Tuesday, May 2, 2017

የሕይወታችን ሁለቱ ጫፎች


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
25/08/2009

በሕይወታችን ጫፍና ጫፍ ያሉ ጊዜአትንና ተፈጥሮአዊ ባሕርያቸውን ሳስባቸው ግርም ድንቅ ይለኛል፡፡ መመሳሰላቸውንም ሳስብ ደግሞ ይበልጥ እደነቃለሁ፡፡ እነርሱም ሕፃንነትና አረጋዊነት ናቸው፡፡ ሁለቱም ከሌላ አካል አካላዊ ድጋፍን የሚሹ ናቸው፡፡ የሁለቱም ፆታ አገልግሎት አይሰጥም፡፡ አንዱ በተፈጥሮ ስላልተዘጋጀ ሌላኛው ግን ተፈጥሮ ራሷ ከአገልግሎት ስላወጣችው ነው፡፡ እናም ሁለቱም በመላእክት ሥርዓት የሚኖሩ ናቸው፡፡ ሁለቱም የእኛ ፈቃድ ሳይጠየቅ በአምላክ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ ነገር ግን አንዱ ወደዚህ ዓለም የሚያስገባ በር ሲሆን ሌላኛው ወደማታልፈው ዓለም የሚያሸጋግር መውጫ  ነው፡፡ ጎዳናቸው ግን አንድ ነው፡፡ አንተ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ እንዲል ከምድር አፈር ከተበጀ አካል ተወልደን ወደ ቀደምት የአያታችን ማኅጸን ወደ ሆነች ምድር እንገባለን፡፡ ከእርሷም በትንሣኤ ተወልደን ለፍርድ በአምላክ ፊት እንቆማለን፡፡ በሥጋ ከወላጆቻችን ተወልደን በየሰከንዷ በሞት ጎዳና እንጓዛለን፡፡ አንዱ ይቀበላል ሌላኛው ይሸኛል፡፡ አንዱ በባሕርይው ያልተዳደፈ ንጹሕ ሲሆን ሌላኛው ግን ንጽሕናውና ቅድስናው እንደ ግብሩ ይወሰናል፡፡ ዕድሜችንን ሙሉ መልካምን በመሥራት ካሳለፍን በንጽሕናና በክብር ከሕፃንነት እንበልጣለን፡፡ አንዱ ለአዲስ ሕይወት የተዘጋጀ ሲሆን ብዙ ፈተናዎች ከፊቱ ይጠብቁታል፡፡ ሌላኛው ግን በዚህ ዓለም መኖርን አስረጅቷት የሰማያዊውን ሕይወት ጣዕም ማጣጣም የሚጀምርባት ሲሆን የኖረባትም ምድር እርሱን ከአገልግሎት ጡረታ የምታወጣበት ዕድሜ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶ ለእርጅና ከበቃን  የሞትን ጣዕም በእርጅናችን ማጣጣም እንጀምራለን፡፡ ሞት በአካላችን ሥራውን መሥራት ስለሚጀምር ጉልበታችን ይከዳናል፤ ዓይናችን ይፈዛል፤ ጆሮችን ይደነግዛል፤ አካላችን ይቀዘቅዛል፤ ጠጉራችን ይሸብታል ወይም ይመለጣል፤ ቆዳችን ከአጥንታችን ጋር ይጣጋል፤ ወዛችን ይረግፋል፤ መዓዛችን ይለወጣል፡፡  ያኔ መልካምን ሠርተን እንደሆነ አምላክ ቶሎ ወደ እርሱ እንዲወስደን እንለምነዋለን፡፡ ካልሆነ ግን በነፍስም በሥጋም ስቃያችን ይጨምራል፡፡ ወገኖቼ በእርጅና ሲኦልን በሚመስል ሕይወት ውስጥ ከመኖር ይጠብቀን፡፡