Friday, July 10, 2015

ክርስቶስ የማይታየው አምላክ ምሳሌ የመባሉ ምክንያት



በዲ/ን   ሽመልስ መርጊያ
3/10/2007
ሕዝቅኤል እግዚአብሔር ለእርሱ እንዴት እንደተገለጠለት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር "በራሳቸውም ላይ ካለው ጠፈር በላይ ድምፅ ተሰማ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።  በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ። ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ታች እንደ እሳት ምስያ አየሁ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ። በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።"(ሕዝ.1:26-28)


በዚህ ኃይለ ቃል ላይ  በዙፋኑ አምሳያ ላይ "እንደ ሰው መልክ አምሳያ አየሁ" ካለ በኋላ  መጨረሻ ላይ  "የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁትም ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ" ብሎ ይደመድማል።

በዚህ በእግዚአብሔር ክብር መልክና ምሳሌ በተባለው ፊት መላእክት የማይታየውን አምላክ ያመልኩታል። ሕዝቅኤልም በእግዚአብሔር ክብር መልክና ምሳሌ ፊት የአምልኮ ስግድትን ለአምላኩ ሰግዶአል። በዚህም መልክ ክብርና ምሳሌ በኩልም እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን ተናግሮታል። ነገር ግን በዘፍጥረት ላይ በመልክም በመፍጠርም ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሆኑ ሰውን በመልካቸውና እንደምሳሌአቸው የፈጠሩ እንዳሉ"እግዚአብሔርም አለ:- ሰውን በመልካቸውና እንደምሳሌአቸው እንፍጠር"ዘፍ.1:24) ተብሎ ተጽፎልን እናገኛልን።  በመልካችንና እንደ ምሳሌአችን  ያለው     በሕዝቅኤል የተገለጠው መልክና ምሳሌ ነው። በዚህ መሠረት በመልካቸውና እንደ ምሳሌአቸው ሰውን የፈጠሩት እግዚአብሔር አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ መሆናቸውን ማንም መጽሐፍ ቅዱስን አስተውሎ ያነበበ በቀላሉ ይገነዘበዋል።

ስለዚህ እኛ የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ቃል ሰው መሆን በፊት እግዚአብሔር በፍጥረቱ የሚመለክበት ክብር መልክና ምሳሌ ነበረን። እግዚአብሔር ቃል ሰው በመሆኑ ምክንያት ግን ክርስቶስ ከእኛ የነሣው የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የሆነው ሰውነት አምላክ በመሆኑ ባሕርያችን በፍጥረት መመለክ ጀመረ። በክርስቶስም ሰውነት በኩልም አብና መንፈስ ቅዱስን ተመለኩ። ምክንያቱም አብ በእርሱ እርሱም በአብ ነውና እርሱን ያየ አብን አይቶአልና መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ በእርሱ ውስጥ ሕልው ሆኖ ይኖራልና እርሱም በመንፈስ ቅዱስ ውስጥ ሕልው ሆኖ ይኖራልና። ስለዚህ ለአብም ለመንፈስ ቅዱስ ፍጥረት ሁሉ አምልኮታቸውን  በክርስቶስ በኩል ያቀርባሉ። ስለዚህም ነው ክርስቶስ የማይታየው አምላክ ምሳሌ ነው መባሉ ተወዳጆች።

No comments:

Post a Comment