Wednesday, April 8, 2015

የጌቴሴማኒው ጸሎት (ቅዱስ ኤፍሬም)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
30/07/2007

“ነፍሴ እስከሞት ድረስ እጅግ አዘነች” አለ የክብር ጌታ የሆነው ጌታችን፡፡ የተሰማውን እንዲህ ብሎ በግልጥ በመናገሩ የክብር ጌታ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አላፈረም፡፡ ለማስመሰልም ብሎ አይደለም፤ በእውነት ነፍሱ እስከሞት ድረስ አጅግ ስላዘነች እንጂ፡፡ ምክንያቱም በእውነት የእኛን ደካማ የሆነ ሥጋችንን በመልበሱና የሥጋን መከራ ከምትካፈለው ነፍሳችን ጋር አንድ በመሆኑ ነው እንጂ፡፡ እርሱ የተናገረው በሙሉ እውነት ነው፤ እንደ አስመሳይ የሰወረን አንዳች ነገር የለም፡፡ በዚህም አንድ አማኝ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ራሱን እንዳያስታብይና እውነትን እንዳይሰወራት ጌታችን በተግባር አብነት ሆኖት እናገኘዋለን፡፡

ከሃዲያንን ለማሳፈር ጌታችን “በሰው ፊት የሚክደኝን እኔ ደግሞ በአባቴ ፊት እክደዋለሁ”(ማቴ፡10፡33)ብሎ ነበረ፡፡ ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ ኑ በልጁ በክርስቶስ ስለተደረገልን ታላቅ ሥራ ምስጋናን እናቅርብ፤ ሃሰት እኛን እውነት ከሆነው አምላክ ለይቶን ነበርና በአንድ ልጁ እውነት ግን ከሃሰት መንገድ ወጣን፡፡ ስለዚህ ከትእቢት በላይ እኛን ከጸጋው ሙላት የሚለየን እንደሌለ ማንም አማኝ ቢሆን ሊረዳው ይገባዋል፡፡ አምላክ የሚወዳት ትሕትናም ከእውነት የሆነች ከእውነት የመነጨች እንጂ ለሽንገላ ያልሆነችውን ትሕትናን ነው፡፡
“ጥቂት ወደ ፊት እለፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፡- አባቴ ቢቻልስ ይህቺ ጽዋ ከእኔ ትለፍ”  አለ፥ በእርሱ ላይ አንዳች የሚሰለጥን የሌለበት ጌታ፡፡ እንዲህ ማለቱ እርሱ በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ስለማያውቅ አይደለም፡፡ ከዚህም አልፎ የደቀ መዛሙርቱን ማርጎምጎም፣ የስምዖንን ክህደት፣  የይሁዳን ራስን ማጥፋት፣ የኢየሩሳሌምን ጥፋት፣ የእስራኤላዊያንን መበታተን ጠንቅቆ የሚያውቅ ጌታ ነው፡፡ ስለምንድን ነው ታዲያ “አባቴ ቢቻልስ ይህቺ ጽዋ ከእኔ ትለፍ” ያለበት ምክንያት?
 ጌታችን ስለሞቱና ስለትንሣኤው በተናገረ ጊዜ ጴጥሮስ  “አይሁንብህ ጌታ ሆይ አይሁንብህ” በማለቱ ጌታ በተግሣጽ ቃል “ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና” ብሎት ነበረ፡፡ ጌታ ሆይ  ስለምን ነበር ጴጥሮስ የእግዚአብሔር ሃሳብ ዘንግቶ የሰውን ሊያቆም የሞከረው? ጌታችንስ ቅዱስ ጴጥሮስ “አይሁንብህ ጌታ ሆይ አይሁንብህ” በማለቱ ስለምን ገሠጸው? እንዲህ  ማለቱስ ምን ጥፋት ነበረው? ጌታ ሆይ አንተም እኮ“ቢቻልስ ይህቺ ጽዋ ከእኔ ትለፍ” አላልህምን? ምን ይሆን የጴጥሮስ ጥፋቱ ጌታ ሆይ? ነገር ግን እርሱ ጌታችን የአባቱ ፈቃድ ምን እንደሆነና ምን እንደሚል የሚያውቅ የአብ ፈቃድ ፈቃዱ የሆነ ጌታ ነው፡፡ ይህቺንም ጽዋ በፈቃዱ ሊያሳልፋት እንደሚችልም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ከእርሱ የተሰወረች እርሱ የማያውቃት የአብ ምስጢርና ፈቃድ የለችም፡፡  ጌታችንም  ነፍሱን ሊያኖራትና ሊለያት እንዲችል ማንም ቢሆን በእርሱ ላይ ስልጣን ያለው አካል እንደሌለ እንዲህም ስለሆነ ራሱን ስለብዙዎች መዳን ቤዛ ያደርግ ዘንድ አብ እንደላከው ከሞቱ አስቀድሞ ተናግሮአል።(ዮሐ.10፡17) እናም  የጌታችን ወደዚህ ምድር መምጣት ይህቺን የሞት ጽዋ በመቀበል ነቢያትና ሰማዕታት በሞታቸው ሊከፍሉት ያልቻሉትን እዳችንን ለመክፈል ነው፡፡
ጌታችን “አባቴ ቢቻልስ ይህቺ ጽዋ ከእኔ ትለፍ” ቢልም ጽዋውን ከመቀበል አልተመለሰም ነበር። ይልቁኑ ስለእኛ የሞትን ጽዋ ጠጣ፡፡ ለምን? በነቢያቱ ስለኃጢአታችን እንዲሞት የተነገረውና የአንዱን የእርሱን የጻድቁን ሞት ምሥጢር  ሊፈጽመው እንደመጣ እንረዳው ዘንድ ነው፡፡  እርሱ ይህን ጽዋ ለመቀበል ፈቃዱ ባይኖረው ኖሮ ሰውነቱን ከቤተ መቅደሱ ጋር አነጻጽሮ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አነሣዋለሁ” ባላለን ነበር። ወይም ለዘብዴዎስ ልጆች “እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ እኔ የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” ባላላቸው ነበር። ወይም “የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ”(ሉቃ.12፡50)  እንዲሁም “ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል፡፡”(ዮሐ.3፡14-15) ወይም “ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል”(ማቴ.12፡40) ብሎ መናገር ባላስፈለገው ነበር። ወይም “ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራን ይቀበልና ይገደል ዘንድ እንዲገባው …”(ማቴ16፡፡21) ወይም “ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር” ወይም “የሰው ልጅስ ስለእርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበረ” (ማቴ.26፡24) ባላለ ነበር።በእነዚህ ሁሉ ጥቅሶች ጌታችን ሞትን ለመቀበል አንዳልፈራ ነገር ግን በፈቃዱ ሞታችንን እንደተቀበለ አንረዳምን? ይህም እስከ ሞት ድረስ በሚደርስ ፈተና ላይ ሳለን የእኛ ፈቃድ ሳይሆን የአብ ፈቃድ እንዲፈጸም ልንጠይቅ እንዲገባ የሚያስተምረን አይደለምን? ….  ይቀጥላል

 በጌታ የተወደዳችሁ ወገኖቼ ሆይ ጌታችን “ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል”(ማቴ.12፡40) ካለው ቃሉ ምን ትረዳላችሁ ግን? መልሳችሁን በጉጉት እጠብቃለሁ

No comments:

Post a Comment