Monday, December 18, 2017

"እንኋት ክርስትና" መጽሐፌ ለኦን ላይን ግዢ በአምዞን ላይ ቀረበች


እነሆ የማኅበረ ቅዱሳን ኤዲቶሪያል ቦርድ በመጽሐፏ ላይ የሰጠውን አስተያየት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ታርማና ተስተካክላ የተዘጋጀች እንኋት ክርስትና መጽሐፌ በአማዞን እንዲህ ሆና ቀርባለች። በተለይ በብሎጌ ላይ ጽሑፎቼን የምትከታተሉ በአሜሪካ፥  በአውሮፓ   ፥ በመካከለኛው ምሥራቅ፥ በሩቅ ምሥራቅ ያላችሁ ወንድሞቼና እኅቶቼ ይህችን መጽሐፌን አሁን ገዝታችሁ በእጃችሁ ማስገባት እንደምትችሉ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። በዚህ ሥራ የተራዳኝን በተለይ መራዊ በጽሐን እንዲሁም የመጽሐፉን ሽፋን እንደገና አርሞ በመሥራት የረዳኝ ወንድሜ አንዷለምን በድንግል ስም ሳላመሰግን አላልፍም።

ከምዕራፍ አንድ ላይ የተቀነጨቡ

 ምሥጢረ ጥምቀትና ምሥጢረ ቁርባንን አስመልክቶ በሶርያ ቅዱሳን አባቶች በጥቂቱ


እነዚህ የሶርያ ቅዱሳን አባቶች ይህን ፅንሰ አሳብ በማዳበር ብዙ የጻፉ ሲሆኑ ባለራዕይው ዮሴፍ የተባለው ቅዱስ አንድ ክርስቲያን በውስጡ ላደረው መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሲታዘዝ በሰውነቱ የሚከሰቱ ለውጦችን ደረጃ በደረጃ ጽፎልን እናገኛለን ፡፡

……..“አንድ ክርስቲያን በሰውነቱ ውስጥ ያደረው መንፈስ ቅዱስ ሥራ መጀመሩን የሚረዳው  በልቡ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር እንደ እሳት መቀጣጠል ሲጀምር ነው፡፡ ይህ ክርስቲያን እግዚአብሔር ከፍቅሩ የተነሣ ዓለማትን እንደ ፈጠረ ወደ ማስተዋል ይመጣል፡፡ ከዚህም ስለእግዚአብሔር ፍቅር ሲባል ለእግዚአብሔር መለየትና የትህርምት ሕይወትን ወደ መምረጥ ይመጣል፡፡ እነዚህ ሁለቱ የመልካም ሥነምግባራት እናቶች ናቸው፡፡ ወንድሜ ሆይ ሁለተኛው መንፈስ ቅዱስ በአንተ ውስጥ ሥራ መሥራቱን የምትገነዘበው እውነተኛ የሆነው ትሕትና በአንተ ሲወለድ ነው፡፡ እንዲህ ስልህ ለታይታይ በሥጋ የሚገለጠውን ትሕትና ማለቴ ግን አይደለም ፡፡ በእኛ ባደረው መንፈስ ቅዱስ ድንቅ የሆነ ሥራ እየተፈጸመ ነገር ግን ራሳችንን እንደትቢያና አመድ የተናቅን አድርገን የምንቆጥርና ከሰው ተርታ የማንመደብ አድርገን  የምንመለከት ከሆነ በእርግጥ እውነተኛይቱትሕትና በእኛ ውስጥ ተወልዳለች ፡፡ (መዝ.፳፩፥፮) ይህ ትሕትና ራስን በእግዚአብሔር ፊት በመመልከት የሚወለድ ትሕትና ነው፡፡