Friday, April 14, 2017

የነፍስ ወግ

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
6/08/2009

ረቂቅ የሆነ እርሱ ፈጣሪዬ በእርሱ ፊት ምንም ግዙፍ ብሆን ሚስቴ ላደረጋት ከምድር አፈር ለፈጠራት ሥጋዬ በእርግጥም ረቂቅ ነኝ፡፡ እርሱ የፈጠረኝ አምላክ በእርሱ አርአያና አምሳል የፈጠረኝ ቢሆንም እንደርሱ ረቂቅ ስለሆንኹ ረቂቃኑ መላእክትም ግዙፋኑ ፍጥረታትም የእርሱን አርአያ በግዘፍ እንዲያዩ አምለክ ሥጋ ሚስቴን ግዙፍ አድርጎ ፈጠራት፡፡
 ከመላእክት እኔ የምለየው ከሥጋ ጋር አንድ አካል መሆን ስለሚቻለኝ ነው፡፡ በሌላ ተፈጥሮዬ ግን ከእነርሱ ጋር አንድ ነኝ፡፡ ቢሆንም ለእኔ ከውድቀት በፊት የነበረው የሥጋ ተፈጥሮ በእጅጉ ይስማማኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም በገነት ለሥጋ የተሰጡ መብላት ሥጋን በሕይወት እንድትቆይ ምንም ዓይነት ሚና የላቸውምና ሥጋን በሕይወት ለማቆየት ስል ምንም ድካም የለብኝም ነበርና፡፡ ከውድቀት በኋላ ግን ከመላእክት ጉባኤ በልዩ ተፈጥሮ ሆኜ የአምላኬን ፍቅር እየተመገብሁ ከምኖርበት መኖሪያዬ ገነት በራሴው ጥፋት የክፋት ምክንያት የሆነውን ሞትን በሥጋዬ ላይ ሹሜ፥ ፍቅርን አጥፍቼ ፥ ፍርሃትን አንግሼ ከመላእክት ጉባኤ ተለየሁ፡፡

ይህች ምድር ለግዙፋን እንጂ ረቀቅ ለሆንኹት የግዞት ሥፍራ ነች፡፡ በዚህችም ምድር ሥጋ የምትሻውን ልፈጽም እባክናለሁ እንጂ በመላእክት ጉባኤ ሳለሁ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠኝ እወቀት ተሞልቼ በፍጹም ሐሴትና ደስታ የምኖረውን መኖር ቀቶብኛል፡፡ የመላእክት ገጽታቸው፣ ሕይወታቸው፣ ማዕዛቸው፣ ተልእኮአቸው ፣አምልኮአቸው፣ ዓለማቸው፣ ክብራቸው፣ ስማቸው፣ ሁሉ ፈጽሞ ተረስቶኛል፡፡ እና በዚህ ምድር ብቸኝነቱ አጎሳቁሎኛል፤ ሁል ጊዜም ቢሆን በሐዘን ውስጥ ነኝ፤ እንደኔ ረቀቃን የሆኑ የወደቁ መላእክት ወይም አጋንንት ይህን መታወሬን ተጠቅመው ሁሌም ሥጋዬ ላይ የነገሠውን የሞት ፍርሃት ተጠቅመው በኃጢአት ላይ ኃጢአትን በክፋት ላይ ክፋትን አምልታና አብዝታ እንድትፈጽም በማድረግ ይበልጥ ከአምላኬ እንድርቅ አደረጉኝ፡፡ ሞት ተፈርቶ  በሕይወት ለመቆየት ሲባል ይዋሻል፣ ይሰረቃል፣ ነፍስ ይጠፋል፣ መብላትም መተንፈስም በጉልበት ታምኖ ሆኖአል፤ ነጻነትም በጉልበት ይጨፈለቃል፤ ለዚህ እንደአማካሪዋ ደግሞ እኔ ነኝ ይህ ክፋቴ ግን ሁሌም ያሳዝነኛል፡፡
ሥጋዬ እኔ ከሌለሁ ሬሳ ናት፡፡ በራሷ በጎም ይሁን ክፉ ማድረግ አይቻላትም፡፡ ነገር ግን ፈቃዱ መንጭቶ እኔን ለክፋት የምታተጋኝ ሚስቴ ሥጋዬ ናት፡፡ ይህ የተገባ እንዳልሆነ እኔ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ይህቺ ምድር እኛ ለሥጋ በምንሰጣት ክፉ ምክርና ትዕቢት ምክንያት ጠፍታ ሥርዓቷ ተዛብቶአልና እንደ ጌታ ትእዛዝ በወዛችንና በድካማችን እንጀራን መብላት አድካሚና ውስብስብ አድርጎታል፤ ለዚህም አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የእኔንም የሥጋንም ድካም የሚያበዙ አሉ፡፡ ይህ ደግሞ በእነርሱ ላይ ጥላቻ እንዲኖረኝ ያደርገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ጠላትህን ውደድ በሚል በአምላክ ፊት የተወደደ አይደለም፡፡ ይህ በምድር በቆየሁበት ዘመን ሁሉ የሚገጥመኝ ነው፡፡ ቢሆንም ሥጋዬ አትብይ ይቅርብሽ ብላት ትሰማኛለችን? ምን ታድርገው ብላችሁ ነው ለሥጋ ሕይወቷ ብዙ ነገር ሆኖባታል፡፡ መጠለያ ትፈልጋለች፣ ምግብ ትፈልጋለች፣ ልብስ ትፈልጋለች እነዚህን በገንዘብ ገብይታ ታገኛቸዋለች፡፡ ምነው እኔም ወደ አምላኬ እንድመለስ እርሷም እርፍ ብላ ለአምላኳ በሰውነቷን እንድትቀድስ እንደ አየሩ መጠለያውም ምግቡም ልብሱም በሆነ አልኹኝ፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ አይሆንም የጌታ ፍርድ አይታጠፍምና፡፡
በኖህ ዘመን ክፋት ጣሪያ ነክታ ምድሪቱ ተበላሽታና ጎስቁላ ሳለች በዚህ የተከፋ የኖህ አባት ላሜሕ ከአያቱ ሄኖክ ሰምቶ ይሆን እንጃ “እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ይህ ያሳርፈናል” ሲል ልጁን ኖህ ብሎ ጠራው፡፡ ይህ ተግባራችንና የእጅ ሥራችን ያለው እኮ እንጀራ ለማግኘት ስንል መልካምን በማድረግ የምንተጋውን ተግባራችንን አይደለም፡፡ በምድርማ እንድከም እንጂ ከእነርሷ በምናገኘው ፍሬ መጽናናትን እንደምናገኝ የታወቀ ነው፡፡ እናም ላሜሕ ተግባራችንና የእጅ ሥራችን ያለው የክፋት ተግባራችንንና ሥራችንን ነበር፡፡ ስለዚህ ሙሴ አምላክ ምድር ተበላሸች፥ ሰውን በመፍጠሬ ተጸጸትሁ አለ፡፡ ይህ ክፋታችን ታዲያ መልካምን እየሠራ የሚደክመውን እንዴት ከፍሬ ያደርሰዋል? ድካሙ ላይ ድካም ይጨምረበታል እንጂ፡፡
የላሜሕ ናፍቆት ግን ምንም ክፉ አድራጊዎቹ በውኃ ሙላት ቢያልቁም ሊፈጸምለት አልቻለም፡፡ ከኖህ በኋላም ክፋት ይበልጥ ብሳለችና፡፡ እናም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው በእውነት ሊኖር የሚወድድ ካለ መዳኑን በመከራና በድካም ሊፈጽም ግድ ነው፡፡ ሕሊናው ግን ዕረፍት አለው፤ መልካምን እየሠራ በድካሙ ላይ ሌላ ድካም ሲጨመርበት ወይም ፍሬውን ሲነጥቁት ማየት ያበሳጨኛል፡፡
እኔ ነፍስ ይህንን ሁሉ አወጣሁ አወረድሁ ከንቱ ከንቱ የከንቱ ከንቱ እንደሆነ ተረዳሁ፤ የሚያሳዝነኝ ግን ከንቱ የሆነው ድካሙ ሳይሆን የድካሙ ጉዳት ነው፡፡ ይቀጥላል ወዳጀቼ …..

No comments:

Post a Comment