በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/10/2007
ተወዳጆች ሆይ ሌላም ግሩም የሆነውን በቅዱሳን አባቶች ዘንድ ያለውን ትርጓሜ ልንገራችሁ፡፡ አባቶች ዘፍ.1፡1-4 ያለው ነቢዩ ሙሴ ስለክርስትና በምሥጢር የተናገረባት ነው ብለው ይተረጉሙታል፡፡ “ቀንም ሆነ ሌሊትም ሆነ አንድ ቀን” የሚለውም ስምንተኛዋ ቀን ናት ይሏታል፡፡ ይህቺ ቀን ፀሐይና ጨረቃ እንዲሁም ከዋክብት ለምድር ብርሃንን ከመስጠታቸው በፊት የነበረች ቀን ነች፡፡
በእርግጥ እንዲህ ሲሉ አንዳች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ሳይዙ አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይለናል “ በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ ፡- በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና” (2ቆሮ.4፡6፤ዘፍ.1፡3) ይለናል።
የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን የተባለውና ለልቡናችን ብርሃን የሆነን እርሱ ክርስቶስ አስቀድሞ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር መሆኑን ነው ቅዱስ ጳውሎስ የገለጠልን፡፡ በእርግጥ ይህን አስመልክቶ ዮሐንስም “በእርሱ ሕይወት ነበረች ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች” እንዲሁም “ለሰው ሀሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር” ብሎ መስክሮልናል፡፡ ክርስቶስም ስለራሱ ሲመሰክር “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሎናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ “እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀን ልጆች ናችሁና”(1ተሰ.5፡4-5) ብሎ እኛ በክርስቶስ ዳግም የተፈጠርን የቀን ልጆች መሆናችንን ገልጦልናል። ይህ ብርሃናችን ክርስቶስ ስለመሆኑ ሲገልጥልን እንደሆነ በራእይው“ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር።”(ራእይ.21፡23) ብሎ ጽፎልናል። ይህ እንዲህ እንዳለ ይህ የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን የተባለው በጉ ክርስቶስ "እግዚአብሔር" ስለመሆኑ ደግሞ “ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፥ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ”(ራእይ.22፡5) ብሎ ይ) ጽፎልናል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን ያለው “በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለው እርሱ ክርስቶስ እግዚአብሔር ስለመሆኑ ዮሐንስም እንዳረጋገጠልን በዚህ ኃይለ ቃል እንረዳለን፡፡
በእርሱ ብርሃንነት የምኖርባት በሐዋርያቱ "ቀን" የተባለችው መቼም ጸሐይና ጨረቃ ብርሃን ከሚሆኑዋቸው ቀናት በእጅጉ የተለየች ቀን እንደሆነች ሁላችሁ የተገነዘባችሁ ይመስለኛል፡፡ ይህቺን ቀንን ነው እንግዲህ አባቶች ስምነተኛዋ ቀን የሚሉአት፤ በእርሱዋ ዘንድ ጨለማ ብሎ ነገር የለም፡፡ ብርሃኑዋ ስሙ ብርሃን የሆነው እርሱ ክርስቶስ ነውና፡፡
አሁን እንግዲህ ይህን ልብ በማለት ነቢዩ ሙሴ በዘፍጥረት ላይ የጻፈልንን ትርጉም እንመልከተው “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” አለን፡፡ ይህ የእኛ ተፈጥሮ ምሳሌ ነው፡፡ ለእኛ ሰማያዊ የሆነች ነፍስ ምድራዊ የሆነች ሥጋ ያለችን ፍጥረታት ነን፡፡ ነገር ግን በአንድነት የተፈጠሩልን እንጂ የተለያዮ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ሊቃውንቱ ሰውን ትንሿ ዓለም ብለው ይጠሩታል፡፡ ስለአፈጣጠሩ ደግሞ “ምድር ባዶ ነበረች አንዳችም አልነበረባትም ጨለማ በጥልቁ ውስጥ ነበረ” ብሎ ጻፈለን፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር አበጅቶት ነፍሱንም ከምንም ፈጠረለት ነገር ግን ያለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሰው እውቀቱ ድንቁርና ነውና ከመንፈስ ቅዱስ መሰጠት በፊት ያለው ተፈጥሮ በጨለማ የተዋጠና ባዶ ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የሕይወት እስትንፋስ እፍ ብሎባት ነፍስ ሕያው ነፍስ ያላት ሆናለች፡፡ ይህ በጥምቀት የሚፈጸምልን ስለመሆኑም “የእግዚአብሔር መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበረ” ብሎ ገለጠለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ ባደረበት የጥምቀት ውኃ ነውና አዲሱን ሰብእና ገንዘባችን የምናደርገው። “እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን አለ” ብርሃን ሆነ” ሲልም የክርስቶስን ለእኛ ያለውን ብርሃንነት ነው፡፡ ቀንም ሆነ ሌሊትም ሆነ አንድ ቀን ሲልም እውቀታችን ሙሉ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህም አዳም መልካሙንና ክፉውን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ የሚለው መፈጸሙ የሚያስረዳ ነው፡፡(ዘፍ.3፡22)
በዚህ መሠረት ነቢዩ ሙሴ ዘፍ.1፡1-4 ያለውን ሲጽፍልን በክርስቶስ ዳግም በመፈጠር ያለንን ሕይወት በምስጢር ሲገልጥልን መሆኑን ልብ እንላለን፡፡
በዚህ ላይ ጥያቄ ካላችሁ አስተናግዳለሁ የምታክሉትም ካለም አስተያየታችሁን እጠብቃለሁ፡፡
qale hiwot yasemalen bertu
ReplyDelete