Sunday, March 26, 2017

ምጽአቱ ለክርስቶስ


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
17/07/2009


ወዮ ይህች ከእውነተኛ ጌታ የወጣች ትምህርት እንዴት ታስፈራለች ? እርሱ  ስለትንሣኤ ሕይወታችን በዐሥሩ ደናግላን መስሎ አስተማረን እንዲህም አለን፥-"በዚያን ጊዜ" ያላት ያችን የምታስፈራዋን የምጽአቱን ቀን ነው።  በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች" አለን። በአሥሩ ደናግላን የተመሰልነው እኛ በጥምቀት ለክርስቶስ የታጭነው ክርስቲያኖችን ነን። ስለሆነም ጌታችን ክርስቲያን መሆናችን ብቻ እንደማያድነን እምነትን ከምግባር፥ እምነትን ከፍቅር ጋር፥ እምነትን ከጦም ከጸሎት ከስግደት ከምጽዋት ጋር አብረን አስተባብረን ይዘን የብርሃን መላእክትን መስለን ራሳችንን ከኃጢአት ጠብቀን የጌታን መምጣት በናፍቆት እንጠብቅ ዘንድ እንዲገባን ሊያስተምረን እንዲህ አለን።
ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች" ነበሩ አለን።  ሰነፎቹ እምነትን ከፍቅር፥  ከምግባር፥ከጦም ከጸሎት ከምጽዋት ጋር ያልያዙ ምንም መልካም ፍሬን ያላፈሩ ክርስቲያኖች ናቸው።  "አምስቱም ልባሞች ነበሩ" አለን እነዚህ ልባሞት በትጋትና በማስተዋል በቅድስና የሚመላለሱ ወገኖች ናቸው።  "ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙም" አለን የክርስትና ስሙን እንጂ ወንጌን ብርሃን አድርገው በቅድስና ያልተመላለሱ ዓለሙን የመሠሉ ብርሃናቸው በሰው ፊት ያልበራ ይልቁኑ በእነርሱ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በማያምኑት ዘንድ እንዲሰደብ ምክንያት የሆኑ ናቸው። "ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ" አለን። 
 ማሰሮ ያለው ይህ የጌታ ቤተምቅደስ የሆነው ሰውነታችን ነው።  ዘይቱም በእርሱ ያለው መልካም ክርስቲያናዊ ሰብእና ነው። መብራቱ በእምነት የተለኮሰው ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ነው። ይህን የጽድቅ መብራት አብርተው እድሜ ዘመናቸውን በቅድስና ተመላለሱ " ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ " አለ።  እንዲህ ሲል"ጌታችን ራሱ ከቀጠራት ሰዓት ዘግይቶ ይመጣል እያለን አይደለም። በእርሱ ዘንድ ሀስት የለም። አንድን ነገር እፈጽማለው ባለበት ሰዓት ይፈጽማል። ዘገየ ሲል እርሱ ከመምጣቱ በፊት እነርሱ በሞት እንዳሸለቡ ሲያስረዳን ነው። በእርግጥ የጥፋት ርኩሰቱ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ ሳይመጣ የዓለም ፍጻሜ አይሆንምና በዚያን ጊዜ ደግሞ በክርስቶስ አምነው መከራውን ታግሠው የሚቆዩት ጥቂቶች ሲሆኑ ብዙዎቹ ያንቀላፋሉ።    ሞት እንደ እንቅልፍ ነው፥ ከሞት የምንነቃበት ጊዜ አለን። 
ስለዚህ ዳንኤል"በምድር ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት እኩሌቶቹ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እኩሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘለዓለም ጉስቁልና"(ዳን.12:2) ፡ብሎ ትንሣኤአችንን ከእንቅልፍ እንደመንቃት አድርጎ ነገረን።  ቢሆንም ግን እርሱ በሚመጣበት ጊዜ በሕይወት የሚኖሩም አሉ እነርሱ እርሱን ይቀብሉ ዘንድ ሥጋቸው ተለውጦ  የትንሣኤን ሥጋ ለብሰው ወደ እርሱ በወደ ላይ ይነጠቃሉ።(1ቆሮ.15:51-52: ፊልጽ.3:21፥1ተሰ.4:16-18)  "እኩል ሌሊትም ሲሆን" አለ ይህም ሰው ሁሉ በተዘናጋበትና ባላሰበበት ሰዓት እንደሚመጣ ሲነግርን ነው። ስለዚህ ዳዊት ባንቀላፋንም ጊዜ በማስተዋል እንድንሆን ያሳስበናል።
"ጌታችን በሚመጣበት ሰዓት  እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ" አለን። ጌታ ምድር ላይ ሊፈርድ ሲመጣ የእርሱ የሆነ ምልክት የሆነው መስቀል በሰማይ ይታያል፥ በዚያም የወጉት ያዩታል፥ በፊቱ እሳት ይነዳል፥ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል የትንሣኤውን ቀርን ይነፋል በዚያን ቅጽበት ሙታን ይነሣሉ በፍርዱ ዙፋን ፊት ይቆማሉ።" በዚያን ጊዜ "እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ" አለን። ብሩካን የሆኑ ሥራቸው በክርቶስ ፊት ይገለጣል፥ ስማቸውም በሕይወት መዝገብ ሰፍሮ ይገኛል። "ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው ልባሞቹ ግን መልሰው፦ ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው።10  ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ። በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና፦ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ።12  እርሱ ግን መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ።13  ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ " ብሎ ትምህርቱን አጠናቀቀ። ሰነፎቹ በትንሣኤ ከዚያ ጽኑ ፍርድ አድኑን ብለው ድጋጎቹን ይለምኗቸዋል። እነርሱም ምህረትን ያሰጧቸው ዘንድ ሰዓቱ እንዳልሆን ስለሚረዱ ባለቤቱ ምናልባት ይምራችሁ እንደሆነ ለምኑት ይሏቸዋል። እነርሱም ሙሽራውን ሲጠባበቁ ዞር በሉ እናንት አመጸኞች ብሎ በሩን በላያቸው ላይ  ይዘጋባቸዋል።  አቤቱ እኔስ በፊት እቆም ዘንድ ማን ነኝ?  ወዮልኝ ለእኔ ወዮልኝ። አቤቱ ይቅር በለኝ።

No comments:

Post a Comment