Tuesday, July 14, 2015

እድሜ ይስጥልኝ ብያለሁ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

07/11/2007

እንደ መንፈሳዊ መረዳት ድንቅ የሚለኝና የሥነ ተፈጥሮአችን አንዱና መሠረታዊ ክፍል  ስለሆነው ነገር ልንግራችሁ። ከእናት ማኅጸን ሥጋችን ከነፍሳችን ጋር ተዋሕዳ ከተፈጠረችበት ጊዜ አንስቶ ወደ እርጅናና ሞት ስታዘግም ነፍሳችን ግን እለት እለት እየታደስችና በእውቀት ሙሉ እየሆነች በመምጣት ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው እርሷ በእግዚአብር ዘንድ  እንደታወቀች እስክታውቅ ድረስ ደርሳ ፍጹም ወደ መሆን ታድጋለች። የዛኔ እግዚአብሔር አምላኩዋን አባ አባ ስትለው በፍጹም ልጅነት መንፈስ ሆና ነው። እንዲህ በመሰለ መንፈሳዊ ከፍታ እያደገ የሚመጣው ግን ሰሎሞን "ጥበብ" ያለው  ሲወድቅም ሲነሣ ያልራቀው  የእግዚአብሔር መንፈስ ከእርሱም ጋር የሆነለት ሰው ብቻ  ነው። 

መንፈስ ቅዱስ ፈቃዳችንን አክባሪ ነው። በልጅነታችን በወላጆቻችን ሥር ስለሆንን ምንም በጥምቀት ከእኛ ጋር ቢሆንም እርሱን እስክናውቀው ድረስ በእርሱ ፈቃድ እንመላለስ ዘንድ ሕሊናችንን ለጉሞ እንደፈቃዱ አይመራንም። ምክንያቱም ለእርሱ እንድንታዘዝለት የሚፈልገው በእውቀትና በፈቃድ ስለሆነ ነው። ነገር ግን ሥጋ እንደ  ሰዓት ዳግም ላትመለስበት ወደ እርጅናና ወደሞት ትነጉዳለች ፥ ሕጻን ሆኖ አይቀርም ወጣትነት ይተካዋል።
 ወጣትነት ከባድ ዘመን ነው። በዚህ እድሜአችን የመንፈስ ቅዱስን ምክር ቸል ብለን ስሜታችንን ተከትለን ስንነጉድ ፥ የኃጢአት እሳቱ ሲጠብሰን ፥ ሲያዋርደን፥  ዳግም ወደ እግዚአብሔር በለቅሶ ስንቀርብ፥  ቀና ብለን ስንሄድ፥ መልሰን በኃጢአት ስንጣድ እዚህም እዚያም ስንረግጥ እንገኛለን። ቢሆንም ግን ከክፉው እንደ ጠቢቡ ሰሎሞን ተዋርደን የውርደት አተላን ልሰን ከውርደታችን ስንማር። መልካሙን በመፈጸማችን  ደግሞ ኢዮብ 
 "ወደ ከተማይቱ በር በወጣሁ ጊዜ፥ 
በአደባባዩም ወንበሬን ባኖርሁ ጊዜ፥
ጐበዛዝት እኔን አይተው ተሸሸጉ፥ 
ሽማግሌዎችም ተነሥተው ቆሙ።
አለቆቹ ከመናገር ዝም አሉ፥ 
እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ጫኑ።
የታላላቆቹም ድምፅ አረመመ፤
ምላሳቸውም በትናጋቸው ተጣጋ።
የሰማችኝ ጆሮ አሞገሰችኝ፥ 
ያየችኝም ዓይን መሰከረችልኝ፤"(ኢዮ.29-11)   እንዲል መልካም የማድረግ ፍሬን  እናጣጥመዋለን። በሁለቱም ግን የተማርን እንሆናለን። ወደዚህ ሕይወት ከመግባታችን  አስቀድሞ ግን  ክፉና ደጉን እንደማያውቁ ሕጻናት ስለምንሆን በእርሱ እንክብካቤና ጥበቃ ሥር እንሆናለን በመፈሳዊው ሕይወትና እውቀት እንጠነክራለን።  ከዚያም መንፈሳዊ ውጊያ ይቀርብልናል። በኃጢአት እንፈተናለን ስንወድቅ የምናውቀው የእርሱ ጥባቆትና እንክብካቤ ይርቅና በሰይጣን አሳራችንን እንበላለን ውርደትን እንጠጣታለን። ከኃጢአታችን በንስሐ ስንመለስ ደግሞ ያ ሸክም ከእኛ ርቆ በውድቀታችን ያገኘንን ክፉ ውርደትንና ጉሰማ ዘንግትን እንዛናለን።
እንዲህ እንዲህ እያልን በራሳችን ወደመቆም እንመጣለን። በዚህ ጊዜ ግን ምርጫው የእኛ ይሆናል፥ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር መሆንና አለመሆን ጉዳቱንና ጥቅሙን ለይተን አውቀናልና። በዚህ ሁሉ ግን  መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ጋር የሆነለት ሰው ብጽዕ ነው። ምክንያቱም ጎልማሳነቱን አልፎ ወደ አዋቂ ሲመጣ ሙሉ ሰው ሲሆን የራሱን ፈቃድ ሳይሆን በውስጡ ያደረውን የመንፈስ ቅዱስን ፈቃድ በማዳመጥ ከቅድስና ወደ ቅድስና ከእውቀት ወደ እውቀት ያድጋል። በሞት በተጠራም ጊዜ ሙሉ ሆኖ ከቅዱሳን ማኅበር ይቀላቀላል። ለዚህ ይሆናል መሰለኝ ወዳጅን ሲመርቁ "እድሜ ይስጥልኝ" የመባሉ ፋይዳው።
 ያለበለዚያማ ጠቢቡ "ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ እጅግ ዘመንም በሕይወት ቢኖር ዕድሜውም እጅግ ዓመት ቢሆን፥ ነፍሱም መልካምን ባትጠግብ መቃብርንም ባያገኝ፥ እኔ ስለ እርሱ፦ ከእርሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል አልሁ። በከንቱ መጥቶአል በጨለማም ይሄዳል ስሙም በጨለማ ይሸፈናል፤ ደግሞም ፀሐይን አላየውም አላወቀውምም፤ ለዚህም ከዚያ ይልቅ ዕረፍት አለው። ሺህ ዓመት ሁለት ጊዜ በሕይወት ቢኖር መልካምንም ባያይ፥ ሁሉ ወደ አንድ ስፍራ የሚሄድ አይደለምን?" (መክ.6: 3-6) እንዲል እድሜን መገተቱ ምን ይጠቅማል ብላችሁ ነው ወዳጆች? 
እናም ተወዳጆች ሆይ እኔ በበጎው በረከት ጠግባችሁ በእውቀት ሙሉዋን ሆናችሁ በቅድስና ተጊጣችሁ በክብር ወደ ቅዱሳን ሕብረት ትሄዱ ዘንድ እድሜ ይስጥልኝ ብያለሁ።  

No comments:

Post a Comment