Tuesday, March 21, 2017

ሦስት አጫጭር ጹሑፎች

በዙሪያችን ያሉ መምህራን

አንድ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ልማር ካለ በዙሪያው የሚያስተምሩት አሉለት። ከዋኖቹና ከማይሳሳቱ ሊሳሳቱ እስከሚችሉት መምህራን በቅደም ተከተል ልንገራችሁ ፥-
የመጀመሪያው መንፈስ ቅዱስ ነው። እርሱ ልጅነትን ከተቀበልንበት ጊዜ አንስቶ መምህራችን ነው። ሁለተኛው ሥጋው ወደሙ ነው። ሥጋው ወደሙን የሚቀብል ሰው ሁሌም ወደላይ ወደ መላእክት ጉባኤ በመነጠቅ ክርስቶስን ወደ ማወቅ ከፍታ እያደገ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ለሰዎች ሊነገር የማይገባውን ሰምቶ ይመለሳል። ያም ማለት ክርስቶስ ባለበት እርሱ በዚያ ይኖራል። ሌላው ከጠባቂ መላእክት ነው። እነርሱ ከእኛ አይለዩም ስለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ እንድን ዘንድ ያለንን ማስተዋልንንና እውቀትን በመስጠት ይረዱናል። ያዕቆብን በመከራው ጊዜ የተራዳው እርሱ ጠባቂ መልአኩ ነበር። አብርሃምን ያስተማረው ለዳንኤል እውቀትንና ማስተዋልን የሰጠው እርሱ ነው ሌላው  በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት ናቸው እነዚህ ለአንድ ኦርትዶክስ ክርስቲያን  ከተጠቀመባቸው መምህራኖቹ ናቸው። ከዚያ በኋላ ልንሳሳት የምንችለው እኛ መምህራን እንከተላለን። 
ቢሆንም ግን ክብር ይግባውና የእግዚአብሔርን ድምጽ  እናውቀዋለንና አዲስም ቢሆን ከእግዚአብሔር የሆነውና ያልሆነውን የምንለይበት ሕሊናና መንፈስ ቅዱስ አለን። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆኖ ከእውቀት ባዶ ሆኖ መገኘት ይከብዳል።


በአፉ መሳም ይሳመኝ

 ስለጠፋነው ስለእኛ ስለ ልጆቹ ጌታ ምን እንዳደረገ ሳስብ ዝም ሲል እደሌለ የቆጠርነው 
አምላክ ስለእኛ ያለውን ፍቅርና ርኅራኄ አስብና ሃዘኔን ለጊዜውም ቢሆን እረሳዋለሁ። ቃሉም እንዲህ ይላል፥-
"እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው" ኦ ጌታ ሆይ  ከአንተም ከሰውም ተንቆና ተጎሳቁሎ፥ በኃጢአት ቆሽሾ በሥጋውም አድፎ በድህነት ማቆ መንምኖ ቆዳው ከአጥንቱ ተጣግቶ ለነበረው ለዚህ ምስኪን የመጨረሻውን እስትንፋሱን ሰምተህ ለእርሱ ያሳየኸው ፍቅርና የሰጠኸው ክብር እንዴት ድንቅ ነው? ይህን ድንቅ ፍቅርህ ራሱን በፊትህ እንዲያዋርድ አደረገው እንደ ገዢ ሳይሆን እንደ ወላጅ አባት  ቆጥሮ "አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም" አለህ። ይህ አምላክ ለዚህ ምስኪን ሰው ያሳየው ፍቅር ውጤት ነው እንጂ ኃጥአን ልጆች ሳይሆኑ ባሮች ናቸውና ለእነርሱ የአባትነት ፍቅር እንደማይገባ ያውቀዋል። ስለዚህም ይህ ሰው አምላክ ለእርሱ ፍቅርን ያሳየው ዘንድ የማይገባ መሆኑን በማውቁ "ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው።" አባቱ ግን ፍጹም ስለሆነው ትሕትናው ብድራት አድርጎ ፍቅሩን ሰጠው ስለዚህ ባሪያዎቹን አለ፦ ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤ የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም" አላቸው። እነዚህን ሁሉ በረከቶች በመስቀል ላይ ሆኖ ሰጠው። በጥምቀት በሞቱ በመተባበር በትንሣኤ እርሱን ለብሶ ተነሣ፥ ለእጁም ቀለበቱ ቀኖቱ ነው፥ ለእግሩም የተጫማት ወንጌል ነው። የሰባውም ፍሪዳ ሥጋው ወደሙ ነው።   አምላኬ ሆይ ይህን በሃዘን ውስጥ ሆኜ አሰብሁት ለጊዜውም ቢሆን ሃዘኔን ረሳሁት አንተ እንዲህ ለሰዎች አዛኝ ነህና ጌታ ሆይ ከላይ ከአርያም ተመልከተን በፍቅርህና በረድኤትህ ጎብኘን። "በአፉ መሳም ይሳመኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና"(ማኅ.1:2)

ሕሊና ለአንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን

 አምላክ ለሰው ሕሊናን መስጠቱ በርቀት የሚኖረውን አምላክ እንዲረዳበትም ነው። እግዚአብሔር ስለ እርሱ ሊኖረን የሚገባውን እውቀት እናውቅበት ዘንድ ሕጉን በረቂቋ ሕሊናችን ውስጥ አትሟታል። በአመክንዮ ለምናቀርባቸው ሙግቶች መልስን ከዚህች የሕጉ ቋት ከሆነች ሕሊና እናገኛለን። ኦርቶዶክስ ክርስቲያንም ከመንፈስ ቅዱስ፥ ከመጽሐፍ፥ ከመምህራን፥ ከተፈጥሮ፥ ከሕግ አውጭዎች ሁሉ የሚገኙትን ሕግጋትና ሥርዓታት አሜን ብሎ የሚቀበለው እውነትን በምትለየው ሕሊናው ተጠቅሞ ነው። ስለዚህ ሕሊና ለአንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በእምነቱ ላይ ወሳኝ ናት።

No comments:

Post a Comment