Friday, January 6, 2017

የዕብራውያንን መልእክት እንዲህ እንረዳው? መቅድም

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ቀን 28/04/2009)

ክብር ይግባውና ሥላሴ በፍቅር ሸንጎው ስለ ሰው ልጆች መዳን ምክርን መከረ፡፡ ሰው በድሎአል አሳዝኖናልም ቢሆንም አርዓያችን ነውና ፈጽመን ልንጥለው አይገባንም  አለ። በመቀጠል “አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ይሆናል” ለጊዜው ግን ከእኛ ርቆ ይኖራል ብሎ ወሰነ፡፡ ምክራቸውንም እውን ለማድረግ ዘመን የማይቆጠርለት ሥላሴ ቀን ቆረጠ፡፡ በአርዓያውና በአምሳሉ የፈጠረውን የሰውን ልጅ ቤተሰብ ሊያደርግና ከወደቀበት ሊያነሣው እንዲሁም በእሪናው ሊያስቀምጠው ወልድ በፈቃዱ ሰው ሆነ፡፡
እርሱም ከአምላክነት እሪናው ሳይለይ ከቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ተገኘ፤ ሥጋና ነፍስ ነሥቶ ከጸጋ ተጓድሎ ደህይቶና ጎስቁሎ የነበረውን የሰውን ባሕርይ ገንዘቡ በማድረግ ሁሉን ወራሽ አደረገው፡፡ ከሥጋዌ በፊት የአብ የሆነ ሁሉ የወልድ ነበር የወልድ የሆነ ሁሉ የአብ ነበር፡፡ ይህ ሥጋ በመሆኑ የቀረ አልነበረም፡፡ ይልቁኑ የቃል የሆነ ሁሉ የሥጋ በመሆኑ ምክንያት ቃል ሥጋን ሁሉን ወራሽ አደረገው፡፡
በዚህ ግን ቃል ብቻ ሳይሆን አብም መንፈስ ቅዱስም ሥጋን ሁሉን ወራሽ አድርገውታል፡፡ አብ በማጽናት መንፈስ ቅዱስ በመክፈል ወልድ በመዋሐድ እኩል ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ ስለዚህ ሥጋን የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን ሁሉ ገንዘቡ እንዲያደርግ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እኩል ሚና ነበራቸው፡፡  ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ አብን ርስት ሰጪ በማድረግ ስለ ክርስቶስ “ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” ማለቱ፡፡


ዓለማትን በፈጠረበት ሲልም አብ ቃልን መሣሪያ አድርጎ ፍጥረታትን ፈጠረበት ብሎ የሚያስብ አይጠፋም በእርግጥ የጽሑፉ ባሕርይ አንባቢን እንዲያ ብሎ እንዲያስብ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን  ስለ አብ ይኸው ቅዱስ “የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? በማለት ይጠይቅና “ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ይላል፡፡ ይህ ያለ ማንም እገዛና ምክር ሥነፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ መፍጠሩን ያሳየናል፡፡ አስከትሎ ደግሞ “ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው? በማለት እርሱ እንዳሻው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ማንም ሳይሰለጥንበት ሁሉን እንደ ፈቃዱ የሚያደርግ እንደሆነ ይገልጽልናል፡፡ በመቀጠል ግን “ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱ ነውና ለእርሱ ለዘለዓለም ክብር ይሁን አሜን”(ሮሜ.11፡34-36) በማለት ፍጥረት ሁሉ ከእርሱ እንደተፈጠሩ በእርሱ እንደተፈጠሩ ለእርሱ እንደተፈጠሩ ይገልጽልናል፡፡
እዚህ ላይ ሊስተዋል የሚገባው ነገር ቢኖር ቅዱስ ጳውሎስ ለአብም “… ሁሉ በእርሱ …” የሚለውን ቃል መጠቀሙን ነው፡፡ እንዲህ ሲባል አብ ራሱ ራሱን መፍጠሪያ መሣሪያ አድርጎ ፍጥረታትን ፈጠረ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን እርሱ ፈጣሪ መሆኑን ለማስገንዘብ እንዲህ እንደተጻፈ መረዳት እንችላለን፡፡
እንዲሁ ዓለማትን በፈጠረበት ሲል አብ ወልድን እንደ መሣሪያ ተጠቅሞ ፈጠረበት እያለን ሳይሆን በመፍጠር ላይ የቃልን ሚና ሊገልጥልን ሲል እንዲህ እንዳለ ልብ ልንል እንችላለን፡፡ ያለበለዚያ ለአብም “ሁሉ በእርሱ “የሚልን ቃልን ተጠቅሞአልና አብን መሣሪያ አድርጎ ፍጥረትን የፈጠረ ማን ነው ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ እንዲህ ማለት ከእኛ ይራቅ፡፡
ቢሆንም ግን ነገሩን ግልጽ ለማድረግ መጽሐፍ ቅዱስ ለአብ የሰጠውን አገላለጽ መልሶ ለወልድም ሲጠቀምበት እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ፡- “ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጠረዋል”(ቆላ.1፡15-16) ይለናል፡፡ በዚህም ኃይለ ቃል ክርስቶስ ሁሉን በእርሱና ለራሱ መፍጠሩን እንረዳለን፡፡ ይህም ቃል ለአብ ከተነገረው “ሁሉ.. በእርሱ እና ለእርሱ ነው” ከሚለው ጋር አንድ ነው፡፡  ከዚህ በተጨማሪ ፍጥረት ሁሉ ከእርሱ በእርሱ ለእርሱ ስለመፈጠራቸው ሲናገር፡-  “ከእርሱ የተነሣ ሁሉ በእርሱ ሁሉ ለሆነ ለእርሱ ተገብቶታልና” (ዕብ.2፡8) በማለት ያስረዳናል፡፡ በዚህ “ከእርሱ በእርሱ ለእርሱ” የሚለውን አገላለጽ ቅዱስ ጳውሎስ ለአብ እንደተጠቀመ ለወልድም መጠቀሙን እናስተውላለን፡፡ ከዚህ ላይ አክለን ደግሞ እርሱ ሰማይንና ምድርን ስለመፍጠሩ “ጌታ ሆይ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው እነርሱ ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ”(ዕብ.1፡10-11) ብሎ ፍጥረታትን ያለ ማንም ድጋፍና እርዳት መፍጠሩንና እርሱ በፈቀደ ሰዓት ሰማይንና ምድርን እንደሚያሳልፋቸው ገልጦልናል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ ቅዱስ ጳውሎስ“ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” ቢል አብ ወልድን መፍጠሪያ አደረገው ማለቱ እንዳልሆነ ከላይ ያስቀመጥናቸው ጥቅሶች ማስረጃ ይሆኑናል፡፡
ይክበር ይመስገንና ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታችን ሊቀ ካህንነት ከመናገሩ እስቀድሞ ክህነቱን በራሱ መለኮታዊ ክበብ እንደፈጸመልን እንረዳው ዘንድ ስለ እርሱ አምላክነት በምዕራፍ አንድ ላይ አተተልን፡፡ እንደሚታወቀውም ጌታችን በመስቀል የተሰቀለው ደሙንም ያፈሰሰው በዚህች ምድር ነው፡፡ ነገር ግን በራሱ መለኮታዊ ማንነት ውስጥ ሆኖ ሁሉን በራሱ እንደፈጸመ ሊገልጥልን ቅዱስ ጳውሎስ "ኃጢአታችን በራሱ ካነጻ በኋላ በግርማው ቀኝ ተቀመጠ" ብሎ ዕብራውያን መልእክቱን ይጀምራል፡፡ ደግሞም መሐል ላይ ደሙን ይዞ በሰው እጅ ወዳልተሠራች መቅደስ ገባ ይለናል፡፡ መቼም እርሱን ወስና የምትይዝ መቅደስ ከፍጥረት ወገን የለችም፡፡ ስለዚህ መቅደስ የተባለው የራሱ መለኮታዊ ማንነት መሆኑን እንረዳለን፡፡ በዚያም ስለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ይታይልናል ተባለለት፡፡ እርሱ ሥጋም ሳይለብስ በሰማይም በምድር ሙሉ ነው ሥጋም ለብሶ ሙሉ ነው፡፡ ስለዚህ በእርሱ በምድር የተፈጸሙ የድኅነት ሥራዎች ሁሉ ሰማያውያን ናቸው ከሰማይም ይልቅ እጅግ ይረቃሉ ምክንያቱም በመለኮታዊው ማንነቱ ውስጥ ሆኖ ነውና ይህን የድኅነት ሥራ  የፈጸመልን፡፡ ይህ ለእኛ ያለውን ጥልቅና እውነተኛ ፍቅር እንድንረዳ አድርጎናል፡፡
እስቲ ልጠይቃችሁ ወገኖቼ በእውን ጌታችን ደሙን ይዞ አርጎአልን? በጭራሽ አላረገም፡፡ ነገር ግን በራሱ መለኮታዊ ክበብ ውስጥ ስለሚፈጽመው በሰማይም እንደተፈጸመልን እንረዳለን፡፡ ዕብራውያን ሰማይ ሲባል ምን እንደሆነ በደንብ ይገባቸዋል። በእነርሱ ዘንድ እግዚአብሔርን ሰማይ ማለት የተለመደ ነው፡፡ ይህም ልዕልናውን ለመግለጽ ሲሉ ነው፡፡ እንዲሁም እርሱ ለፍጥረት ሁሉ ዓለምና ሕይወት ሆኖአቸው በእርሱ ሥልጣን ሥር ይኖራሉና ሰማይ ይሉታል፡፡
ወንጌላውያን ጌታችን ደሙን ይዞ ወደ ሰማይ አረገ ብለው አልጻፉልንም፡፡ ታዲያ ቅዱስ ጳውሎስ ለምን እንዲህ አለ? በእጅ ያልተሠራ መቅደሱ የተባለው የራሱ መለኮታዊ ማንነት ስለመሆኑ “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት አለን”(ዕብ.10፡19-20) እንዲል በሥጋው በኩል ወደ ቅድስት መግባትን አግኝተናል፡፡  ለምን ይህ ሁሉ አለ? ይህም ምን ማለት ነው? በሥጋ በፈጸመው የድኅነት ሥራ መዳንን አገኘን ማለት ነው፡፡ ይህም ሥጋውንና መለኮቱን ፈጸሞ መነጠል እንደማይቻል የሚያስረዳ ነው፡፡ ፍጹም አንድ ሆነዋል፡፡ እርሱ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ጌታችን የማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስና የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚነጣጥሉት ሁለት አካልና ባሕርይ እንደሚሰጡት ሳይሆን ፍጹም አንድ ሆኖ አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ መባሉን ልብ ልንል ይገባናል፡፡
ድንግል እናቱም የእርሱ የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት እንደሆነች መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ እርሱ ክርስቶስ በሰማይም በምድር ሙሉ ነው ዓለምም በመሃል እጁ የተያዘች ናት፡፡ ስለዚህ በምድር የፈጸመው በሰማይም እንዲሁ ተከናውኖአል፡፡ ይህንን ነው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ሊያስረዳን የፈለገው፡፡  ስለዚህም ከዘመን በላይ ከቦታ ውጪ ሆኖ አሁንም ደሙ ሲያድነን ይገኛል፡፡ እኛም ሐዋርያት በተገኙበት ዘመንና ቦታ ተገኝተን ጌታችን ከቆረሰው ሥጋና ደም እንቀበላለን፡፡ በእርሱም መቅደስ ወደ ሆነው መግባትን አግኝተናል፡፡ ስለሆነም እርሱ በእኛ እኛም በእርሱ እየኖርን ነው፡፡ የመለኮቱ ባሕርይ ተካፋዮችም ሆነናል፡፡  ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ድንቅ የሆነውን የጌታችንን የማዳን ሥራ ታላቅነት በዚህ መልክ ገለጠው፡፡ እናም በማይናወጥ ማንም ሊነቀንቀው በማይችል መሠረት ላይ ታንጸናል እርሱም ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ ከሁሉ በላይ ሆኖ የተባረከ አምላክ ነው እኛም ከእርሱ ጋር ስለሆንን ማንም ሊደርስበት በማይችል ከፍታ ላይ ተቀምጠናል፡፡ መላእክት ይህን አስተውለው ያደንቃሉ፡፡ እኛም ከጌታችን ጋር አንድ ቤተሰብ ሆንን፡፡ ይህ ግሩም ድንቅ የሆነ እርሱ ለእኛ ያለውን ዘለዓለማዊ ፍቅር የገለጠበትና ያረጋገጠበት ነው፡፡

 ኦ ጌታችን ሆይ እንዲህ ታደርግልን ዘንድ እኛ ማን ነን? እኛ በዓመፃ ስናርቅህ አንተ በወጋንህ ጎንህ በኩል ከራስህ ጋር አንድ አደረግኸን፤ ክፉ በዋልንብህ ፈንታ መልካምን በብድራት መለስህልን፣ ይህ ፍቅርህ እንዴት ግረሩምና ከመነገር በላይ ነው ጌታ ሆይ!!!! አቤቱ በልደትህ ባሕርያችንን ገንዘብህ በማድረግ ፍጹም እርቅን አደረግህ፤ በዚህ ፈጽመህ እንደማትጥለን አረጋገጥክልን፡፡ በምንም ውስጥ እንሁን ወደ አንተ መመለሳችንን በትዕግሥት ሆነህ ትጠባበቃለህ፤ ምክንያቱም እጅግ ትወደናለህና፡፡ አቤቱ እባከህ ይህን ማስተዋል ከእኔ አታርቀው በዚህ ማስተዋል ውስጥ በመሆን ድንቅና ለእኛ የሆነውን ፍቅርህን አጣጥም ዘንድ ፍቀድ እንጂ ወደ ዓለሙ አትመልሰኝ ምክንያቱም ፈጽሞ የተናቀና የማይጠቅም ነውና፡፡ አቤቱ ፈጣሪዬ ሆይ ለአንተ ክብር ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትር ለዘለዓለሙ አሜን!!!

No comments:

Post a Comment