንድነት እንዴት ይህቺ ሕንፃ ቤተክርስቲያን አታልፍም ልንል እንችላለን? ሕንፃዋ ቤተክርስቲያንም በምስክሩ ድንኳን መመሰሉዋ ለዚህ ነው፡፡ እኛ ሁላችን ወደ ዘለዓለማዊው መኖሪያችን ወደ እግዚአብሔር ተራራ መፍለሻችን አይቀሬ ነው፡፡
የተቀደሰው የእግዚአብሔር ተራራ የተባለው የቱ ነው ታዲያ? በነቢዩ ሕዝቅኤል “… ግፍ በውስጥህ ተሞላ ኃጢአትንም ሠራህ ስለዚህ እንደ ርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ”(ሕዝ.28፡16) የሚል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ስለዚህም በተራራ የተመሰለው መንግሥተ ሰማያት መሆኑን እንረዳለን፡፡ እንግዲህ ድንኳን ከሆነው ማደሪያችን ወደ ተቀደሰው ተራራ የምንፈልስ ስደተኞች ከሆንን ለዚህ እንደተገባቸው ቅዱሳን ሆነን ልንገኝ ይጠበቅብናል፡፡
 ነቢዩ “አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያደራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?  ብሎ ይጠይቃል፡፡ መንፈስ ቅዱስም እንዲህ ብሎ መልስ ይመልስለታል፡፡ “በድንኳኔ የሚያድር በተቀደሰውም ተራራዬ የሚኖር እንዴት ያለ ሰው እንደሆነ ማወቅ ትፈልጋለህን? ይለዋል፡፡ አስከትሎም "የምልህን ለመፈጸም የምትጠነቀቅ ከሆነ በድንኳኔ ታድራለህ በተቀደሰውም ተራራዬ ትኖራለህ ይለዋል፡፡ እናንተም ከእኔ ዘንድ ትርጓሜውን አትፈልጉ እግዚአብሔር ለነቢዩ በመንፈሱ የሰጠውን ምላሽ አድምጡ እንጂ፡፡
መንፈስ ቅዱስ"በቅንነት የሚሄድ ጽድቅንም የሚያደርግ” ይለዋል፡፡ ይህ በመዝሙር 118፡1 ላይ “በመንገዳቸው ንጹሐን የሆኑ በእግዚአብሔር ሕግ የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው” ካለው ጋር  ተመሳሳይ ነው፡፡ ልዩነታቸው በዚህ መዝሙር ላይ “በቅንነት የሚሄድ ማለቱ” ብቻ ነው፡፡ “በቅንነት የሚሄድ” የሚለው ኃይለ ቃል በትእዛዝ ስለተሰጠን ሕግጋት የሚናገር ነው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ መንፈስ ቅዱስ በስተመጨረሻ ላይ ያለነውር የተገኘ አላለም፡፡ ነገር ግን በጽድቅ ጎዳና ላይ ስላለ ሰው እየተናገረ ነው፡፡
አንድ ሰው ምናልባት “እኔ አልሳትኩም፤ ኃጢአትንም አልፈጸምኩም ሊል ይችላል፡፡ ነገር ግን መልካም የትሩፋት ሥራዎችን ካልሠራ(በበጎ አድራጎት ሥራዎች) ካልተጋ ከኃጢአት ተጠብቆ መኖሩ ለእርሱ የሚያመጣለት አንዳች ፋይዳ የለም፡፡ በእርግጥ ቀጣዩ ምንባብ ይህን የሚያጠናክር ነው፤ እንዲህ ይላል፡- “ጽድቅን የሚያደርግ” ፡፡ “ጽድቅን የሚያደርግ” ምን ማለት እንደሆነ ልብ በሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሰውነቱን በንጽሕና የጠበቀ ወይም ጥበብን ገንዘቡ ያደረገ ወይም ትዕግሥተኛ የሆነ አላለንም፡፡ 
በእርግጥ እነዚህ እጅግ በጎ ምግባራት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ለመንፈሳዊው ሕይወታችን መንፈሳዊው ጥበብ ለእኛ ታላቅ እርዳታን ያደርግልናል፡፡ ትዕግሥትም በእኛ ላይ የመጣውን መከራ በጽናት ተቋቁመን ለማለፍ ይረዳናል፡፡ ሰውነታችንንም ከነውር ሁሉ ጠብቀን መገኘታችን ነፍሳችንን ከርኩሰት ሁሉ ይጠብቃታል፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ሁሉ ጽድቅን ማድረግ (በቅን መፍረድ ይልቃል) ጽድቅን ማድረግ የመልካም ሥነ ምግባሮች ሁሉ እናት ናት፡፡ ከመካከላችን አንዱ እንዴት በቅን መፍረድ ከሁሉ መልካም ሥነምግባራት ይልቃል? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሌሎች በጎ ምግባራት ገንዘቡ ላደረጋቸው ሰው ክብርን ያመጡለታል፡፡  በቅን የሚፈርድ ማለትም ጽድቅን የሚያደርግ ሰው ግን ይህ ጸጋው ለእርሱ ክብርንና ደስታን የሚያመጣለት አይደለም፡፡ እኔ ጠቢብ ብሆን ጥበቤ ደስ ታሰኘኛለች፡፡ ጎበዝም ብሆን ትዕግሥቴ መጽናናትን ታመጣልኛለች፡፡ ከነውር ሁሉ የጸዳው ከሆንኩ ደግሞ ንጽሕናዬ በውስጤ መንፈሳዊ ደስታን ትሰጠኛለች፡፡ በተቃራኒው ግን በቅን መፍረድን ገንዘቡ ያደረገ ሰው ለሌሎች ደስታን ቢሰጥ እንጂ ለራሱ ደስታን የሚያገኝ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ደሃ ከወንድሜ ጋር ቢጋጭ ወንድሜም ስልጣኑን ተጠቅሞ ደሃውን ቢበድለውና ቢያጠቃው ለዚህ ደሃ ሰው የኔ ጥበብ ምን ይረባዋል፣ የእኔ ትግዕሥት ምን ያደርግለታል፤ የኔ ንጽሕና በምን ያገለግለዋል፡፡ ነገር ግን እውነትን መሠረት አድርጌ ለወንድሜ ሳላደላ ለደሃው በቅንነት ብፈርድ ደሃው ይጠቀማል፡፡ ቅን ፍርድ ወንድም፣ እናት፣ አባት፣ ቤተሰብ፣ ዘመድ ብሎ ነገር አታውቅም፡፡ ሰውን ከሰው አታበላልጥም ለሁሉ እኩል ትፈርዳለች፡፡ እርሷ አምላኩዋን እግዚአብሔርን የምትመስል ናት፡፡
በዚህም ምክንያት ሌሎችን በጎ ምግባራት ሳይጨምር መንፈስ ቅዱስ “ጽድቅን የሚያደርግ” ብሎ ተናገረ፡፡ በቅን መፍረድን የሚወድድ ሰው በፍትሕ መዛባት ምክንያት ሰዎች ተበድለው ሲያይ ያዝናል፤ በሰዎች ልጆች ስቃይ ደስ አይሰኝም፡፡
ስለቀሩት የመዝሙሩ ምንባቦች ደግሞ ጥቂት እንበል፡፡ መንፈስ ቅዱስ “በልቡ እውነትን የሚናገር” አለን፡፡ ልባቸው በሀሰት የተሞላ በአንደበታቸው ግን እውነትን የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ስላሉ እንዲህ አለ፡፡ ልባቸው ከአንደበታቸው ጋር ፈጽሞ የማይጋጠም ንግግርን የሚናገሩ ሰዎች አሉ፡፡ በመቀጠል “በአንደበቱ የማይሸነግል” አለ፡፡ በልቡ ያሰበውን አንዳች ሳይደብቅ የሚናገር ማለቱ ነው፡፡ በማስከተልም “በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ” አለ፡፡ አንዳንዶች ባልንጀሮች የሚሉአቸው የሥጋ ወንደማቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ዘመዶቻቸውን ነው፡፡ 
ነገር ግን ጌታችን ለአንድ ጸሐፊ በምሳሌ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲሄድ በመንገድ ላይ ወንበዴዎች አግኝተውት በሞትና በሕይወት ስለተጣሉት ሰው እንዲህ ብሎ አስተምሮ ነበር፡፡ ጌታችን እንዲህ አለ በሞትና በሕይወት መካከል በወንበዴዎች ክፉኛ ተደብድቦ በወደቀው ሰው አጠገብ አንድ ካህን አለፈ ምንም ሊያደርግለትም አልፈቀደም፡፡ ሌዋዊውም እንዲሁ እንደካህኑ አደረገ በስተመጨረሻም አንድ ሳምራዊ አገኘው እርሱም ራራለት ቁስሉንም በዘይት አጠበለት፡፡ በአህያውም ጭኖ ሕክምና ወደ የሚያገኝበት ቦታ ወሰደው የሕክምናውንም ወጪ በሙሉ ከፈለለት፡፡ እናም ከእነዚህ ከሦስቱ መልካም ያደረገው የቱ ነው? ብሎ ጌታችን ጠየቀ በዚህን ጊዜ ባልንጀራዬ ማን ነው ያለው ይህ ጸሐፊ ያለ ምንም ማመንታት “መልካም ያደረገለቱ” ብሎ መለሰለት፡፡ ጌታችም አንተም እንዲሁ አድርግ ብሎት ከእርሱ ተለየ፡፡
 እንዲሁ ለእኛም ሰዎች ሁሉ ባልንጀሮቻችን ናቸው፡፡ የትኛውንም ሰው ቢሆን ባልንጀራችን አይደለም በሚል ሰበብ ልንጎዳው አይገባንም፡፡ እንዲህም ከመሰለ ተግባርም እግዚአብሔር ይጠብቀን፡፡ ሁላችንም አንዳችን ለአንዳችን ባልንጀሮች ነን፡፡ ሁላችን የአንድ አዳም ልጆች ነን፡፡
መንፈስ ቅዱስ አስከትሎ “ዘመዱን የማይሰድብ” አለን፡፡ ይህ ታላቅ የሆነ ሥነ ምግባር  ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በዘመዱ ላይ የማያንጎራጉር አላለም፡፡ ነገር ግን ዘመዱ በሆነው የሰው ዘር ላይ ክፉ ቃልን ከአንደበቱ የማያወጣ ማለቱ ነው፡፡ ይህ የመሰለ ሕይወት ያለው ሰው እጅግ የተባረከ ነው፡፡
“ኃጢአተኛ በፊቱ የተናቀ” አለን፡፡ በጻድቅ ሰው ፊት ቄሳርም ይሁን ሀገር ገዢ፤ ጳጳስም ሆነ ካህን ኃጢአትን የሚወድ ሆኖ ከተገኘ የተናቀ ነው፡፡ “እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን የሚያከብር” ሲልም ይህ ሰው አካሄዱን ያለነውር ያደረገ፣ ስልጣኑን ፈርቶ ኃጥኡን ገዢ የማያከብር፤ እግዚአብሔርን በሚፈሩት የሚደስትና ተገቢውን ክብር የሚሰጥ ሰው መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህ ሰው እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ካየ ምንም እንኳ በድህነት የተጎሳቆለ ሆኖ ያገኘው ቢሆንም ያከብረዋል እንጂ አይንቀውም፡፡…. ለባልንጀራው የሚምል የማይከዳም” አለ፡፡ ባልንጀራ የሚለውን ቃል ከላይ እንደሰጠነው ማብራሪያ እንረዳውና ትርጉምን እንወቅ…. ከሰዓታችን የተነሣ እዚህ ላይ ትምህርታችንን እንግታ ቅኖች እንሁን፤ ለሰው ልጆች ሁሉ መልካምን በማድረግ እንትጋ፤ በአራጣም ገንዘባችንን አናበድር፤ እንዲህ ፈጽመን የተገኘን እንደሆነ እግዚአብሔር አምላክ ወደ ተቀደሰው ተራራው ከቅዱሳኖቹ  ጋር መኖሪያችንን ያደርግልናል፡፡            

1 comment:

  1. መንፈስ ቅዱስ አስከትሎ “ዘመዱን የማይሰድብ” አለን፡፡ ይህ ታላቅ የሆነ ሥነ ምግባር ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በዘመዱ ላይ የማያንጎራጉር አላለም፡፡ ነገር ግን ዘመዱ በሆነው የሰው ዘር ላይ ክፉ ቃልን ከአንደበቱ የማያወጣ ማለቱ ነው፡፡ ይህ የመሰለ ሕይወት ያለው ሰው እጅግ የተባረከ ነው፡፡

    ReplyDelete