Tuesday, May 5, 2015

ወገኖቼ አንድ እውነት ልንገራችሁ



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

27/08/2007

 እውነቱም ይህ ነው፡- ደስታና እረፍት አይደለም በምድራዊ ሕይወታችን ውስጥ ይቅርና በመንፈሳዊው ምልልሳችን እንኳ ሁሌ የምናገኘው አይደለም፡፡ በምድር የምናጣጥማቸው ደስታና እረፍት መገኛቸው ከእግዚአብሔር ስጦታዎች እንጂ ከሌላ ከምንም አናገኛቸውም። ቢሆንም እነዚህ የሚታወኩበት ጊዜ ስለሚመጣ ያኔ ደስታህና እረፍትህ ለጊዜውም ቢሆን ሊወሰዱብህ ይችላሉ፡፡ እንዲህም ቢሆን ተፈጥሮውያኑ የእግዚአብሔር ስጦታዎች እየተጤኑ ካልሆኑ በቀር ከወይኒ ቤትም በላይ የከፉ የስቃይ እስር ቤት ሊሆኑብህ ይችላሉ፡፡
ስለዚህ ወገኔ በእነዚህ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ሙሉ ለሙሉ ባይሆን እንኳ የደስታህና የእረፍትህ እርሾ ከአንተ ፈጽሞ እንዳይወሰድ ከፈለግህ አስቀድመህ ይሉንታን ከራስህ አርቅ ፡፡ ይሉንታ የደስታንና የእረፍትን እርሾ ፈጽሞ ከሰውነትህ የሚያስወግድና በምትኩ የማይጠፋ የቁጭት ፍም አኑሮ የሚያልፍ ነው፡፡ ስለዚህ ወዳጄ ሕሊናህ የሚልህን ስማው ፤ ሕሊና የአንተን ደስታና እረፍት ጠንቅቆ የሚያውቅና የቁጭት ፍምን ከአንተ የሚያርቅ መለኪያህ ነው፡፡
 ወዳጄ እንደ ምሳሌ እናንሣ ብንል እንኳ ተፈጥሮአውያን ስጦታዎች ከሆኑት መካከል አንዱና ዋነኛው ፆታዊ ፍቅር ነው።
  ወገኔ ሆይ ትዳር መልካም ነው፤ ነገር ግን ለትዳር ጓደኝነት ከውጫዊ ቁሳቁሶች በፊት ፍቅርን አስቀድም፡፡ ከዚያ በኋላ በትዳርህ ደስታና እረፍትን ታገኛለህ፡፡ 

ወዳጄ ሆይ ይህ ፍቅር እግዚአብሔር ለሰው ዘር ሁሉ ሲፈጠር የሰጠው የትዳር መሠረት ነው፡፡ ክርስቲያን ከሆንህ ማንንም ልትወድድ ተጠርተሃል ቢሆንም ግን አንዷን ብቻ ልታፈቅር ተፈጥረሃል፡፡
 እንዲሁም እኅቴ ሆይ በእርግጥ መውደድ እግዚአብሔርን ከማወቅ የሚመነጭ እንጂ ውለታን የሚያስቀድም አይደለም፡፡ ያለበለዚያ መውደድሽ አድሏዊ ሊሆን ነው፡፡ወዳጅሽን ወድደሽ ጠላትሽን ልትጠይው የሚገባ አይደለምና፡፡ እንዲህ ዓይነት መውደድ እግዚአብሔር የሚፈቅደው መውደድ አይደለም፡፡ እርሱ እግዚአብሔር እኛን እንዲሁ እንደወደደን እኛም ፍጥረቱን በተለይ የሰውን ዘር ሁሉ እንዲሁ ልንወድድ ይገባናል፥ በተለይ ክርስቲያን ነን ለምንል ለእኛ ቃሉ ይሠራል፡፡ 
ቢሆንም ግን ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ እግዚአብሔርን ማወቅ፣ ማወቅ ብቻ አይደለም ለእርሱ በመታዘዝ እርሱን መቅመስን ይጠይቃል፡፡  ከዚያ በኋላ ነው ሰውን እንደሚገባና እግዚአብሔር እንደሚፈቅደው መውደድ የሚቻለን፡፡ 
ነገር ግን ውድ እኅቴ ሆይ ልብ ልትይው የሚገባ ቁም ነገር አንቺ በፍቅር ልትወድቂለት የምትችይው ለአንድ ሰው ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ይህም ጤናማና መሠረታዊ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በሚፈቅደው መውደድ ምንም እንኳ ሰውን ሁሉ ብትወጂ ለትዳር ጥምረት ግን የምታፈቅሪውን እንጂ የምትወጂውን አትመርጪም፤ እንድትመርጪም አልመክርሽም፡፡ ምክንያቱም ይህ ሁሉን መውደድ ለትዳር የተሰጠ መውደድ ሳይሆን ለአብሮነት የተሰጠ መውደድ ነው፡፡ እናም ፍጥረትን ሁሉ እኩል በምትወጂበት መውደድ ትዳር ብትመሠርቺ በእውነት ነው የምልሽ ልብሽ በእጅጉ ይጎዳል፡፡ የትዳር ዘመንሽ ሁሉ በለበጣና በሽንገላ የተሞላ ይሆናል፡፡ 
ለወንዱም እንዲሁ ነው ያለፍቅር ወደ ትዳር ብትገባ አንገትህን ደፍተህ ባለመጣጣምና ባለመግባባት ዘመንህ ጨልሞብህ ትኖራለህ፡፡  ስለዚህ ክርስቲያን የሰውን ዘር ሁሉ ባለመውደዱ ሊኮነን ይችላል፤ ባለማፍቀሩ ግን አይኮነንም፡፡ መውደድና ማፍቀር ለየቅል ነው፡፡ ያለ ፍቅር ትዳርን የመሠረተ ሰው እድሜ ዘመኑን ሙሉ በጽኑ እስር ቤት ውስጥ ጥሎአልና  ደስታና እረፍት የራቀው ሰው ይሆናል፡፡ ፍቅር ለአንድ ሰው ነው እንጂ ለሁሉ የሚሰጡት የእግዚአብሔር ስጦታ አይደለም፡፡ እንዲያ ከሆነ ግን ምንዝርና ነው፡፡ 
ስለዚህ ወገኖቼ ወደ ታላቁ ለሰው ደስታና እረፍት ብሎ እግዚአብሔር ወደመሠረተው ትዳር ከመግባታችሁ በፊት ደስታችሁና እረፍታችሁ ለዘለዓለም እንዳይነጠቅባችሁ ትዳራችሁ ፍቅርን እንጂ ገንዘብን፣ ዘርን፣ ክብርን ወይም ጥቅምን መሠረት ያደረገ እንዳይሆን ተጠንቀቁ፡፡ 
ወገኔ ሆይ እንደሚባለው ትዳር ከዝሙት ለመጠበቅ፣ ለመረዳዳት ወይም ዘርን ለመተካት ተብሎ የሚገባበት ሕይወት አይደለም፡፡ ፍቅር በራሱ ትዳርን ያመጣዋል እንጂ ትዳር ፍቅርን አያመጣውም፡፡ ስለፍቅር ትዳር ለሰው ልጆች ተሠራ እንጂ ትዳር ስለፍቅር ለሰው ልጆች አልተሠራም፡፡ ከዝሙት ለመጠበቅ ለመረዳዳት ወይም ዘርን ለመተካት ትዳር አልተሰጠም፡፡ ስለፍቅር ግን ትዳር ለሰው ልጆች ሁሉ ተሰጥቶአል፡፡  ከዝሙት መጠበቅም ሆነ መረዳዳት ፍቅር ላይ በተመሠረተ ትዳር ውስጥ በሙላት ይገኛሉ፡፡ ያለፍቅር በተመሠረተ ትዳር ውስጥ ግን ከዝሙት መጠበቅም ሆነ ከልብ የመነጨ መረዳዳትና መናበብ የማይታሰብ ነው፡፡ ዘርን መተካት ግን ይቻል ይሆናል፡፡ ግን ፍቅር ሕይወቱ ለሆነው ወደዚህ ዓለም ለሚመጣው አብራካችሁ ግን ወደዚህች ምድር የመምጣቱ ዓላማ ተምታቶበት ስለሚያድግ ገና ከጀምሩ መጪው ሕይወቱ በፈተና የታጠረና መራራ ይሆንበታል፡፡
 ያለ ፍቅር ወደ ትዳር መምጣት ማለት ራስን በገዛ ፈቃድ በሚዳሰስ ጨለማ ውስጥ በጽኑ ሰማያዊ ወኅኒቤት ውስጥ መጣል ማለት ነው፡፡ ይህም ከሲኦል የሚተናነስ አይደለም፡፡ ወይም ሰብአዊነትን ወደ ማጣት የሚያደርስ ከክፉም የባሰ ክፉ የእግር እሳትና የጭቁር ቁስል ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ትዳር ያልገባችሁ ወገኖቼ እመክራችኋለሁ፤ ትዳርን በተመለከተ ከይሉንታ ራሳችሁን አርቁ፤ በፍጹም የማታፈቅሩትን ይሉንታ ይዙዋችሁ፣ ውለታው ከብዷችሁ፣ ችግር አስገደዷቸሁ ምድራዊ ሀብትን ጓጉታችሁ አትግቡ፡፡ 
ራሱ ፍቅር ወደ ትዳር ያምጣችሁ እንጂ አስቀድሞ የሌለውን ፍቅር በትዳር ውስጥ አመጣዋለሁ ብላችሁ ራሳችሁን ወደ ማትወጡበት አዘቅጥ አትጣሉ፡፡ ፍቅር ትዳር ነው ትዳርም በፍቅር ነው፤ ነገር ግን ፍቅር በሌለበት ትዳር ትዳር አይባልም፡፡ ምክንያቱም ፍቅር የለበትምና፤ ፍቅር ከሌለበት እንግዲህ ወኅኒ ቤት እንጂ ትዳር አይደለም፡፡ እናም ወገኖቼ የምነግራችሁ እውነት ይህ ነው፡፡ ለትዳራችሁ ፍቅርን አስቀድሙ፡፡ በፍቅርም ወደ ትዳር ኑ እንዲያ ከሆነ ብቻ ነው እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሠራው ትዳር ደስታና እረፍት ልታተርፉ የሚቻላችሁ፡፡

1 comment:

  1. Geta yabertak sle kdsna deregawoch lebechaw meshafe btsfe des yeleghal memenum yanebewal

    ReplyDelete