Thursday, January 19, 2012

“በዓለ ጥምቀት የሙሽሪት ምዕመናን የደስታ ቀን”




ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
10/05/2004
አምላክ ሆይ በነቢዩ ኢሳይያስ “ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል ጻድቅ ባርያዬ በዕውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል ኃጢአታቸውንም ይሸከማል፡፡”(ኢሳ.53፡11) ተብሎ አስቀድሞ የተናገረው እውን ሆኖ ዛሬ በዐይናችን ተመለከትነው፡፡ ጌታ ሆይ! በሕማምህ ወለድከን፤ በጥምቀትም ከሞትህ ጋር በመተባበር በመንፈስና በእሳት በመጠመቅ እሳታውያንና መንፈሳውያን የሆኑ መላእክትን መሰልናቸው፡፡ ስለዚህም በእደ ዮሐንስ በባሕረ ዮርዳኖስ በመጠመቅ ለእኛ ጥምቀትን የመሠረትክባት ይህቺን ዕለት በታላቅ መንፈሳዊ ደስታና ፍቅር እንዲሁም በታላቅ ተመስጦ ሆነን እናከብራታለን፡፡
ጌታ ሆይ ልጆችህ ልዩ ልዩ ሕብረ ቀላማት ባላቸው አልባሳት አጊጠውና ደምቀው ቅዱስ ሥጋህንና ክቡር ደምህን ከተቀበሉበት ማዕድህ፣ አምሳለ መስቀል ከሆነው ከምሕረት ቃል ኪዳን ታቦትህ ፊት ሆነው፣ በሐዋርያት ለአንተ ለሰማያዊው ሙሽራ የታጩበትን  ቀን ነፍስን በሐሴት በሚሞላ መንፈሳዊ ዝማሬና በታላቅ ደስታ ሆነው ሲያከብሩ ከላይ ከአርዓም ተመልከት፡፡

 ሚስት የሰርጉዋን ቀን ፈጽማ እንደማትረሳ አባቶቻችን ሐዋርያትም ይህቺን ዕለት ፈጽመው አይረሷትም፡፡ ምክንያቱም ለሰማያዊው ሙሽራ ክርስቶስ ሚዜው በሆነው በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በባሕረ ዮርዳኖስ ለጌታ ለዘለዓለም የታጩበት ዕለት ናትና፡፡ ይህቺ ዕለት ለመጥምቁ ዮሐንስም ታላቅ የደስታ ቀን ናት፤ ምክንያቱም ከማኅፀን በመንፈስ ቅዱስ ያወቀውን ጌታ በአካል በማግኘቱና ሐዋርያትን ለእርሱ ለሰማያዊው ሙሽራ በማጨት በእጁ ያስረከበበት ዕለት ናትና፡፡ እነርሱም በተራቸው እኛ የአንተ እንሆን ዘንድ ለአንተ አጩን፡፡ አስቀድመን ግን በመተላለፋችን ልክ እንደ እስራኤላዊቱ ድንግል በደም ተለውሰንና ረክሰን ለሰይጣንና ለፈቀዱ ተገዝተን ተጥለንና ተረስተን ነበር፡፡(ሕዝ.16፡6-14) አንተ ግን በደምህ ተቤዥኸን፣ በማየ ገቦህ ቀድሰህ ከመላእክት ኅብረት ደመርከን፡፡ ስለዚህ መጥምቁ ዮሐንስ በደስታ ሆኖ “ሙሽራዊቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፡፡ ቆሞ የሚሰማው ሜዜው ግን በሙሽራው ድምፅ እጅግ ደስ ይለዋል” አለ፡፡ እርሱ እንዲህ ደስ ካለው ከእርሱ ይልቅ ለሰማያዊው ሙሽራው በጥምቀት የታጨነው እኛ እንዴት አብልጠን ደስ አይለን?
 ከእንግዲህ እኛ በደምህ ተረጭተን በማየ ገቦህ ተቀድሰን የአካልህ ሕዋሳት ሆነናል፡፡ ከዚህ የበለጠ ምን ደስታ አለ? ጌታ ሆይ አሁን አንተ በሠራህልን ጥምቀት የአንተ ቅርንጫፎች ሆነናል፡፡ ስለዚህም ካለ እኔ ምንም ልታፈሩ አትችሉም ብለህ አስተምረኸናልና ከፈቃድህ ርቀን፣ በራሳችን ማስተዋል ተደግፈን፣ አንተን በማሳዘን በገዛ ክፉ ምግባራችን ከአንተ ተቆርጠን እንዳንጣል ማስተዋልንና አንተን መፍራትን ስጠን ዘወትር ፈቃድህን ለመፈጸም አትጋን ለዘለዓለሙ አሜን!!

1 comment:

  1. AMEN!!!LUEULU EGIZIABIHARI HOYI ZEWETIRI YIHIN YEMDANI KENI BEAYIN HILINACHI EYASEBIN BEFKAD GIBIRACHI EYFESIMIN KANITEGA LIZELALEMI LEMINORI ERIDANI

    ReplyDelete