Sunday, February 26, 2012

አጋፔ (Agape)



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
18/06/2004
(ስብከት ወተግሣጽ ከሚለው መጽሐፌ ተወስዶ የተብራራ)
ቃሉ ግሪክ ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም ክርስቲያናዊ ፍቅር ``Charity`` (1ኛ ቆሮ 131-8) ማለት ሲሆን ይህ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ የተገለጠ ፍቅር ነው፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ ቅዱስ ሂፖሊተስ አጋፔን ከቅዱስ ቁርባን ጋር አገናኝተው ያስተምሩታል፤ መጽሐፉም ይህንን ይደግፋል፡፡ ይሁዳ ቁ.12 ላይ “በፍቅር ግብዣችሁ”ሲል ክርስቲያናዊ ፍቅርንና ቅዱስ ቁርባኑን በአንድነት አጣምሮ ሲገልጠው ነው፡፡ “ፍቅር” ያለው አጋፔ የተባለው ክርስቲያናዊ ፍቅርን ሲሆን “ግብዣችሁ” የተባለው ቅዱስ ቁርባኑ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በእሑድ ወይም በስምንተኛው ቀን ይመሰላል፡፡ የክርስቲያን እሑድ እንደ ስምንተኛው ቀን ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም እሑድ የቀናት መጀመሪያ ናት፡፡ ክርስቲያን ደግሞ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረትና በኩር ስለሚሆን ብኩርና ያገኘባት ያች ቀን ለእርሱ እንደ እሑድ ቀን ናት፡፡
ይህ ክርስቲያን በጥምቀቱ ከዚህ ዓለም እያለ በላይ በሰማያት ከትመው ከሚኖሩት ከቅዱሳን ነፍሳትና ቅዱሳን መላእክት ጋር መኖሪያውን ያደርጋል፡፡ እነርሱ ከምድራዊ ሥርዐት ውጪ እንደሆኑና ምድራዊው የሆነው የቀን ቀመር እንደማያገለግላቸው እንዲሁ ለዚህም ክርስቲያንም በአዲስ ተፈጥሮው ከእነርሱ ጋር ማኅበርተኛ ሆኖአልና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል፡፡ ወደ ዕረፍቱ የገባ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና፡፡”(ዕብ.4፡9-10)እንዳለው ለእርሱም የቀን ቀመርና አቆጣጠር አያስፈልጉትም፡፡ ይህን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያብራራው “ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፤ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም በደስታ ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፍት መላእክት ፣ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኩራት ማኅበር የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር ፤ፍጹማንም  ወደ ሆኑት  ወደ ጻድቃን መንፈሶች፤ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገረው ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል” ብሎናል፡፡ (ዕብ.11፡22-24)



ህች ሰንበት የተመሰለችባት የዕረፍት ሥፍራ ምን እንደምትመስልም ወንጌላዊው ዮሐንስ “ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለሆነ ፀሐይና ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር፡፡ አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፤ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርሰዋ ያመጣሉ በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፤ የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርሰዋ ያመጣሉ፡፡ ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኩሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርሰዋ ከቶ አይገባም”(ራእ.21፡23-27)ብሎ ያብራራታል፡፡ የዚህች ሥፍራ ቋንቋ በመስቀሉ ለእኛ የተገለጠልን የክርስቶስ ፍቅር ወይም አጋፔ ነው፡፡
እኛም ክርስቲያኖች በዚህ ሥፍራ ከትመው ከሚኖሩት ጋር ነዋሪዎች ስለምንሆን ቅዱስ ጳውሎስ “እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀን ልጆች ናችሁ” አለን፡፡(1ተሰሎ.5፡4) ያም ማለት የፍቅር ልጆች ናችሁ ሲለን ነው፡፡ እኛ ለፍጥረቱ የምናሳየው ፍቅር አፍቃሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ለእኛ የገለጠልንን ፍቅር ነው፡፡ እንዲህ ያደረግን እንደሆነ በሰማያት ያሉትን ቅዱሳንን መሰልናቸው ማለት ነው፡፡ 
ይህ ሐዋርያ “እርሱ … ሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቶአልና በሕይወት መኖርን ግን ለእግዚአብሔር ይኖራል፡፡ እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደሞታችሁ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ”(ሮሜ.3፡20)ብሎ እንዳስተማረው በዚያች በሰማያዊቱ ርስታችን እየኖርን እንደሆነ አያሰብን በቅድስና መመላለስ እንዲገባን መከረን፡፡ ሙሉ ለሙሉ የምንወርሳት ግን በምጽአት ነው፡፡ በዚህ ምድር በቅድስና ከተመላለስን ደግሞ በዚህ ምድር ሆነን በእርሱዋ ውስጥ መኖር እንጀምራለን፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር ሕያዋን ሆነው እንደሚኖሩት፣ ኖሮውም እንዳለፉት ክርስቲያኖች እርሱን አፍቃሪያችንን መስለን ለፍጥረት ፍቅርን በመመገብ፣ ለዚህ ዓለም ጠብና ክርክር የሞትን፤ ለፍቅር ግን ሕያዋን የሆንን ልንሆን ይገባናል፡፡
 እግዚአብሔር አምላክ እርሱን መስለን ከእኛ የሚጠብቀውን ይህን ክርስቲያናዊ ፍቅር ወይም አጋፔን ለፍጥረት ሁሉ ለመመገብ የፍቅርን ጥሩር ለብሰን የፍቅርን ትጥቅ ታጥቀን ፍቅርን ተጫምተን እንሰለፍ፤ ያለዚህ ጠላታችንን ዲያብሎስን ድል ልንነሣውና የጠፉትን ልናድን ፈጽሞ አይቻለንም !!! እኛን በፍቅሩ የማረከንን ክርስቶስን እንምሰለው፤ ፍቅሩን ለብሰን ምርኮን ለእርሱና ለአባቱ እናምጣ፤ ለዚህ ታላቅ ሕይወት እንዲያበቃንም እርሱን ማወቅን ያብዛልን ለዘለዓለሙ አሜን!!!      


1 comment:

  1. Tewodros N.
    Memhir, Kale Hiwot Yasemalin!!!

    ReplyDelete