Saturday, May 20, 2017

ምጽዋትና ጥቅሟ በሊቃውንት አባቶቻችን

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
12/09/2009Oዓ.ም

እባካችሁ ከዚህ ጽሑፍ የታዘባችሁትን ጻፉልንኝ

(ከፍትሐ ነገሥት ላይ የተወሰደ)

ምጽዋትስ ከርኅራኄ ወገን ነው፡፡ ይኸውም ሰው በገንዘቡ ምጽዋትን ለሚሹት ሰዎች የሚያደርገው ርኅራኄ ነው፡፡ ከእነርሱ ዘንድ ትርፍ ሳይሻ ጌታችን “ገንዘባችሁን ሽጣችሁ ለድሆች ምጽዋት ስጡ” ብሎ ስላዘዘ ነው “የማይጠፋ ኮረጆ አድርጉ የማይጠፋ የማያልፍ ሰማያዊ ድልብ አከማቹ”(ሉቃ.12፡23) እንዲሁም ዳግመኛም ጌታችን ምጽዋትን ስጡ ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋል አለ፡፡
ሰው በምጽዋት በሚቻለው መጠን ፈጣሪውን ይመስለዋል፡፡ ምጽዋትና መራራት ከአምላክ የተገኘ ባሕርይ ነውና፡፡ ጌታችንም “እንደ ሰማያዊ አባታችሁ የምትራሩ ሁኑ አለ”(ማቴ.5፡48) ምጽዋትሰ አምላካዊት ብድር ናት፡፡ ይህችውም የታመነችና የምትረባ አምላካዊት ንግድ ናት፡፡ ይህችውም ዳግመኛ ወዶ እስኪወስዳት ድረስ ብልህ ሰው ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያኖራት አደራ ናት፡፡ ይህችውም ዳግመኛ በነባቢት መቅደስ ዘንድ ተቀባይነት ያላት ቁርባን ናት፡፡ እግዚአብሔርም ስም አጠራሩ ከፍ ከፍ ይበልና መሥዋዕትን ያይደለ ምጽዋትን እሻለሁ” አለ”(ሆሴዕ.6፡6፤ማቴ.9፡13) ዳግመኛም ከእርሱዋ ጋር ጾም ተቀባይነት ያለው ይሆናል፡፡ ነቢዩ እንደተናገረ(ኢሳ.58፡6-7)ጸሎትን ከርሷ ጋር ይቀበላል፤ በቆርነሌዎስ እንደተነገረ፡፡ ያለርሷ ድንግልናም አትጠቅምም በአምስቱ ሰነፎች ደናግል እንደ ተጻፈ”(ማቴ.25፡11-12)

በምጽዋት ምክንያት ትእዛዞችና ሕጎችም የአምላክ ነገር በሚናገሩ መጻሕፍት እጅግ የተነገሩ ናቸው፤ ስለርሷም ጌታችን “ለለመነህ ስጠው አለ(ማቴ.5፡42) ዳግመኛም የሚራሩ ብፁዓን ናቸው አለ ለእነርሱም ይራራላቸዋልና፡፡”(ማቴ.5፡7) ለሚራሩ ሰዎች ዓለም ሳይፈጠር ወደ ተዘጋጀላችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ግቡ ማለቱ፥ ሐዋርያው ጳውሎስም ለድሆች ምጽዋትን መስጠትን አትዘንጉ ምሰሏቸውም ማለቱ ይህን በመሰለ መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደሰ ያሰኘዋልና ነው”(ዕብ.13፡17)
የምጽዋት ጥቅሟ በብዙ ወገን ነው፡፡ ከርሷም አንዷ ሁሉም በእያንዳንዱ እንደ ችሎታው መጠን ምጽዋትን ይሰጡ ዘንድ ለባለጸገጎቹና ለድሆቹም ትገባቸዋለች፡፡ ዋጋዋም እንደ ሰጭዋ ትጋት መጠን ነው፤ በብዙም ቢሆን በጥቂቱም ቢሆን፡፡ ለባለጸጎችስ ጌታችን በብዙ ያስጠበቁትን ሰው በብዙ ይመረምሩታል”(ሉቃ.12፡48) ብሎ እንደተናገረው ነው፡፡
ብዙ ለወደደኝም ብዙ ይሠይለታል ማለቱ ስጡ ሰፍረው መልተው አትርፈውም ይሰጧችኋል ማለቱ ነው፤ ይልቁንም በሥራችሁ በሰፈራችሁበት መስፈሪያ ይሰፍሩላችኋልና (ሉቃ.7፡47፤ማር.4፡24)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ከዚህ የጌታን ቃል ተከተለ “በጥቂቱ የዘራ በጥቂቱ ያጭዳል በብዙ የዘራ በብዙ ይሰበስባል ሰው ሁሉ በልቡ የሚያሰበውን ምያድርግ" አለ። (2ቆሮ.9፡6)
የዚህ ዓለም ባለጸጎች በልባቸው እንዳይታበዩ እዘዛቸው፥ በመስጠት በመታዘዝ ደስተኞች ይሆኑ ዘንድ፥ ይመጣ ዘንድ ላለው ክብር ለሰውነታችው በጎ መሠረት ይመሠረቱ ዘንድ። (1ጢሞ.6፡17) ስለ ድሆችም ልዑል ጌታችን አንዲት ሴት ሁለት ጸሪቅ ባገባች ጊዜ “ይህች ያላትን ገንዘቧን ሰጥታለችና ሌሎቹ የተረፋቸውን አገቡ አለ”(ማር.12፡42-43)፡፡ ዳግመኛም “የክርስቶስ ወገኖች ናቸው ብሎ በስሜ ቀዝቃዛ ጽዋ ያጠጣችሁ ዋጋውን አያጣም ብዬ እነግራችኋለሁ አለ”(ማር.8,9፡41)
ዳግመኛም ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ በኢሳይያስ አንደበት “ምግብህን በአንተና በተራቡት መካከል ከፍለህ ስጥ” አለ(ኢሳ.58፡10) ዳግመኛም ሐዋርያት በዲድስቅልያ በ7ኛው አንቀጽ በተቻለህ መጠን ገንዘብ የሰጠህን እግዚአብሔርን ውደደው አሉ፡፡ የምትችለውንም አንድ ወይም ሁለት ወይም ሦስት ጸሪቅ ቢሆን ከሙዳየ ምጽዋት ጨምረው አሉ፤ ልትታዘዝ ብትወድም በገንዘብህ እንግዶችን ምሰላቸው፡፡ ከመበለቶች ድካም የተነሣ የሚሰጠው እንጀራ ምንም ትንሽ ቢሆን እግዚአብሔር ይቀበለዋል፡፡
ምንም የሌለውም ይጹም የምሳውንም ግማሽ ለድሆች ይስጥ፡፡ ዳግመኛም የታዘዘችው ምጽዋት ከሁለት ወገን ትከፈላለችና፡፡ ከሚመጸውት ሰው እጅ በስውርና በግልጥ ለተቸገሩ ለተራቡ ለተጠሙ ለተራቆቱ ለእንግዶች ለሕመምተኞች ለታሰሩት ለተሰደዱት ትከፈላለች፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን “ምጽዋትህ በስውር ብቻ ይሁን በስውር የሚያይህ አባትህ ገልጦ ዋጋህን ይሰጥሃል” እንዳለ(ማቴ.6፡3-4)በፍርድ ቀንም በቀኙ የሚቆሙትን ስለሚላቸው ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ዕብ.13 እንግዳ መቀበልን አትተዉ ብሎ እንደተናገረ እንግዳ በመቀበላቸው ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ይቀበሉ ዘንድ ያደላቸው አሉና፡፡ የታሠሩትንም ከእነርሱ ጋር እንደ ታሠራችሁ ሁናችሁ አስቡ፡፡
 በግልጥስ የሚመጸውት ሰው ወደ ተሾመው ካህን የሚወስዳት ናት፡፡ ይህችውም ዓሥራት በኩራት ስዕለት ናት ሐዋርያት እንደተናገሩ፡፡ አሥራት በኩራት ስዕለት ግን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚወስዷቸው ናቸው፡፡ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ለእግዚአብሔር አገልጋዮች ያካፍሏቸው፡፡ ደጋጉ ሹማምንት ያስተዳድሩበት ዘንድ ለነዳያን የሚያመጧትን ገንዘብ ግን እናት አባት ለሞቱባቸው፣ ለባልቴቶቹ ፣ለተቸገሩት፣ ችግር ላለባቸው ለእንግዶችም፣ ከፍለው ይስጧቸው፤ በእርሱ እግዚአብሔር እንዲቆጣጠራቸው እርሱ ይህን ሹመት በእጃቸው ያደረገ ለተቸገሩት ሰዎች በእውነት ከፍለው ይሰጡ ዘንድ ነውና፡፡ የቤተ እግዚአብሔርን ገንዘብ አታጥፉ አትብሉት ፈቃዳችሁን ለመፈጸም ብቻ አትበትኑት፡፡ በእግዚአብሔር ፊት የቀና መንገድ ይሆንላችሁ ዘንድ የተቸገሩትን ሰዎች አስተዳደሩበት እንጂ፡፡
አስቀድሞ የተባለውን ስሙ እኛም ዳግመኛ እነሆ ስዕለት ዓሥራት ለክርስቶስ አገልጋዮች ለካህናት አለቃ አስቀድሞ የታዘዘላቸውን በኩራት ለሚያገለግሉትም አስቀድሞ የታዘዘላቸውን እርሱን እንነግራችኋለን፡፡ ዛሬ ልትሰጡት የሚገባችሁን ስዕለት በኩራት አሥራት ዳግመኛ ወደ እርሱ አምጡት የተቸገሩትን እርሱ ያውቃቸዋልና ይኸውም የተሾመው ካህን ነው፡፡ ለእርሱ እንደሚገባው ሁሉ ለእያንዳንዱ ይመግባቸው አንዱ ሁለት ጊዜ ወይም ብዙ ጊዜ በአንድ ቀን በአንድ ሳምንት እንዳይቀበል ፈጽሞ ምንም ያልተቀበለ ሌላም እንዳይገኝ፡፡
የእህላችሁን መጀመሪያ የእጃችሁን ሥራ ስለ በረከት ወደ እርሱ አምጡ ይባርካችሁ ዘንድ ዓሥራታችሁን በኩራታችሁን ስዕለታችሁን እጅ መንሻችሁን መጀመሪያ የደረሰውን እህል ከወይኑ ከዘይቱ ከፍራፍሬው ከጸምሩ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ገንዘብ ሁሉ ለእርሱ ስጡት፡፡ እርሱ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና መሥዋዕታችሁን ይቀበል ዘንደ ዕጣናችሁም ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ያማረ ይሆን ዘንድ፡፡ እርሱም የእጃችሁን ሥራ ይባርክላችኋል የምድርንም ፍሬ እጅግ ያበዘላችኋል፡፡
በረከት በሚመጸውት ራስ ላይ ትኖራለችና ስለዚህ ምጽዋት ከሰው ወገን ለሰው ይገባልና፡፡ ምንም ለሚሿት  የምትገባ ብትሆን ነገር ግን የፈቃድ ጭንቅ ላለው ሰው አስቀድሞ መስጠት ይገባዋል ….
 ቀሪውን እናንተ አንብቡት ወዳጆቼ ቢሆንም ግን ሊቃውንቱ ምጽዋትን እንዴት ሞሽረው እንደሚናገሩላት አስተዋላችሁን? የላቀ ዋጋዋንስ እንዴት ባለ ቃል አጣፍጠው እንዳቀረቡልን ተመለከታችሁን? እንግዲህ ልጠቀም ያለ ይጠቀምባት፡፡
ከሊቃውንት አባቶቻችን በረከትና ረድኤት ይድረሰን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment