Wednesday, January 25, 2012

በእውን እግዚአብሔር በሰዎች ልጆች ላይ ፍትሐዊ ነውን?(ቅዱስ ይስሐቅ)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
17/05/2004
 ስለእግዚአብሔር ብሎ ማጣትን በፍጹም ፈቃደኝነትና ደስታ የተቀበለ ሰው እርሱ በውስጡ ንጹሕ የሆነ ሰው ነው፡፡ የሰውን ስህተት የማይመለከት እርሱ በእውነት አርነት የወጣ ሰው ነው፡፡ ከሰው በሚቀርብለት ክብር ያልተደሰተ እርሱንም በማያከብሩት ያልተከፋ ሰው እርሱ ለዚህ ዓለምና ለምድራዊ አኗኗር የሞተ ሰው ነው ፡፡ ማስተዋል ለሰዎች ከተሠሩላቸው ሕግጋት ሁሉ እጅግ የላቀና በየትኛውም ደረጃ እና መመዘኛ ሥራን በአግባቡ ለማከናወን ዓይነተኛ መሣሪያ ነው ፡፡ ኃጢአተኛውን አትጥላው እኛ ሁላችን የኃጢአትን ሸክም የተሸከምን በደለኞች ነንና ፡፡
 ስለ እግዚአብሔር ብለህ እርሱን ለመቃወም ከተነሣህ ግን ስለ እርሱ አልቅስለት ፡፡ ስለምን እርሱን ትጠላዋለህ? ኃጢአቱን ጥላ  ስለእርሱም መመለስ ጸልይለት ፡፡ እንዲህ በማድረግ በኃጢአተኞች ላይ ያለተቆጣውን ነገር ግን ስለእነርሱ መዳን የጸለየውን ክርስቶስን ምሰለው፡፡ ስለኢየሩሳሌም መጥፋት እንዴት እንዳለቀሰ አትመለከትምን ? በብዙ ድክመቶቻችን የተነሣ ሰይጣን በእኛ ላይ ያፌዝብናል ፡፡ በእኛ ላይ በሚያፌዘው ሰይጣን የሚፌዝበትን ወንድማችንን ስለምን እንጠላዋለን? ሰው ሆይ ስለምን እንዲህ ይሆናል ? ኃጢአተኛን መጥላት ትፈልጋለህ እርሱ እንዳንተ ጻድቅ መሆን ይሣነዋልን ? ፍቅር ሳይኖርህ የአንተ ቅድስና ምን ይጠቅምሃል ? ስለእርሱ ስለምን አታነባም ? ነገር ግን አንተ እርሱን ታሳድደዋለህ ፡፡ አንዳንዶች በኃጥአን ላይ ባለማስተዋል በቁጣ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የኃጢአተኞችንም ሥራ ለይተው የሚያውቁ አድርገው በራሳቸው  ይታመናሉ፡፡

ስለዚህም ስለእግዚአብሔር አምላክ መሐሪት አዋጅ ነገሪ ሁን፡፡ ምንም እንኳ አንተ ለእርሱ የተገባህ ሆነህ ባትገኝም እግዚአብሔር ገዢህ ነው፡፡ አንተ የምትከፍለው እዳ እጅግ የበዛ ቢሆንም እርሱ ግን ያለብህን እዳ ትከፍለው ዘንድ አላስገደደህም ፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው አንተ ለሠራኸው ጥቂት በጎ ሥራ ታላቅ ዋጋን ከፈለህ፡፡
እግዚአብሔርን ፍትሐዊ ነው ብለህ አትጥራው፡፡ አንተን በተመለከተ የእርሱ ፍትሐዊነት አልታየምና ፡፡ምንም እንኳ ነቢዩ ዳዊት “እግዚአብሔር ዓለምን በጽድቅ ይፈርዳታል”(መዝ.፱፥፰) ቢልም ልጁ ግን እርሱ ቸርና ርኅሩኅ እንደሆነ ለእኛ ገለጠልን፡፡ “እርሱ ለማያመሰግኑት ለክፉዎችም ቸር ነው” አለን፡፡( ሉቃ.፮፥፴፭)እግዚአብሔር በወይን እርሻው ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለቀጠራቸው ሠራተኞቹ ያደረገውን ተመልክተህ እርሱን እንዴት ፍትሐዊ ነው ብለህ ልትጠራው ትችላለህ ? ምክንያቱም “ወዳጄ ሆይ አልበደልሁህም በአንድ ዲናር አልተስማማኸኝምን ? ድርሻህን ውሰድና ሂድ እኔ ለዚህ ለኋለኛው እንደ አንተ ልሰጠው እወዳለሁ በገንዘቤ የወደድኩትን አደርግ ዘንድ መብት የለኝምን ? ወይስ እኔ መልካም ስለሆነሁ ዓይንህ ምቀኛ ናትን ? ይላልና ፡፡(ማቴ.፳፥፲፪-፲፭)
እግዚአብሔር ፍትሐዊ ነው የሚለው ሰው ማን ነው? ገንዘቡን በአመፃ አኗኗር አጥፍቶ የመጣውን የጠፋውን ታሪክ ስንመለከትና ምንም እንኳ ስለፈጸመው ኃጢአት ቢያዝንም ወደ እርሱ በመሮጥ አንገቱን አቅፎ በመሳም በሀብቱ ሁሉ ላይ ባለሥልጣን አላደረገውምን ?(ሉቃ. ፲፭፥፲፩) እኛ እንዳንጠራጠርም ከልጁ በቀር ሌላ ማንም ስለእርሱ መሐሪነት አልነገረንም ፡፡ ልጁ ራሱ እነዚህን ነገረን እንጂ ፡፡ ስለእርሱ ምስክሩ  የባሕርይ ልጁ ነው ፡፡
 የቱ ጋር ነው ታዲያ የእግዚአብሔር ፍትሐዊነቱ ? እኛ ኃጢአተኞች ሳለን እርሱ ስለእኛ ሞተ(ሮሜ.፭፥፰)በዚህ ቦታ እግዚአብሔር መሐሪ መሆኑን ካመንን መሐሪነቱ እንደማይለወጥ እንዲሁ እናልምናለን፡፡ የእግዚአብሔር ባሕርይ እንደ ሰው ተለዋዋጭ አይደለምና ኃጢአተኛ ለሆነው ሰው እግዚአብሔር ምሕረት የለሽ ይሆናል ብሎ ማሰብ ከእኛ ይራቅ፡፡ እግዚአብሔር እርሱ የሌለውን ከሌላ የሚያሟላ ፣ወይም ኖሮት ያጣው ወይም የጠፋበትን በሌላ የሚተካ ፍጡር አይደለም፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ቄርሎስ ዘፍጥረትን በተረጎመበት መጽሐፉ እንዳለው ለእግዚአብሔር አስቀድሞ የነበረው ለእርሱ የሆነና ወደፊትም የእርሱ ሆኖ የሚኖር ነው፡፡ እርሱን ከማፍቀር በመነጨ ፍርሃት እግዚአብሔርን ፍራው፡፡ ለእርሱ የተሰጠው ስም ፍርሃትን የሚያመጣ ስም አይደለም፡፡ ማፍቀር እንደሚገባህ ሆነህ አፍቅረው ፤ እርሱ በዓለም ፍጻሜ የሚሰጥህን መልካም ነገር አስበህ ግን አይሁን፡፡ ነገር ግን እኛ እንኖርባት ዘንድ ፈጥሮ ስለሰጠንም ስለዚህች ምድር ፣ በእርሱዋ ለእኛ የሰጠንን ቸር ስጦታን አስበን አናፍቅረው ፡፡
እርሱ ስለሰጠው ስጦታ ብድራትን ሊከፍለው የሚችል ሰው ማን ነው ? እንደ ሥራችን ከእርሱ ዘንድ ብድራቱን የምንቀበለው የት ነው ? እኛን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ይፈጥረን ዘንድ ያማከረውስ ሰው ማን ነው ? እኛ ሳንፈጠርን ፣ ማስተዋሉም ሳይሰጠን በፊት በእርሱ ፊት እኛን ይፈጥረን ዘንድ የማለደው ማን ነው ? ለዘለዓለማዊ ሕይወት ይህን ሥጋችንን ካንቀላፋበት የሚያነሣውስ ማን ነው ?
 ትቢያ ከሆነው ሰውነት ውስጥ የማሰብ ችሎታን ያኖረውስ መቼ ነው ? እግዚአብሔር ለእኛ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር እንዴት ታላቅ ነው !! የአምላካችንና የፈጣሪያችን ቸር ስጦታ እንዴት ንቅ ነው ! ሁሉን በቀላሉ የሚከውን ኃይሉ እንዴት ብርቱ ነው ! እኛን በአዲስ ተፈጥሮ እንደገና የፈጠረን እርሱ ለእኛ ያለው ወሰን አልባ ፍቅሩ እንዴት ግሩም ነው !!
 እኛ ምንም ኃጢአተኞች ብንሆን እርሱን በሚመስል ልደት ወለደን ፡፡ ወደ እርሱ ዕረፍትም አገባን ፡፡ እርሱን ፈጽሞ ማመስገን የሚበቃ ሰው ማን ነው ? እርሱ በኃጢአት የተላለፉትንና በእርሱ ላይ የስድብን ቃል ያወጡትን በፍቅሩ ስቦ በንስሐ አጥቦ መለሳቸው ፣አከበራቸው በቸርነቱም የእርሱ መንጎች አደረጋቸው ፡፡
 ምድራዊውን ሰውነታችንን አድሶ እንደው በከንቱ እንደ አፈር ተበታትኖ ከነበረው ስሜት አልባ ተፈጥሮ የሚያስብ ሰውን ፈጠረ ፡፡ ኃጥአን የእርሱን የትንሣኤው ምሥጢር ፈጽመው መረዳት አይችሉም ፡፡
እኛን በእሳት የምትቀጣን አንተንም ባሰብን ቁጥር ሁሌም ስጋት ውስጥ የምትጥለን ሞት ሆይ! በእግዚአብሔር ፍቅር በጠፋህ ጊዜ ድል መንሣትህ ወዴት አለ ? እኛን ከሶኦል አውጥቶ ፈራሽ የሆነውን ተፈጥሮአችንን የማይፈርስና እሳታዊ አድርጎ በመለወጥ ከመቃብር ተጥሎ የነበረውን ማንነታችንን በክብር ከሚያስነሣው ከትንሣኤው ክብር ጋር ሲነጻጸር ሲኦል ሆይ ማስደንገጥህ ወዴት አለ ?
እናንተ የማታስተውሉ ኑና የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ተመልከቱ ! ፈጣሪያችን ማስተዋልን ጥበብ የተሞላ ፣ ተአምራቱም አጅግ ድንቆች አይደሉምን? ለኃጥአንም በብድራት የመለሰው ፍትሐዊ ፍርድ ሳይሆን ትንሣኤውን አይደለምን? በምድራዊ ሰውነታቸው ምድርን ለአበላሹአት ሰዎች በብድራት የመለሰላቸው የጸጋውን ልብስ አይደለምን? እርሱንም በትንሣኤ እርሱን ደርበው የማይፈረስ ሰውነትን ለብሰው ይታያሉ፡፡ በኃጢአት ዘወትር ለምናሳዝነው ሰዎች በትንሣኤው የሰጠን ክብር ካለመኖር ወደ መኖር በመምጣት ከፈጠርንበት ክብር ይልቅ በእጅጉ የላቀ ነው ፡፡ ስለማይመጠ የጸጋ ስጦታህ ጌታ ሆይ ለአንተ ክብር ይሁን ፡፡
ጌታ ሆይ እንደ ማዕበል ወጀብ የሆነውን ስጦታዎችህን በተመለከትኩ ጊዜ አንደበቴ በመገረም ተሞላ ፡፡ ስለዚህ አንተን ከማመስገን ውጭ ከአንደበቴ ምንም ምን አይወጣም ፡፡ የእኛን በሕይወት መኖር የምትወድ ቸሩ ንጉሣችን ሆይ ለአንተ ምስጋናን ማቅረብ የሚቻለው  ምን አንደበት ነው ? በእነርሱ ውስጥ ደስ ይለንና እናድግባቸው ዘንድ ሁለት ዓለማትን የፈጠርክልን ጌታ ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን ፡፡ አንተ በፈጠርክልን ፍጥረታት በኩል ወደ ክብርህ እውቀት እንደርስ ዘንድ ምራን ከአሁኑዋ ሰዓት ጀምሮ እስከዘለዓለሙ ድረስ  ይሁን አሜን!!”




1 comment:

  1. Amen Egziabher ye agelgilot zemenihin yabzalih, yibarkilih....cherinetun ke ene yalaraqe Egziabher amlak Yetemesgene Yehun.

    ReplyDelete