Thursday, January 5, 2017

ዐይንተ አልባቢነ


ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
27/04/2009
መጽሐፍ ቅዱስ ሥጋንም ነፍስንም በተናጠል ሰውነት ይላቸዋል፡፡ ግዙፉን አካል ሰውነት እንዲለው አንዲሁ ቅዱስ ጳውሎስ “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ”(ኤፌ.3፡16-17) ብሎ እንደጻፈልን ረቂቋንም ነፍስ ውስጣዊ ሰውነት ይላታል፡፡ ይህ የተዋሕዶን ምሥጢር ለማስረዳት  ትልቅ ቁልፍ ቃል ነው፡፡ ምንም እንኳ መጽሐፍ ሥጋንና ነፍስን በተናጠል ሰውነት ይበላቸው እንጂ ሰውነታችን አንድ ነው፤ ሁለት አይደለም፡፡ ሰውነት ስንል ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የሥጋና የነፍስ አንድነት ስያሜ ነው፡፡ ሥጋና ነፍስ ፍጹም በሆነ ተዋሕዶ አንድ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን የየራሳቸው ግብር አላቸው ቢሆንም በተናጠል አይደለም፡፡
በክርስቶስም የምናየው ይህንን ነው፡፡ እርሱ “እንግዲህ የሰው ልጀ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?” በሚለው ቃሉ ለሰው ልጅነቱ ቅድምና ሰጥቶ መናገሩን እናስተውላለን፡፡ “በሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው”(ዕብ.2፡17) የሚለው ደግሞ ሰዋዊ ማንነቱ እንዳልተለወጠ ያስገነዝበናል፡፡ በዚህ ማነንቱ ሆኖ አምልኮ ለእርሱ ለእግዚአብሔር በግ ቀረበለት፡፡ ጌታ ተወለደልን ተባለ፤ ሕፃን ሳለ አምልኮን ከሰብአ ሰገል ተቀበለ፡፡ አንድያ የአግዚብሔር ልጅ፣ አምላክ፣ እግዚአብሔርም ተባለ፤ በደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ” ተብሎ”ደሙ" የእግዚአብሔር ደም ተባለ፡፡ በዚህም መለኮታዊ ልዕልናውን የሰው ልጅ ሲል እኛንም በመምሰሉ ራሱን የሰው ልጅ ብሎአል፡፡ ለሁለቱም ማንነቱ አንድ "የሰው ልጅ" የሚለውን ስያሜ ተጠቀመ፡፡ ይህም ከድንግል የተካፈለውን ሰውነት ከመለኮታዊ ልዕልናው መለኮታዊ ልዕልናውን ከሰውነቱ ነጣጥሎ እንዳላስተማረን በተረዳ ነገር ታወቀ፡፡ በዚህ ጥቅስና በሌሎችም ጥቅሶች ጌታችን የተዋሕዶውን ምሥጢር ገለጸልን፡፡
   
ይህን እዚህ ላይ ቆም እናድርገውን ግሩምና ድንቅ የሆነ ትይንትንና ረቅቂ አካላትን ወደምናስተውልባት ውስጣዊ ሰውነታችን እንመለስ፡፡ ጌታ ሆይ ይህቺን ውስጣዊ ሰውነታችንን ባትፈጥርልን ኖሮ በእውነት እንስሳትን በመሰልን ነበር፡፡
ወገኖቼ ሆይ የሰው ግዘፍ ሰውነቱ ዓይን የምታየውና ረቂቋ ውስጣዊ ዓይናችን የምታየው አንድ አይደለም፡፡ የግዘፍ ሰውነታችን ዓይን በግዘፍ የሚታዩትን በተፈጥሮአቸው መንፈስ ያልሆኑትን አካላት የምትመለከት ስትሆን፥ ረቂቋ ሰውነታችን ዓይኖች ግን ረቂቃን መላእክትንና እርሱ እንደተገለጠላት መጠን እግዚአብሔርን በርቀቱ ትመለከተዋለች፡፡  
የሚደንቀው አዳምና ሔዋን ከጥፋት በፊት እግዚአብሔርን አውቀው ከእግዚአብሔር በቀጥታ ትእዛዝን ለመቀበል የበቁት፤ በድለውም ሳሉ በገነት የጌታቸውን ድምፅ ሰምተው የተሸሸጉት በዚህች ሰውነታቸው አይተውና ጆሮዎች ሰምተው  ነው። ፍርዱንም ሲቀበሉ በዚህች አካላቸው ዓይተውና ሰምተው ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ክርስትና ከመግባቱ በፊትም ክርስቲያኖች በደማስቆ መገንድ ላይ ሲያሳድድ ሳለ በሕቡዕ የሚመለከተውን አምላኩን የተመለከተው ውጫዊው ዓይኖቹ ታውረው የውስጣዊ ሰውነቱ ዓይኖች ከበሩ በኋላ ነው፡፡ እንዲሁ የአብርሃምን ሚስት ሳራን ለራሱ ሚስት ትሆነው ዘንድ የወሰደው ንጉሥ አቤሜሌክ እግዚአብሔር በሕልሙ ለውስጣዊ ሰውነቱ ተገልጦ ስለ ሣራ የነቢይ ሚስት መሆን ነግሮት ከድርጊቱ  እንደዲመልስ አስጠነቀቀው፡፡ 
ገር ግን ሳናንቀላፋ አምላክም ሆነ መላእክት የሚገለጡልን ወቅት አለ፡፡ ሲገለጡልን ግን ውጫዊዋ ሰውነታችን በምታውቀው መልክ ነው፥ የምትረዳቸው ግን ውስጣዊ ሰውነታችን ናት፡፡ 
አይሁድ የውስጣዊ ሰውነታቸው ዓይኖች ስላልበሩ በሥጋ ለእኛ የተገለጠውን ክርስቶስን መረዳት ከበዳቸው፡፡ ነገር ግን አጋንንት እንኳ ለይተውት ጊዜአችን ሳይደርስ ልታጠፋን መጣህን? አሉት፡፡ የልቡናቸው ዓይኖች የበሩ ሐዋርያት ግን “እነሆ የእግዚአብሔር በግ” ብሎ ዮሐንስ መጥምቅ ሲያመላክታቸው ሳያመነቱ ተከተሉት፡፡
ይህ ነው እንግዲህ ተፈጥሮአዊና መንፈሳዊ ሰው የሚለይበት መሥፈርት፡፡ ፍጥረታዊው ሰው መንፈሳዊውን ሰው ሊመረምረው አይችልም፡፡ ምክንያቱም የውስጣዊ ሰውነቱ ዓይኖች አልበሩምና፡፡ መንፈሳዊው ሰው ግን ፍጥረታዊውን ሰው ያውቀዋል ምክንያቱም እንደ ፍጥረታዊው  ሰው የውጫዊው ዓይኖቹ ተከፍተዋል፥ ነገር ግን ውስጣዊ ዓይኖቹ እንደ ፍጥረታዊው ሰው  የታወሩ አይደሉም፡፡

አቤቱ ፈጣሪዬ ሆይ እባክህ የልቡናዬን ዓይኖች አብራልኝ፡፡ አንተንና መላእክትን በእምነትና እንደ ቅዱሳኖችህ በውስጥ ሰውነቴ ዓይኖች እንዳይና እንድሰማ አድርገኝ፡፡ የቅዱሳን ሁሉ ናፍቆት እርሱ ነውና፡፡  

No comments:

Post a Comment