Monday, August 31, 2015

የተመሰገነችው ድህነት በቅዱስ ኤፍሬም


ትርጉም ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
25/12/2007

ቅዱስ ጳውሎስ "ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል።"(1ጢሞ.6:6-8) እንዳለው ክርስቶስን በመሰለና ለራስ በቂ በሆነ ሕይወት ውስጥ በመገኘት ናት በቅዱስ ኤፍሬም የተወደደችው ድህነት።
 ይህቺ ድህነት ሙሉ ትኩረትን እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚረዱ ተግባራት መኖርን ትጠይቃለች።ይህ ነው ለቅዱስ ኤፍሬም ድህነት የሚለው ቃል ትርጉሙ።  ድህነት የሥጋ ድህነት ማለት አይደለም ለቅዱስ ኤፍሬም ይህ እንዳልሆነ እርሱ ራሱ በቃሉ  "ለሥራ ከመትጋት አትለግም ምንም እንኳ ባለጠጋ ብትሆን፥ ሰነፍ ሰው በሥራ ፈትነቱ  የተነሣ ቁጥሩ የበዛ ኃጢአትን ይፈጽማታልና" ብሎ ይመክራል። ስለዚህ ድህነት ማለት ለቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ከሆነ ድህነት ሳይሆን ድኅነት ነው።

እርሱ ድሆች የሚላቸው በውጭ ሲታዩ ድሃ የሚመስሉ በውስጥ ግን ባለጠጎች የሆኑትን ነው። ለምሳሌ እንዲህ ከሆኑት መካከል ኤልያስንና ኤልስዓን አንስቶ እንዲህ ይላቸዋል:-  "ቁጥራቸው ከድሆች ወገን የሆኑ ኤልያስና ኤልስዓ ከላይ ያለውን ሰማያዊ ሀብትን ወደዱ። ድሃው ለድሃው ከሁሉ በላይ የሆነን ሃብትን ሰጠው። አንተም ከውጭ ሲታይ ድሃ የመሰለውን በውስጥ ግን ባለጠጋ የሆነውን የጌታህን ድሃ መሆን ከወደድህ የቃሉ ጅረት ከአንተ ፈልቆ አንተን የመንፈሱ መገልገያ በገና ያደርግሃል። በነፍስህም የእርሱን መልካም ስጦታ እያሰብህ የምስጋናን ቅኔን በውስጥህ ስትቀኝ ትኖራለህ።" መጽሐፉም በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው እንዲል እግዚአብሔርን በማወቅና ለእርሱ በመገዛት ሕይወት ውስጥ ሆነው በትሕትና የሚመላለሱ እነርሱ በእርግጥ በሥጋ ምንም ድሆች ቢሆኑ ባለጠጎች ናቸው። የእነርሱ ባለጠግነት ለኤልያስና ለኤልስዓ በሰጠው ታላቅ ስጦታ የተገለጠ ነውና።
ይህችን ድህነት ቅዱስ ኤፍሬም በክርስቶስ እንደታየች ሲገልጣት እንዲህ ይለናል።

"በዘመን ከሁሉ ይልቅ የሸመገልኸው ጌታዬ ሆይ አንተን የተሽከመችህ ማኅፀን ተፈጥሮአዊ ሥርዓትን እንዴት ቀየረችው? ወደዚች ማኅፀን ከሁሉ ይልቅ ባለጠጋ የሆነው ገባ ድሃ ሆኖ ተወለደ። በልዕልና የሚኖረው ወደዚህች ማኅፀን ገባ ትሑት ሆኖ ወጣ በብርሃን ውስጥ የሚኖረው እርሱ ወደ እርሷ ገባ ከእርሷም የተዋረደውን የሰውን ሥጋ ለብሶ ተወለደ" ይለናል። ይህም በእርሱ እኛን ባለጠጎች ለማድረግ ነው።

ይህን አስመልክቶም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይለናል:-
"የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ"(2ቆሮ.8:9)  እንዲሁም  " ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥
በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ"(ፊልጵ.2:7-8)

ይህችን በክርስቶስ የታየችውን በውስጧ ግን  በበረከት የተሞላች ድህነትን ነው እንግዲህ ቅዱስ ኤፍሬም የተመሰገነችው ድህነት የሚላት። ይህች ድህነት ራስን በፈጣሪ ፊት ማዋረድን የምትጠይቅ በትሕትና ያጌጠች በውስጧ ለሌሎች በሚተርፍ መንፈሳዊ ብልጥግና የተሞላችውን ናት።

ይህችን የተመሰገነች ድህነትን ምንነት ሲገልጣት :-

"ወደ እርሷ ለተጠጉ እንደ እናት ቸር ወደሆነች ድህነት ሽሹ፥ መጠጊያችሁም እርሷ ትሁናችሁ። እርሷ ልጆቹዋን ምርጥ ምርጥ በሆኑ መንፈሳዊ በረከቶች የምትመግብ ናት። ቀንበሩዋም ቀሊልና  ልዝብ እንዲሁ ደስ የምታሰኝ፥ ጣፋጭና ልዩ  ትዝታዎች በሕሊና ውስጥ የምታኖር ናት። በሕሊናው የታመመ ብቻ ግን ይህችን የመሰለችውን ድህነት ይጠላታል። ታካችም ክብርት የሆነችውን የዚህችን ድህነት ቀንበር መሸከምን ይፈራል" ይለናል።

ይህቺ ድህነት የመንፈሳዊ ብልጽግና ምንጭ እንደሆነች ቅዱስ ኤፍሬም :-

"በዚህች የብልጥግና ሁሉ ግምጃ ቤት በሆነች  ድህነት በእጅጉ ተገረምሁ። ደሃ ከሆነው በቀር ማንም ከዚህች የመንፈሳዊ ሀብታት ባለጠጋ የሆነ የለም። ነገር ግን አማንያን በእርሷ ዙሪያ ሲሰባሰቡና ከእርሷ ሲናጠቁ ሀብቶቹዋ እለት ከእለት እየጨመረ ይሄዳል እንጂ ከብልጥግናዋ አንዳች አይጎድልባትም ነበር። ይህችን መንፈሳዊ ምንጭን በጥልቀት ለነደላት ሰው እጅግ ግሩማን የሆኑት ሀብታት በዝቶ ይፈስለታል" ይለናል።

በዚህም ምክንያት እንዲህ ብሎ ይመክረናል:-  "ስለዚህ ድህነትን አፍቃሪ ሁን በመንፈስም ድሃ ለመሆንም መሻቱ ይኑርህ። እነዚህ በላይ ያለውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ያበቁሃል።"
እንዲህም ሲል  "በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።" ማለቱ ነው።(ማቴ.5:3)

ይህች ድህነት ብዙ ጊዜን ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትሰጥ በመንፈሳዊ ተግባራት የምትጠምድ ድህነት ናት። እነርሱም በጸሎት በጦም በምጽዋት በመንፈሳዊ መረዳት በተመስጦ በፍቅር በትሕትና የምትጠምድ ከእግዚአብሔር ጋር በትሕትና እንደ አብርሃም እንደ ሙሴ እንደ ሐዋርያት የምታነጋግር የራሷ መንፈሳዊ ክበብ ያላት ጥቅሟ በተግባር ሳይታክት ለሚሻት የምትታወቅ ሕይወት ናት። ይህቺ ናት እንግዲህ ቅዱስ ኤፍሬም የሚያሞካሻት ድህነትየሚላት ተወዳጆች።

No comments:

Post a Comment