Saturday, September 15, 2012

ክርስትና ማለት እነኋት፡-


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/01/2005
ክርስትና በመንፈስ ቅዱስ እገዛ የሚረዱዋት እምነት ናት፡፡ ብዙዎች ግን በአእምሮ ጠባያቸው ተደግፈው ክርስትናን ከተፈጥሮአዊ ሥርዐት ጋር አቆራኝተው ለመረዳት ሲሞክሩ ከክርስትና ጽንሰ ሐሳብ ሳቱ፡፡ ነገር ግን ክርስትናን ሊረዳት የሚፈለግ ካለ እነኋት፡-  እግዚአብሔር በዘመን ፍጻሜ ያደርግ ዘንድ ያለው አሳቡ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ስለሆነ(ኤፌ.110)ሁሉን ወደ ራሱ ሊያቀርብ ከዚያም ሲያልፍ ሊያዋሕድ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት እናታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሱዋ ነፍስ በመንሳት ሰው ሆነ፡፡ በመስቀሉ በፈጸመው የማዳን ሥራ ሁሉንም ወደ እርሱ አቀረባቸው፡፡(ዮሐ.12፡32)
ስለሆነም በእርሱ ያመንን እኛ ክርስቲያኖች በጥምቀት ከሞቱ ጋር በመተባበር በእምነትም ከትንሣኤው በመካፈል አሮጌውን ሰው ቀብረን አዲሱን ሰው ለብሰን ተነሥተናል፡፡ ስለዚህም እኛ ክርስቲያኖች ልክ እንደ ጌታችን ለዚህ ዓለም የሞትን ስንሆን በትንሣኤው ደግሞ ሕያዋን ሆነን ከቅዱሳን መላእክትና ከቅዱሳን ነፍሳት ጋር አንድ ቤተሰብ ሆነን እየኖርን እንገኛለን፡፡ ይህን በፍጥረታዊው አእምሮ ጠባይ ለመረዳት እጅግ የሚከብድ ነው፡፡ ይህን እምነት አለኝ የሚልና በጥምቀት ከክርስቶስ ሞት ጋር የተባበረ ክርስቲያን ብቻ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠው መረዳት የሚገነዘበው እውነት ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን “እኔ ግንድ ነኝ እናንተ ቅርንጫፎች ናችሁ” አለን፡፡ በዚህ መልክ ከእርሱ ጋር ካልተባበርን በቀር ስለሰማያዊቱ ዓለም ምንም ዐይነት እውቀት አይኖረንም፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኒቆዲሞስን "ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለድክ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ልታይ አትችልም አለው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ያለእርሱ በጎ መሥራትም መዳንም አይቻለንም፡፡(ዮሐ.155-6)