Wednesday, February 15, 2012

“እኔ በእርሱ እኔነት ውስጥ”



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
08/06/2004
ይገርማል!! እኔ እምላትን አካል የሥጋዬን ታኽል እንኳ ባለማወቄ ይደንቀኛል፡፡ እኛ  ቅዱስ ጳውሎስ “ዛሬስ በመስታወት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን” (1ቆሮ.13፡12) እንዳለው ያህል እንኳ ያላየናት እኔ የምንላት መንፈሳዊት ረቂቅ አካል  አለችን ፡፡ ነፍሴ ምን እንደምትመስል እንደማላቃት እንዲሁ እኔ የምላት አካሌን አለማወቄ እንዴት የሚያሳፍር ነገር ነው ጃል!! ነገር ግን እኔ ያመጣሁት ሳይሆን እግዚአብሔር አምላክ በድንቅ ቸርነቱ ከእኔ የሰወራት ናት፡፡ በዚህ ምድር በቅድስና ለመኖር ከተጋሁ በመንፈስ ቅዱስ መነጽርነት ልክ መላእክትን እንደማየት ላያትና ቅዱስ ጳውሎስ “በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን ዛሬ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደታወቅሁ አውቃለሁ”(1ቆሮ.13፡12) እንዳለው አያታለሁ!!
እኛ በቅድስና የተጋን እንደሆነ በዚህ ምድር ሳለን እንደ ቅዱስ ጳውሎስ እኔነታችንን በድንግዝግዝታ ልንመለከታት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ካልተጋን ልክ እንደባለ ጠጋው ነዌ በሲኦል ሳለን ማየታችን አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ እውቀቶች የተለያዩ እውቀቶች ናቸው፡፡ በቅድስና ተግተን በመኖራችን እኔነታችንን ማወቃችን ለእኛ ለክብር ሲሆን ላልተጉቱ ግን ለኩነኔ ነው፡፡ እነርሱ በዚያን ጊዜ የሚመለከቱት እኔ የሚሉዋት ረቅቅ አካላቸው ሰይጣንን መስላ ነው፡፡ እኛ ግን እኔነታችንን የምናገኛት ክብር ይግባውና ክርስቶስን መስላ ነው፡፡


 ተመልከቱ በምድር ሳሉ በጽድቅ የተጉ ማንን እንደሚመስሉ ራሱ ክርስቶስ ቅዱስ ጳውሎስ ገና ወደ ክርስትና ሳይመለስ በፊት በደማስቆ ሰማይ ላይ ገልጦለት ነበር፡፡ “ሳውል ሳውል ሆይ ስለምን ታሳድደኛለህ?” አለው፡፡ የሚሰደዱት በምድር የነበሩት ክርስቲያኖች ናቸው፤ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጳውሎስን ስለምን ታሳድደኛለህ? አለው፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው? ምክንያቱማ የእነዚህ እኔነታቸው በክርስቶስ ውስጥ ስለነበረች ነው፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች “ሞታችኋልና ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና ሕይወታችሁ የሆነው ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ”(ቆላ.3፡3-4)ብሎ ተናገረ፡፡
 በጽድቅ የተጉ ቅዱስ ጳውሎስ ያሳድዳቸው የነበሩት ክርስቲያኖች እኔነት በላይ በሰማይ በክርስቶስ ውስጥ ሆኖ ተገለጦ ታየ፡፡ እኔም እርሱን የምመስልባትን እኔነቴን በእርሱ እኔነት ውስጥ ያገኘዋት እንደሆነ ፈጽሞ እንደማቃትና እጅግ ደስ እንደሚለኝ እረዳለሁ፡፡ ችግሩ ግን በእርሱ እኔነት ውስጥ እኔነቴ ሕያው ሆና እንድትቆይ በጽድቅ ያልተጋሁ እንደሆነ ነው፡፡ እኔነታችንን በክብር እንድናያት ከፈለግን ትጋት ከእኛ እንደሚጠበቅ ነገር ግን ለዚህ እንድንበቃ የሚያስችለን ኃይልን ስላገኘን ከተጋን በክብር እኔነታችንን እንደምናያት ቅዱስ ጳውሎስ ሲገልጥልን “... በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና፡፡ በዚያ ውስጥ በእውነት እንቃትታለን፡፡... በእውነት የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለሆነ በድንኳን ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን፡፡ ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱ የመንፈሱን መያዣ ሰጠን” ብሎናል፡፡(2ቆሮ.5፡4)
 ፍቅር የሆነው እግዚአብሔር ለነቢዩ ሙሴ በኮሬብ በዕፀ ጳጦስ ውስጥ በእሳት ሐመልማል በተገለጠለት ጊዜ “ያለና የሚኖር እኔ ነኝ”(ዘጸአ.3:14)ብሎ ስለእርሱ እኔነት ገለጠልን፡፡ እርሱ የራሱን እኔነት ጠንቅቆ ያውቃታል፡፡ እኛም በእርሱ ተፈጥረናልና የራስ ጠጉራችን እንኳ በእርሱ ዘንድ የተቆጠረች ናት፡፡ ታዲያ እኛ በእርሱ ስንሆን ማለትም “እኛስ የክርስቶስ ልብ አለን” እንዲል  የክርስቶስ ልብ በሆነው መንፈስ ቅዱስ ታግዘን እንዴት ለዘመናት ተሰውራ የኖረችውን እኔነታችንን ምንጥር አድርገን አናያት? በተሟላ መልኩ እናያታለን፡፡
 ነገር ግን አንዳንዶቻችን ምነው እግዚአብሔር አምላክ እኔነታችንን እንዳናቃት አድረጎ በዚህ ምድር ዕውር ድንብራችንን እንድንመላለስ አደረገን? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡ አዎን! በእርግጥ አምላክ እኔነታችንን በጥረት እንድናገኛት ፈቃዱ ስለሆነ ከእኛ ሰውሯታል፡፡ ይሁን እንጂ በምድር እያለን እንዳናያት አልከለከለንም፤ እንዳውም እንዴት እኔነታችንን መመልከት እንደምንችል እርሱ ራሱ ሰው በመሆን አሳይቶናል፡፡ እርሱም ለእኛ ረቂቅ የሆነውን መንፈሳዊ ዐይንን በጥምቀት ሰጠን፡፡ዐይናችንም ይክበር ይመስገንና እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በእርሱም ዐይንነት ታግዘን እኔነታችንን እንመለከታታለን፡፡
 ተመልከቱ በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር በሞቱና በትንሣኤው ከተባበርንነና እርሱ በሰጠን የሕይወት ዘመናችን ለጽድቅ ሕይወት ከተጋን በመንፈሱ አይደለም እኔነታችንን ለሰው ሁሉ የተሰወሩትን ምሥጢራትን እንመለከትበታለን፡፡ ይህም  ምልከታ ቅዱስ ጳውሎስ "እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ ... ወደ ገነት ተነጠቀ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ፡፡" እንዳለው ዓይነት ምልከታ ነው፡፡(2ቆሮ.12፡2-6) ስለዚህም በሞት ወደ ክርስቶስ  መሄድ ለእኛ የሚናፍቀን እንጂ የሚያስከፋን አይሆንብንም፡፡ እንዲያም ስለሆነ በዚህ ምድር እንግደላችሁ በሚሉን ሰዎች  ላይ እንሳለቅባቸዋለን፡፡ ምክንያቱም እኔነታችን ከክርስቶስ ጋር በአብ ቀኝ ተቀምጣለችና፡፡ሕይወታችን ከእርሱ ጋር በሰማይ ተሰውራለችና፡፡ ከእርሱ እጅ ማንም ፈልቅቆ ሊነጥቀን የሚቻለው የለም፡፡ ይህን አስመልክቶ እርሱ ራሱ “እኔም የዘለዓለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ ለዘለዓለምም አይጠፉም ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም” ብሎናል፡፡ ያኔ የነፍስ ዐይኖቼ ጠርተው እኔነቴን ልክ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ በአብ ቀኝ ቆሞ ካለው ክርስቶስ ጋር ሳያት እንደ ቅዱስ ዳዊት ቸር ፈጣሪዬን “አቤቱ ኩላሊቴን ፈጥረሃልና(በመንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ሰጥኸኛልና) በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛልና(በጥምቀት) ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና(አንተን መስዬ ዳግም በአንተ ተፈጥሬአለሁና) አመሰግንሃለሁ” እለዋለሁ፡፡(መዝ.138/39፡13-14) ፍቅር የሆነው አምላክ ሁላችንንም እኔነታችንን በክብር ለማየት የበቃን ያድርገን ለዘለዓለሙ አሜን!!!

1 comment:

  1. kale hiwot yasemaln tsegawn yabzalh amlake kdusan !!!

    ReplyDelete