ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
10/05/2004
ቅዱስ ኤፍሬም ጥምቀትን ነቢዩ ኤርምያስን በተሸከመች ማኅፀን መስሎ
ሲያስተምር “ነቢዩ
ኤርምያስ ገና ከእናቱ ማኅፀን ሳለ ተቀደሰ ተማረም፡፡ ደካማ የሆነችው ማኅፀን የፀነሰችውን ቀድሳ የወለደች ከሆነ እንዴት ጥምቀት ከእርሷ
ማኅፀን የተፀነሱትን ይበልጥ ቀድሳና አስተምራ አትወልድ! ጥምቀት ተጠማቅያንን ንጹሐንና መንፈሳውያን አድርጋ ትወልዳቸዋለች” ይለናል፡፡ ከቅዱሱ አስተምህሮ እንደምንረዳው ገና ከእናታቸው ማኅፀን ሕፃናት ፈጣሪያቸውን እንደሚያቁና እንደሚለዩ
ነው፡፡ ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ዳዊት "ኃጥአን ከማኅፀን ጀምረው ተለዩ ከሆድም ጀምረው ሳቱ፤ ሐሰትንም ተናገሩ"ይለናል(መዘዝ.56፡3) ቅዱስ ጳውሎስ ስለኤሳውና ስለያዕቆብ ሲናገር “ርብቃ
ደግሞ ከአንዱ አባታችን ከይስሐቅ በፀነሰች ጊዜ ልጆቹ ገና ሳይወለዱ በጎ ወይም ክፉ ምንም ሳያደርጉ ከጠሪው እንጂ ከሥራ ሳይሆን
በምርጫ የሚሆን የእግዚአብሔር አሳብ ይጸና ዘንድ ከእርሱዋ ፡- ታላቁ ለታናሹ ይገዛል
ተባለላት፡፡ ያዕቆብን ወደድሁ ኤሳውን ጠላሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው”(ሮሜ.9፡10) ብሎ ጻፈልን፡፡
በእርግጥ እነዚህ ሕፃናት ከእናታቸው ማኅፀን ነበሩና
በዚህች ምድር ተወልደው ክፉም ደግም አላደረጉም፡፡ ነገር ግን በማኅፀን አይደለም፡፡ያለበለዚያማ እግዚአብሔር አድሎአዊ ነው ልንል
ነው፡፡ ምክንያቱም ገና ክፉና ደጉንም ሳያደርጉ አንዱን በመውደዱና አንዱን በመጥላቱ፡፡ ነገር ግን እርሱ እንዲህ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር
የሰውን ልጆች ሁሉ ቅኖችና ንጹሑን አድርጎ ፈጥሮአቸዋል፡፡ ነገር ግን ከእርሱ ጋር መኖርን ከፈቀዱ ከእርሱ ጋር በደስታና በተድላ ይኖራሉ፡፡
እንደ ጠፋው ልጅ ከአንተ ጋር መኖር አንሻም ድርሻችንን ስጠንና እንደ ራሳችን ምርጫ እንኑር ብለን ከጠየቅነው የድርሻችንን ሰጥቶ
ያሰናብተናል፡፡ ውጤቱ ይምረርም ይጣፍጥም እጣ ፈንታችን በእጃችን የተያዘች ናት፡፡ ከፈቀድንና ከታዘዘን እንድናለን ነገር ግን ካልፈቀድንና
ካልታዘዘን ከእርሱ ከአፍቃሪያችን እንለያለን፡፡ ኤሳውና ያዕቆብም ገና ከእናታቸው መኅፀን ሳሉ ለእግዚአብሔር ያላቸው ዝንባሌ ይለያያልና የእግዚአብሔር ምርጫ አንደምርጫቸው ሆነ፡፡
እንዲህ የማንል ከሆነ እንዴት እግዚአብሔርን ፍትሐዊ ነው ልንለው እንችላለን? እንዲህ
ካልሆነ ስለምን መልካም እንዲሆንልን በጎ ሥራን በመሥራት እንደክማለን? የጌታችን የአምላካችን ምርጫማ ሰዎች ሁሉ ይድኑ ዘንድ ነው፡፡
ነገር ግን እርሱ ምርጫችንን ያከብራልና እንደ ፈቃዳችን ይሰጠናል፡፡ ኤሳውና ያዕቆብም እንዲሁ ከማኅፀን ሳሉ ከእግዚአብሔር አምላካቸው
ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት እጣ ፈንታቸውም እንደዚያው ሆነ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክ “ያዕቆብን ወደድኩ ኤሳውን ግን
ጠላሁ” አለ፡፡ ከኤሳው መወለድን አላሻሁም ነገር ግን ከያዕቆብ ዘር እወለዳለሁ ሲለን እንዲህ አለን፡፡ ስለዚህም እነሆ ጌታችን
ከያዕቆብ ወገን ከሆነች ከቅድስት ንጽሕት ድንግል ማርያም ተወለዶ አዳነን፡፡ ክብር ለእርሱ ለወደደን ይሁን፡፡
እንዲህም ስለሆነ ነው እግዚአብሔር አምላክ ስለነቢዩ ኤርምያስ “ከሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ” ማለቱ፡፡(ኤር.1፡5) ገና ሳይፀነስ ፈቃዱ የታወቀው ሌዊ እንኳ ክርስቶስን እንደለየው ቅዱስ ጳውሎስ “አሥራትን የሚያወጣው ሌዊ እንኳ በአብርሃም እጅ አሥራትን ሰጥቶአል መልከ ጼዴቅ በተገኘበት ጊዜ ገና ከአባቱ ወገብ ነበረና”ብሎ መስክሮለታል፡፡(ዕብ.7፡9-10) ስለዚህም ሕፃናት እንግዳ ሆነው የሚኖሩባትን ምድር ሕግና ሥርዐት ባያውቁም ዓለማቸው በሆነች በእናታቸው ማኅፀን ያለው ነገር ያውቃሉ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ኅብረት ምን መምሰል እንዳለበት ጠንቅቀው ይረዱታል፡፡ ነገር ግን በእኛ መተላላፍ ምክንያት ገና ከእናታቸው ማኅፀን ሳሉ የሚያውቁትን አምላክ እንዳናስረሳቸው ከእኛ ከወላጆች ታላቅ የሆነ ሓላፊነት አለብን አበቃሁ፡፡
No comments:
Post a Comment