Tuesday, May 2, 2017

የሕይወታችን ሁለቱ ጫፎች


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
25/08/2009

በሕይወታችን ጫፍና ጫፍ ያሉ ጊዜአትንና ተፈጥሮአዊ ባሕርያቸውን ሳስባቸው ግርም ድንቅ ይለኛል፡፡ መመሳሰላቸውንም ሳስብ ደግሞ ይበልጥ እደነቃለሁ፡፡ እነርሱም ሕፃንነትና አረጋዊነት ናቸው፡፡ ሁለቱም ከሌላ አካል አካላዊ ድጋፍን የሚሹ ናቸው፡፡ የሁለቱም ፆታ አገልግሎት አይሰጥም፡፡ አንዱ በተፈጥሮ ስላልተዘጋጀ ሌላኛው ግን ተፈጥሮ ራሷ ከአገልግሎት ስላወጣችው ነው፡፡ እናም ሁለቱም በመላእክት ሥርዓት የሚኖሩ ናቸው፡፡ ሁለቱም የእኛ ፈቃድ ሳይጠየቅ በአምላክ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ ነገር ግን አንዱ ወደዚህ ዓለም የሚያስገባ በር ሲሆን ሌላኛው ወደማታልፈው ዓለም የሚያሸጋግር መውጫ  ነው፡፡ ጎዳናቸው ግን አንድ ነው፡፡ አንተ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ እንዲል ከምድር አፈር ከተበጀ አካል ተወልደን ወደ ቀደምት የአያታችን ማኅጸን ወደ ሆነች ምድር እንገባለን፡፡ ከእርሷም በትንሣኤ ተወልደን ለፍርድ በአምላክ ፊት እንቆማለን፡፡ በሥጋ ከወላጆቻችን ተወልደን በየሰከንዷ በሞት ጎዳና እንጓዛለን፡፡ አንዱ ይቀበላል ሌላኛው ይሸኛል፡፡ አንዱ በባሕርይው ያልተዳደፈ ንጹሕ ሲሆን ሌላኛው ግን ንጽሕናውና ቅድስናው እንደ ግብሩ ይወሰናል፡፡ ዕድሜችንን ሙሉ መልካምን በመሥራት ካሳለፍን በንጽሕናና በክብር ከሕፃንነት እንበልጣለን፡፡ አንዱ ለአዲስ ሕይወት የተዘጋጀ ሲሆን ብዙ ፈተናዎች ከፊቱ ይጠብቁታል፡፡ ሌላኛው ግን በዚህ ዓለም መኖርን አስረጅቷት የሰማያዊውን ሕይወት ጣዕም ማጣጣም የሚጀምርባት ሲሆን የኖረባትም ምድር እርሱን ከአገልግሎት ጡረታ የምታወጣበት ዕድሜ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶ ለእርጅና ከበቃን  የሞትን ጣዕም በእርጅናችን ማጣጣም እንጀምራለን፡፡ ሞት በአካላችን ሥራውን መሥራት ስለሚጀምር ጉልበታችን ይከዳናል፤ ዓይናችን ይፈዛል፤ ጆሮችን ይደነግዛል፤ አካላችን ይቀዘቅዛል፤ ጠጉራችን ይሸብታል ወይም ይመለጣል፤ ቆዳችን ከአጥንታችን ጋር ይጣጋል፤ ወዛችን ይረግፋል፤ መዓዛችን ይለወጣል፡፡  ያኔ መልካምን ሠርተን እንደሆነ አምላክ ቶሎ ወደ እርሱ እንዲወስደን እንለምነዋለን፡፡ ካልሆነ ግን በነፍስም በሥጋም ስቃያችን ይጨምራል፡፡ ወገኖቼ በእርጅና ሲኦልን በሚመስል ሕይወት ውስጥ ከመኖር ይጠብቀን፡፡  
ሰው በዚህች ምድር ሺህም ዓመት ይኑር ሁለት ሺህ መቼም ቢሆን ከሞት አይቀርም፡፡ የሚያሳዝነው ግን ንጹሕ የሆነውን ባሕርይ ገንዘቡ አድርጎ ወደዚህ ዓለም የመጣው ሰው በኃጢአት አድፎና ቆሽሾ ምድሪቱንም በኃጢአቱ አጎስቁሏት ያለፈ እንደሆነ ነው፡፡ ለዚህ ሰው ባልተፈጠረ ይሻለው ነበር፡፡ ወይም ጭንጋፍ ሆኖ ቢቀር በተሻለው ነበር፡፡ ይህ በመጀመሪያ ደረጃ ወደ እርጅና በመጣ ጊዜ ሥጋው ስለምታርፍ ነፍሱ በሠራችው ሥራ በጸጸት ተቃጠላለች፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከክፋት ውጪ መልካምን ስለማታውቃት መልካምን መሥራት ብትፈልግም ይሳናታል፤ በሦስተኛ ደረጃ ሰለ እግዚአብሔር የምታውቀው ነገር የለምና ለንስሐ መብቃት ሳትችል እንዲሁ ታልፋለች፡፡ በዐራተኛ ደረጃ ደግሞ የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሷ ላይ ስለሆነ ፈርታና ተንቀጥቅጣ ከእርሱ ስትሸሽ ትኖራለች፡፡ ወደ እርሷ የተላከው መልአክ በግድ ከሥጋዋ መንጭቆ በመውሰድ አስቀድሞ ወደ ሲኦል ቀጥሎም ወደ ገሃነም ይጥሎአታል፡፡ ወዮ አምላካችን እንዲህ እንዳይሆንብን በምድር ባቆየኸን እድሜ ሁሉ አንተን በመፍራትና በማሰብ በመንቀጥቀጥ በበጎ ሥራ ጸንተን እንድንኖር አብቃን፡፡ ይህ እጅግ የሚያስፈራ ነውና፡፡
ግሩም የሆነው ነገር ደግሞ ነፍስ በሁለቱም የሕይወት ጫፎች ከሥጋ ፈቃድ ነጻ መሆኗ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን  ሐዋርያቱን “ሕፃናትን ተዉአቸው፥ ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉ ናትና” ሲላቸው በሌላ ሥፍራም ሕፃንን በመካከላቸው አቁሞ “ማንም ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና” ብሎአቸው ነበር፡፡ እድሜ ለንስሐ የሚሰጥ አምላክ በእርጅናችን ነፍስ ከሥጋ አርነት እንድትወጣ ያደርጋታል፡፡ በዚያ ጊዜ በሰከነ ሕሊና ስለምንሆን ምርቱን ከገለባው ለይተን እናውቃለን፡፡ እውነትን እንዳስሳታለን፣ እናውቃታለን በማወቃችንም እንደነግጣለን፡፡ ሳንጠቀምባትም እንዳናልፍ እንሰጋለን ፈጥነንም እርሷን ወደ መጠቀም እንመጣለን፡፡  በቁጭትም ምነው ድሮ አውቄሽ ብሆን ኖሮ እንዲያ ሳልባክን እኖርብሽ ነበር እንላታለን፡፡ ብቻ ወገኖቼ በአእምሮ ሽማግሌዎች እንጂ ጁጁዎች እንዳንሆን እንጸልይ፡፡ እግዚብአብሔር በሰጠን የእድሜ ዘመናችን መልካምን በመሥራትና እግዚአብሔርን በማወቅ የተመላለስን ከሆነ በእርጅናችን ሕሊናችን ይበልጥ ብሩህ ስለምትሆን በአካል ብናረጅም በአእምሮ ግን ወጣቶች ነን፡፡ ከዘመኑ ጋር አብረን መጓዝ ትውልድን መቅደምና መምራት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ዕድሜ ዘመናችንን ሙሉ ክፋትን ስንፈጽምና እግዚአብሔርን ከማወቅ ርቀን የኖርን ከሆነ መልካሙን ነገር ስለማናውቅ በሥጋም የምንፈጸማቸው ዓለማዊ ግብሮች በእርጅና ምክንያት ስለሚጠፉ ያኔ ጅጁዎች እንሆናለን ፡፡ ልክ ራሱን እንደማያውቅ ሕፃን የምንሠራውን አናውቅም፡፡ እንደታወርንም ወደ አምላካችን እንጠራለን ያኔ እንደ ነዌ ዓይናችን ቢገለጥ ምን ይረባናል ወዳጆቼ? እናም ወዳጆቼ እግዚአብሔር ለመልካም ሽምግልና ያብቃቸሁ ማለት ታላቅ ምርቃት እንደሆነ ልብ በሉ፡፡ ጅጁም ከመሆን ይሰውራችሁ የአካልም የነፍስም ጥፋት ነውና፡፡ ለዚህስ አሜን ይባላል አሜን! እንዲህ ሆኖ የቁም ሞት መሞት ክፉ ደዌ ነውና፡፡
ቢሆንም ግን ለእኛ ያለው የአምላክ ፈቃድ በመልካም ሽምግልና በዚህ ዓለም መውጫ በር በኩል ወደ እርሱ እንድንሄድ ነው፡፡ እግዚአብሔር በሰጠን ዕድሜ ለክፋት ነገር ሕፃናት ለበጎ ነገር ሽማግሌዎች ሆነን ሕይወታችንን በማስተዋል በአምላክ ፈቃድ የመራናት እንደሆነ ከአምላክ በሚሰጠን ለሌሎች በሚተርፈው ጸጋችን ለመጪው ትውልድ አርአያ ከመሆን ባለፈ ለትውልዱ ማረፊያ እንሆናለን፡፡ ብዙዎች ቅዱሳን በዚህ ጎዳና ተጉዘው ለዚህ ክብር በቁ፡፡ በአዳም አባታችን ቅድስና ምክንያት ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ እኛን ለማዳን በሕፃን ግብር ከድንግል ተወልዶ አዳነን፡፡ የሴት ወገን የሆነው ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረጉ ዘወትር ሲታወስ ይኖራል ሕይወቱም አስተማሪ ነው ፡፡ እርሱም አካሄዱን ከአምላኩ ጋር በማድረጉ እግዚአብሔር ወሰደው፡፡ እርሱ ክርስቶስን በሕይወታቸው ደስ ያሰኙት በትንሣኤ ዘጉባኤ ወደ ጌታችን እንዲነጠቁ ምልክት ሆናቸው፡፡ አምላካችን ቅድስናን የሚወድ አምላክ እንደሆነ ላለፈው፣ ለአሁኑና ለሚመጣው ዘመን ሲሰብክ ኖረ ይኖራልም፡፡ በእርሱ ዘመን ላሉት ተስፋ ትንሣኤ እንዳለ ሲያበስራቸው በእኛም ዘመን ላሉትም ለሥጋ ሳይሞቱ ሕይወት እስከ ምጽአት መኖር እንዳለ አሳያቸው፡፡ ይህ አባት ስለ መጪው ዘመንም ጽፎልናል፡፡ እርሱ ከትንሣኤ ዘጉባኤ ቀድሞ የክብር ትንሣኤ የሚፈጸምለትም አባት ነው፡፡

እንደ ሄኖክ አካሄዱን ከአምላኩ ጋር ያደረገ ኖህም አለ፡፡ በእርሱም ዓለም በጥፋት ውኃ ዳግም እንዳትጠፋ ሆነች፡፡ ለጻድቁም ለኃጥኡም ጸሐይን የሚያወጣ ዝናብን የሚሰጥ አምላክ ከኖህ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አስቦ ምድሪቱን በጥቁር ደመና በከደናት ጊዜ ሁሉ የቀስተ ደመና ምልክትን በሰማይ ላይ ያኖራል፡፡ በዚህም በአካለ ሥጋ ከእኛ ዘንድ ያልሆነው ኖህ ምን ጊዜም ይታወሳል፡፡ በተግባርም በእርሱ ቅድስና በጥፋት ውኃ  ዳግም እንዳንጠፋ ሆነናል፡፡ እንዲሁም ሴም፣ ያፌት፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ ፣ሙሴ፣ ዳዊት፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ፣ ካህኑ ዘካርያስ፣ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ሰባ ሁለቱ አርድእት፣ በወርቃማው የቤተ ክርስቲያን ዘመን የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ቅዱሳን ሁሉ በመልካም እርግና ቢያልፉም ረድኤታቸው አሁንም እያገለገለን ይገኛል፡፡ በሥጋ ቢሞቱም በመንፈስ ከእኛ ጋር አንድ ጉባኤ ናቸው፡፡  ይህን በክርስቶስ አገኘነው፡፡ እናም ወዳጆቼ የሚበልጠውን ምክር ልንገራችሁ ሰውን ሁሉ አክብሩ በእርሱ ላይ አንዳች ስልጣን የላችሁምና በምንም ግብር ውስጥ ቢገኝ እንደ ሥራው የሚከፍለው እንዳለ አስባችሁ ስለእርሱ ጸልዩለት እንጂ አትፍረዱበት፡፡ በቃሉ እንጂ በገዛ ማስተዋላችሁ አትደገፉ፤ ቃሉ ስለሚል አድርጉ እንጂ በራሳችሁ ወስናችሁ አታድርጉ፤ ሕፃናት በመልካም ሰብእና ተቀርጸው እንዲያድጉ ትጉ፤ በምንም ሕይወት ውስጥ ይኑሩ አረጋውያንን አክብሩ እነርሱ በእግዚአብሔር ቦታ ናቸውና፡፡ አምላክ ፍጻሜአችንን ያሳምርልን ወዳጆቼ ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነውና፡፡ 

No comments:

Post a Comment