Tuesday, June 5, 2012

"አባታችን ሆይ" በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የመጨረሻው ክፍል


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
29/09/2004
...እርሱ ንጉሣችን ከሆነ ማን ያስፈራናል? ጌትነቱን ማንም ሊቃወምና ሊያጠፋ የሚቻለው የለም ፡፡ አርሱ  “መንግሥት የአንተ ናትና” ሲለን እኛን የሚዋጋውን ለጊዜ እግዚአብሔርን የሚቋቋም የሚመስለውን ሰይጣንን ለእኛ እንዲገዛ አሳልፎ እንደሚሰጠን ሲያመላክተን ነው ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እርሱ ከእግዚአብሔር ባሪያዎች አንዱ ነው ፤ ምንም እንኳ ከተዋረዱትና ለመተላለፋችን ምክንያት ከሆኑት ወገኖች ዋናው ቢሆንም ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፈቃድ ካለገኘ በቀር በእግዚአብሔር ባሮች ላይ የማደር መብቱ የለውም፡፡ ስለምን  እኔ “ በባሮቹ ላይ” እላለሁ ፣ በእሪያዎች ላይ እንኳ በማደር እነርሱን አስቻኩሎና አጣድፎ ለማጥፋት ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፈቃድን መቀበል የግድ አለበት (ማቴ.፯፥፲፬) በእንስሳት መንጋ ላይ እርሱ ካለፈቀደለት በቀር ከቶ ሊያድር ካልቻለ በሰው ልጆች ላይ እርሱ እግዚአብሔር ካልፈቀደ በቀር እንዴት ሊያድር ይችላል?


“ኃይል” አለ ፡፡ ስለዚህም ድክመቶችህ እጅግ ብዙ ቢሆኑም ያለሥጋት በድፍረት ለመቆም እንድትችል ሁሉን በቀላሉ መፈጸም  የሚቻለው እርሱ በአንተ ላይ መንገሡን አሳወቀህ ፡፡ በአንተም ሥራውን መከወን ለእርሱ አይሳነውም  ፡፡
“ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን”  በዚህ ወደ አንተ ከቀረቡ መከራዎች ሁሉ ነጻ ሊያወጣህ እንደሚችል ብቻ አልገለጸልህም ፡፡ ነገር ግን አንተን ማክበርና ማላቅ እንደሚቻለው አሳወቀህ ፡፡ የእርሱ ኃይል እጅግ ታላቅ እንደመሆኑ መጠን እንዲሁ ክብሩም እንዲሁ በቃላት ሊገለጽ የማይችል እጅግ ታላቅ ነው ፡፡ ለእርሱ የሆኑ ጸጋዎች ሁሉ ወሰን አልባና ፍጻሜ የሌላቸው ናቸው ፡፡  እርሱ ኃይሉ ታላቅ ክብሩም በቃላት ሊነገር የማይችልና ፍጻሜ የሌላቸው ናቸው ፡፡ ድል አድራጊው እርሱ የእርሱ የሆኑትን እንዴት ባለ ክብር እንደሚያከብራቸውና በእርሱ ታምነውነና ተደግፈው እንዴት እንዲኖሩ ታስተውላለህን?
ስለዚህም አስቀድሜ  ለማብራራት እንደሞከርኩት በእርሱ ዘንድ  የተጠላውንና የማይወደደውን ቂምና ጥላቻን ከልባችን አስወግደን  ከንቱዎች ከሆኑት ከእነዚህ  ክፉ ጠባያት ርቀን በሁሉ ዘንድ መልካም የሆነውን መፈጸም እንዲገባን አበክሮ ሊያሳስበንና እንዴት መጸለይ እንዲገባን ካስተማረን በኋላ በድጋሜ መልካም የሆነው ምግባር ምን እንደሆነ ያስታውሰናል ፡፡ ስለዚህም ይህን ብንፈጽም በእኛ ላይ የሚመጣብንን ቅጣት ማስቀረት እንደምንችል ያሳስበናል፡፡
“ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ” ካለ በኋላ “የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና ፣ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ አባታችሁም ይቅር አይላችሁም” (ማቴ.፮፥፲፬) አለን ፡፡
በዚህም ኃይለ ቃል “ሰማይ” እና “አባት” የሚለውን ቃል በድጋሚ መጠቀሙን እናስተውላለን ፡፡ ይህም ሰሚዎቹ ትሕትናን ገንዘባቸው እንዲያደርጉ ለመርዳት ነው ፡፡ በዚህ ቃል አስቀድመው እንደ አውሬ በከፋ ምግባር ይመላለስ የነበረው ሕዝብ እርሱን የመሰለ አባት ማግኘቱንና ከተራና ከተናቀ ምድራዊ አስተሳሰብ አውጥቶ በሰማያት መኖሪያውን እንዳደረገለት ሊያሳየው እንዲህ አለው ፡፡ ይህ ሲፈጽምልን በጸጋው እኛም የእርሱ ልጆች እንባል ዘንድ ከእኛም በጎ ምግባር እንደሚያስፈልግ ሲያስታውሰን አይደለምን?  እግዚአብሔርን ለመምሰል የበደሉንን ይቅር ከማለት በቀር የበለጠ ነገር የለም ፡፡ እርሱም አስቀድሞ “እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣል” በማለት እንደርሱ እኛም መሐሪያን  እንድንሆን መጠራታችንን ማስተዋል እንችላለን፡፡
ይህም እንዲሆን ፈቃዱ እንደሆነ ሊያሳየን በእያንዳንዱዋ ኃይለ ቃል ላይ  “አባታችን ሆይ” “ፈቃድህ በሰማያት እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን” “የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ” “በደላችንን ይቅር በለን” “ ወደፈተና አታግባን” “ከክፉ አድነን እንጂ” በማለት የጋራ ጸሎት እንድንጸልይ አዞናል፡፡ በወንድሞቻችን ላይ እንዳንቆጣና በእነርሱ ላይ በጠብ ከመነሣሣት እንድንቆጠብ ሲል  በእያንዳንዱ የጸሎታችን ክፍል ላይ እነዚህን የብዙ ቁጥር ግሶችን እንድንጠቀም አዞናል ፡፡
ከዚህ ሁሉ ማሳሰቢያ በኋላ የበደሏቸውን ይቅር ከማለት ይልቅ ጠላቶቻቸውን እግዚአብሔር ተበቅሎ እንዲያጠፋላቸው የሚለምኑትን ሰዎች እግዚአብሔር በእጥፍ ሕጉን በመተላለፋቸው እንዴት የባሰ ፍርድን አይፈርድባቸው ይሆን!  እርሱ እግዚአብሔር ሁሉን እንዲህ አስማምቶ መፍጠሩ አንዱን ከአንዱ እንዳለይለያይና በፍቅር ተደጋግፈው እንዲኖሩ በመሻቱ አይደለምን? ለመልካም ነገር ሁሉ ፍቅር መሠረት ነው ፡፡ እርሱ ፍቅርን የሚያፈርሱ ነገሮችን ሁሉ ከያቅጣጫው እንዲወገዱ ያደርጋቸዋል ፡፡ ሁላችንንም ወደ አንድ በማምጣት ፍቅርን እንደሲሚንቶ በመጠቀም እርስ በእርሳችን እንድንያያዝ ፈጠረን ፡፡ 
አባትም ይሁን እናት ጓደኛም ይሁን ሌላ እንደ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር እኛን የሚወደን የለም፡፡ ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ሁሉ እርሱ እግዚአብሔር  በየቀኑ ለእኛ የሚያደርገውን መግቦትና የእርሱን ሥርዐት ወዳድነት አሳይቶናል፡፡ ነገር ግን ስለ ሕመሞቻችሁና ስለሃዘኖቻችሁ እንዲሁም በሕይወታችሁ ዘመን ስለገጠሟችሁ መከራዎች የምትነግሩኝ ከሆነ በየቀኑ እናንተ እርሱን ምን ያህል በክፉ ሥራችሁ እንደምታሳዝኑት ልብ በሉ፡፡ እንዲህ በማድረጋችሁም በደረሰባችሁ መከራ ሁሉ መገረማችሁንና መደነቃችሁን ታቆማላችሁ ፡፡ ነገር ግን በየቀኑ ስለምንፈጽማቸው ኃጢአቶች ምክንያት በእኛ ላይ ስለመጣው ከፉ ነገር ሁሉ ልብ የማንል ከሆነ ግራ መጋባት ውስጥ ልንገባ እንችላለን ፡፡ በቀን ውስጥ ብቻ የምንፈጽማቸውን በደሎች በጥንቃቄ ብንመረምራቸው ስለመተላለፋችን እንዴት ያለ ታላቅ ቅጣት ሊታዘዝብን እንዲገባ መገንዘብ እንችላለን ፡፡              
ስለዚህም በቀን ውስጥ የፈጸምናቸውን በደላችንን በማሰብ  የበደሉንን ይቅር ልንል ይገባናል፡፡... እኛ በጸሎት ቸልተኞች አይደለንምን ? ከእኛ መካከል በትዕቢት ተሞልቶና ከንቱ ውዳሴን ሽቶ የሚጸልይ የለምን ?  ወንድሙን በክፉ የማይናገረው፣ የወንድሙን ውድቀትን የማይመኝ ፣ ወገኑን በንቀት ዐይን የማይመለከተው ፣ግፍ ቢፈጽምበት እንኳ የወንድሙን መተላለፍ ይቅር የሚል አለን ?
ነገር ግን እኛ በቤተክርስቲያን ለአጭር ጊዜ በቆየንባት ሰዓት ውስጥ እጅግ ታላቅ ክፋትን እንፈጽማለን ፡፡ ከቤተክርስቲያን ወጥተን ወደ ቤት ስንመለስ ምን ያህል የከፉ በደሎችን እንፈጽም ይሆን ? በወደቡዋ (በቤተክርስቲያን) ታላቅ የሆነ ወጀብ ካለ ወደ ኃጢአት መተላለፊያው ባሕር ስናመራ ማለትም ወደ ገበያ ሥፍራዎችና ወደ ቤቶቻችን ስናመራ በሥጋ ምቾቶቻችን ተስበን የከፉ ኃጢአቶችን አንፈጽምምን?
ነገር ግን እግዚአብሔር ከእነዚህ ሁሉ መተላለፎቻችን እንድንድን ያለምንም ድካም አጭርና ቀላል መንገድን ሠርቶልናል ፡፡ የበደለንን ይቅር ማለት ምን ዐይነት ድካም ይጠይቃል ?  ነገር ግን እርስ በእርሳችን በጠላትነት ተፋጠን እንገኛለን ፡፡ በውስጣችን ከተቀጣጠለው ቁጣ ለመዳንና መጽናናትን ለማግኘት ፈቃዳችን ብቻ በቂ ነው ፡፡ ይቅርታ ለማድረግ ባሕር ማቋረጥ ፣ ረጅም መንገድ መጓዝ ፣ ወይም ተራራን መቧጠጥ ወይም ብዙ ገንዘብ ማጥፋት ወይም ሥጋችንን ማጎሳቆል አያስፈልገንም ፤ ነገር ግን ፈቃደኛ መሆን ብቻ በቂ ነው ፡፡ እንዲህ ከሆነ ኃጢአታችን ሁሉ አንድ ሳይቀር ይወገድልናል ፡፡
ነገር ግን እርሱን ወንድምህን ይቅር ማለት ትተህ እግዚአብሔር ያጠፋልህ ዘንድ የምትለማመን ከሆነ ምን ዐይነት የመዳን ተስፋ ሊኖርህ ይችላል? አስቀድመህ ከእግዚአብሔር ጋር በፈቃድ አልተስማማህም፤ ከዚህ አልፈህ የጠላትህን ጥፋት በመጠየቅህ ምክንያት እግዚአብሔርን ታስቆጣለህን? እርሱን ትለማመነው ዘንድ የሃዘን ማቅን ደርበሃል፤ ነገር ግን የአውሬ ጩኸት ወደ እርሱ እየጮኽ በኃጥእ ላይ የሚመዘዙትን የጥፋት ፍላፃዎችን በራስ ላይ ታመጣለህን ? ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ስለጸሎት ሥርዐት ባስተማረበት ወቅት ከበቀል ነጽተን ጸሎታችንን ማቅረብ እንዲገባን“… በስፍራ ሁሉ አለ ቁጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን አጆች እያነሡ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ” ብሎ እንዳስተማረው አንተም እንዲሁ ልታደርግ ይገባሃል፡፡ (፩ጢሞ.፪፥፳)አንተ ምሕረትን የምትሻ ከሆነ ከቁጣ መቆጠብ ብቻውን ለአንተ በቂ አይደለም ፤ ነገር ግን ለዚህ ነገርም እጅግ አስተዋይ ልትሆን ይጠበቅብሃል ፡፡
አንተ በራስ ፈቃድ ራስህ ላይ የጥፋት ሰይፍን የምትመዝ መሆንህን ከተረዳህ ለአንተ መሐሪ ከመሆንና የክፋት መርዝ የሆነውን ቁጣ ከሰውነት ከማስወገድ የበለጠ ምን የሚቀልህ ነገር አለ ? ነገር ግን ይቅር ባለማለትህ በአንተ ላይ ሊመጣ የሚችለውን የእግዚአብሔርን ቁጣ ያላስተዋልክ እንደሆነ አንድ ምሳሌ ልስጥህ  ፡፡፡ አንድ ወቅት በሰዎች መካከል ጠብ ይነሣና እርስ በእርሳቸው ክፉኛ ይነቃቀፋሉ  ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ሰው ከአንተ ምሕረትን ያገኝ ዘንድ ከእግርህ ሥር ወድቆ ይለማመንሃል ፡፡ ነገር ግን የእርሱ ጠላት የሆነው መጥቶ አንተን እየተለማመነህ ያለውን ሰው ከወደቀበት ላይ መደብደብ ቢጀምር አንተን ከበደለህ ሰው ይልቅ የሚለማመንህን በሚመታው ሰው ላይ ይበልጥ አትቆጣምን ? እንዲሁ የጠላቱን ጥፋት የሚለምን ሰው እግዚአብሔርን እንዲህ እንዲያስቆጣው ይረዳ ፡፡ አንተም እግዚአብሔርን ስለመተላለፍህ እየተለማመጥከው ሳለ ድንገት ልመናህን ከማሃል አቋርጠህ በቃልህ ጅራፍ ጠላትህን ልትገርፈው ብትጀምር እግዚአብሔር አንተን የሚታገስህ ይመስልሃልን?  ነገር ግን  በዚህ ተግባርህ ቁጣው በአንተ ላይ እንዲቀጣጠል ታነሣሣዋለህ፡፡ ምንድን ነው ? እርሱ ለአንተየሰጠውን ትዕዛዝ ይዘነጋዋልን? እርሱ ሁሉን የሚያውቅ እግዚአብሔር አይደለምን? እርሱ ሕግጋቶቹ ሁሉ በፍጹም ጥንቃቄ ይፈጸሙ ዘንድ የሚሻ እግዚአብሔር ነው ፡፡ ከአንተ እንደሚጠብቀው አድርገህ ሕግጋቶቹን ከመፈጸም ርቀህ እንደፈቃድህ በጥላቻ ሕግጋቶቹን  የምትጥሳቸው ከሆነ እጅግ የከፋ ቅጣን እንደሚጠብቅ በእርግጥ እወቅ፡፡ አጥብቆ ትጠብቀው ዘንድ ያዘዘህን ትእዛዝ ካቃለልክ በኋላ ከእርሱ ዘንድ ምን በጎነትን አገኛለሁ ብለህ ትጠብቃለህ ?
ይህን ባለማስተዋል እጅግ ቆሻሻ ወደ ሆነው ወደዚህ ምግባር የሚመለሱ ወገኖች ግን አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ለጠላቶቻቸው ጥፋትን የሚለምኑ ብቻ አይደሉም ፤ የገዛ ልጆቻቸውን በመርገም የገዛ ሥጋቸውን የሚያጠፉ ወይም ከእርሱ የሚመገቡ ናቸው ፡፡ በጥርሶቼ የልጄን ሥጋ መች በላሁ ብለህ አትንገረኝ ፡፡ ይህንን በእርግጥ አድርገኸዋል ፡፡ ከእግዚአብሔር ቁጣ ወጥቶ በልጅህ ላይ እንዲወድቅና ለዘለዓለማዊ ቅጣት ተላልፎ እንዲሰጥ እንዲሁም ከነቤተሰቡ ተነቃለቅሎ እንዲጠፋ ከመለመን የበለጠ ምን አስከፊ የሆነ ጸሎት አለ ?
ለምን እንዲህ ይሆናል ፡፡ከዚህስ የከፋ ጭካኔ ምን አለ ? እንዲህ በክፋት ተጨማልቀህ በልቡናህ ውስጥ ይህ ክፉ መርዝ አስቀምጠህ እንዴት ከቅዱስ ሥጋው ልትቀበል ትቀርባለህ ? የጌታንስ ማዕድ ስለምን ታክፋፋለህ? አንተ “ሥጋው በሰይፍ ተቆራርጠህ ቤቱንም ገልብጠህ አጥፋው ፣ ያለውን ሁሉ እንዳልነበር አድርገህ ከምድረ ገጽ አስወግደው” ብለህ የምትለምንና እልፍ ጊዜ ሞትን እንዲሞት የምትጸልይ አንተ ሰው ሆይ! አንተ ከነፍሰ ገዳዮች ፈጽሞ የምትለይ አይደለህም ፡፡ ወይም ሰዎችን እንደሚመገብ እንደክፉ አውሬ ነህ ፡፡
ስለዚህ ከዚህ ክፉ ሕመምና እብደት ራሳችንን እንጠብቅ ፡፡ እርሱ እንዳዘዘን እኛን ለሚያሳዝኑን ርኅራኄን በማሳየት “የሰማዩ አባታችንን”  እንምሰለው ፡፡ የገዛ ኃጢአታችንን በማሰብ ከዚህ ክፋት እንመለስ ፡፡ በቤታችንም  ከቤታችንም ውጭ በገበያ ቦታ ፣ በቤተክርስቲያንም የምፈንጽመውን ኃጢአት በጥንቃቄ በመመርመር ከዚህ ክፋት እንራቅ፡፡
ለዚህ ትእዛዝ ተገቢውን ትኩረት ካለመስጠት የተነሣ ካልሆነ በቀር ለከፋ ቅጣት የሚዳርገን ሌላ ትእዛዝ የለም ፡፡ ነቢያት ሲዘምሩ ፣ ሐዋርያት በመንፈሳዊ ቅኔ ሲቀኙ ፣ እግዚአብሔርም ሲያስተምር  እኛ ግን በዓለም ተጣብቀን እንባክናለን ፡፡ ራሳችንን በምድራዊ ነገሮች አሳውረናል ፡፡ በተዋንያን መድረክ ላይ የሚነበበውን የንጉሥ ደብዳቤ ለመስማት በጸጥታ እንድንቆም የእግዚአብሔርን ሕግ በጸጥታ ለመስማት አንተጋም ፡፡  በዚያ የንጉሡ ደብዳቤ ሲነበብ አማካሪዎች፣ ገዢዎች የመንግሥት ልዑካኑና ሕዝቡ ሁሉ ቃሉን ለመስማት  ይቆማል ፡፡ በዚያ ጸጥታ ውስጥ አንድ ሰው ቢንቀሳቀስና ድምጽ ቢያሰማ ንጉሡን እንደናቀ ተቆጥሮበት ከባድ ቅጣትን ይቀበላል ፡፡  በዚህ ቦታ ግን ሰማያዊ ደብዳቤ በተነበበ ጊዜ በሁሉ አቅጣጫ ታላቅ የሆነ ሁከት ይቀሰቀሳል፡፡ ነገር ግን ደብዳቤውን የላከው ንጉሥ ከዚህኛው ምድራዊ ንጉሥ እጅግ የሚልቅ ነበር ፡፡ ታዳሚዎቹም የተከበሩ ናቸው ፡፡ ሰዎች ብቻ አይደሉም የሚገኙበት መላእክት ፣ ሊቃነ መላእክት የሰማይ ሠራዊቶች ሁሉ ይገኙበታል ፡፡ አኛም በምድር ያለነው ምስጋናን እናቀርብ ዘንድ ከጉባኤው ታድመናል ፡፡ “ሥራዎቹ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል” ተብሎ እንደተጻፈ ፡፡ አዎን እርሱ ለእኛ የፈጸማቸው እኛ ከምናስበውና ከምንረዳው በላይ ናቸው ፡፡
ይህን ጉዳይ ነቢያት ሁል ጊዜ የሚያውጁት ነው ፡፡ እያንዳንዳቸው በተለያየ መንገድ ይህን የእግዚአብሔርን ድል አድራጊነት ለእኛ ጽፈውልናል ፡፡ ንጉሥ ዳዊት “ወደ ላይ ዓረግህ ፣ ምርኮን ማረክህ ስጦታህን ለሰዎች ሰጠህ”(መዝ.፷፯፥፲፰) እንዲሁም  “እግዚአብሔር ነው በሰልፍ ኃያል”(መዝ.፳፫፥፰)  ሌላውም ነቢይ “የኃይለኛውን ሙርኮ ይበዘብዛል” ብሎአል ፡፡ የተማረኩትን ከሙርኮ ሊያድን ለእውርን ብርሃንን ሊሰጥ ነው ጌታችን ወደዚህ ምድር መምጣቱ ፡፡
 ሌላው ደግሞ በሞት ላይ ያገኘነውን ድል አሰምቶ በመናገር እንዲህ ይላል “ ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ ?ሞት ሆይ ድል መንሣትህ የታለ ? (ኢሳ.፳፭፥፰) በሌላ ቦታ ደግም ሰላምን ስለሚሰጠን ስለምስራቹ ቃል  ሲመሰክር “ሰይፋቸውንም ማረሻ ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ”(ኢሳ.፬፥፬) ሲል ፤ ሌላኛው ነቢይ ደግሞ  ኢየሩሳሌም እየተጣራ  “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበለሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዪ አነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ፡፡ ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” ብሎ ይሰብካል ፡፡ ( ዘካ.፱፥፱) ሌላኛውም “እናንተ የምትፈልጉት ጌታ ይመጣል ::  በዚያች ቀን በእርሱ ፊት ማን ይቆማል ? በእርሱ ከእስራቶቻችሁ በመፈታታችሁ  እንደ ጥጃ ትዘላላችሁ፡፡” በዚህ ነገር የተደነቀው ሌላ ነቢይም “እርሱ የእኛ ጌታ ነው ከእርሱ ጋር የሚሰተካከል ጌታ ፈጽሞ  የለም” ብሎአል ፡፡
ነገር ግን እነዚህና ከእነዚህም ከጠቀስናቸው በላይ የተነገረለትን የነገሥታት ንጉሥ ቃልን ለመስማት በመንቀጥቀጥ በጸጥታ መቆም ሲገባን በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እንዳለን በመቁጠር እንጮኸለን ፣ እናወካን ፡፡ ሰላማዊ የሆነውን ጉባኤችንን ሁል ጊዜ ምንም በማይጠቅሙ ንግግሮች ስንረብሸው እንገኛለን ፡፡
ስለዚህ በትንሹም ፣ በትልቁም ጉዳይ ፤ በመስማትም ፣ በመሥራትም በውጭም ይሁን ፣ በቤታችን እንዲሁም በቤተክርስቲያን እጅግ ቸልተኞች ሆነናል ፡፡ እነዚህ ክፋቶቻችንን እንደያዝን የጠላቶቻችንን ነፍስ በመለመን ከባድ ኃጢአትን በራሳችን ላይ እንጨምራለን ፡፡  ከዚህ ኃጢአታችን ጋር የሚስተካከል ምን ኃጢአት አለ ? በዚህ ባልተገባ ጸሎታችን ምክንያት ለእኛ ስለመዳን የሚቀርልን ምን ተስፋ አለን ?
 ከእኛ የማይጠበቅ ሥራን እየሠራን በእኛ ላይ በደረሰው ውድቀትና ሕመም ልንደነቅ ይገባናልን ?  ልንደነቅ የሚገባን እነዚህ በእኛ ላይ ባይመጡብን ነው ፡፡ የመጀመሪያው ተፈጥሮአዊ ከሆነው ባሕርያችን መንጭቶ ነው ፡፡ ለሁለተኛው ለበደላችን ግን ምንም ምክንያት የምናቀርብለት አይደልም ፡፡ ለፍጥረት ሁሉ ፀሐይን በሚያወጣውና ዝናብን በሚሰጠው እንዲሁም ሌሎችንም በጎ ሥጦታዎችን በሚሰጠን በእግዚአብሔር ላይ በጠላትነት መነሣትና እርሱን በቁጣ ተሞልቶ መናገር ፣ ምንም ምክንያት ልናቀርብለት የማንችልበት በደላችን ነው ፡፡ ከቆረቡና እጅግ ታላቅ የሆነውን ጸጋ ተቀብለው ካበቁ በኋላ ፣ ከአውሬ ይልቅ ከፍተው ፣ እርስ በእርሳቸው በጠላትነት ተፋጥጠው የሚኖሩና ጎረቤቶቻቸውን  በምላሳቸው እያቆሰሉና አፋችን በእነርሱ ደም እያራሱ በቁጥር እጅግ የከፋ ቅጣት ለራሳቸው የሚያከማቹ አሉ ፡፡
ስለዚህም ይህን መተላለፋችንን አስበን ይህን ክፉ መርዝ ከውስጣችን አስወግደን ልንጥለው ይገባናል ፡፡ አንዳችን በአንዳችን ላይ ያለንን ጠላትነት እናቁም ፡፡ ለእኛ እንደምንጸልይ አድርገን ለሰው ልጅ ሁሉ ጸሎትን እናድርግ ፡፡ እንደአጋንንት ጨካኖች ከመሆን ይልቅ እንደ ቅዱሳን መላእክት ርኅሩኀን እንሁን :: ምንም ዐይነት ጥቃት በእኛ ላይ ይድረስ የራሳችንን ኃጢአትና የጌታ ትእዛዝን በመፈጸማችን የምናገኘውን ብድራት አስበን ፣ ከቁጣ ይልቅ የዋሃትን ገንዘባችን እናድርግ ፡፡ ከዚህች ምድር በምናልፍበት ጊዜ እኛ ለወንድማችን እንዳደረግንለት ጌታችን ለእኛም እንዲያደርግልን  ምንም የማይጠቅመንን ጠብን በትዕግሥት በማሳለፍ ጥለናት በምንሄዳት በዚህች ዓለም ሰላማዊያን ሆነን እንመላለስ ፡፡ በሚመጣው ዓለም የምንቀበለው ቅጣት የሚያስፈራን ከሆነ ሕይወታችንን በጠብ ያልተሞላ ቀላልና ሰላማዊ እናድርገው ፡፡ ወደ እርሱም የምንገባበትን የምሕረትን በር እንክፈተው ፡፡ ከኃጢአት ለመራቅ አቅሙ ያነሠን ቢሆን እንኳ እኛን የበደሉንን ይቅር በማለት በጥበብ እንመላለስ ፡፡ ይህም ማድረግ የሚያስጨንቅ ወይንም የሚከብድ አይደለም ፡፡ ጠላቶች ላደረጉን ቸርነትን በማድረግ ለራሳችንን ታላቅ የሆነውን ምሕረት ከአምላክ ዘንድ እናከማች ፡፡
በዚህ ዓለም በሁሉ ዘንድ ተወዳጆች እንድንሆን እንዲሁም እግዚአብሔር እኛን ወዳጆቹ በማድርግ ፣ የክብሩን አክሊል እንዲያቀዳጀን ለሚመጣውም ዓለም የተገባን ሆነን እንድንገኝ እግዚአብሔር ይርዳን ፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ታላቅ ፍቅር ባለው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእርሱ ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን ፡፡               

3 comments:

  1. KHY, wendimachin, I have really enjoyed all the sessions on Abatachin hoy!
    God bless you more and more

    ReplyDelete
  2. ለዚህ ትእዛዝ ተገቢውን ትኩረት ካለመስጠት የተነሣ ካልሆነ በቀር ለከፋ ቅጣት የሚዳርገን ሌላ ትእዛዝ የለም ፡፡ ነቢያት ሲዘምሩ ፣ ሐዋርያት በመንፈሳዊ ቅኔ ሲቀኙ ፣ እግዚአብሔርም ሲያስተምር እኛ ግን በዓለም ተጣብቀን እንባክናለን ፡፡ ራሳችንን በምድራዊ ነገሮች አሳውረናል ፡፡ በተዋንያን መድረክ ላይ የሚነበበውን የንጉሥ ደብዳቤ ለመስማት በጸጥታ እንድንቆም የእግዚአብሔርን ሕግ በጸጥታ ለመስማት አንተጋም ፡፡ በዚያ የንጉሡ ደብዳቤ ሲነበብ አማካሪዎች፣ ገዢዎች የመንግሥት ልዑካኑና ሕዝቡ ሁሉ ቃሉን ለመስማት ይቆማል ፡፡ በዚያ ጸጥታ ውስጥ አንድ ሰው ቢንቀሳቀስና ድምጽ ቢያሰማ ንጉሡን እንደናቀ ተቆጥሮበት ከባድ ቅጣትን ይቀበላል ፡፡ በዚህ ቦታ ግን ሰማያዊ ደብዳቤ በተነበበ ጊዜ በሁሉ አቅጣጫ ታላቅ የሆነ ሁከት ይቀሰቀሳል፡፡ ነገር ግን ደብዳቤውን የላከው ንጉሥ ከዚህኛው ምድራዊ ንጉሥ እጅግ የሚልቅ ነበር ፡፡ ታዳሚዎቹም የተከበሩ ናቸው ፡፡ ሰዎች ብቻ አይደሉም የሚገኙበት መላእክት ፣ ሊቃነ መላእክት የሰማይ ሠራዊቶች ሁሉ ይገኙበታል ፡፡ አኛም በምድር ያለነው ምስጋናን እናቀርብ ዘንድ ከጉባኤው ታድመናል ፡፡ “ሥራዎቹ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል” ተብሎ እንደተጻፈ ፡፡ አዎን እርሱ ለእኛ የፈጸማቸው እኛ ከምናስበውና ከምንረዳው በላይ ናቸው ፡፡

    ReplyDelete
  3. Wendimachin Kale Hiwetin yasemalin...Betam Ejig astemari tsihufoch nachew. Please continue in your spiritual writing....you have no idea how much i am learning....ye kedemut ye abatochachin menfesawi hiwet endet yasqenal wendimoche?

    ReplyDelete