Tuesday, June 12, 2012

እምነት እውነት ፍቅር በክርስትና



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/10/2004
አንድ በሀገራችን የነገሡ ንጉሥ ነበሩ፡፡ እኒህ ንጉሥ አንድ ወቅት “ልጅ ለአባቱ እምነት ለእናቱ እውነት ነው”ብለው ተናገሩ ይባላል፡፡ እንዲህ ብለው ከሆነ በእውነት ድንቅ የሆነን እውነት ተናገሩ፡፡ እኔ ግን እንዲህ እላለሁ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሔዋን አዳምን ታውቀውና ታፈቅረው እንዲሁም እንደ እናትነቱና እንደ አባትነቱ ትታዘዘው ዘንድ፣ እርሱን ፈጥሮ ካበቃ በኋላ ልክ ልጅ ከእናቱ ተወልዶ በአካል እስኪገለጥ ድረስ ከእናቱ ሰውነት ውስጥ ተሰውሮ እንዲቆይ እንዲሁ በአዳም አካል ተሰውራ እንድትቆይ አደረጋት፡፡ እናት ልጁዋን በዐይን ለማየት እንድትናፍቅ እርሱዋን ለማየት አዳም በናፈቀ ጊዜ እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ በመስቀል ላይ በተቀበለው ሕማም አርዓያ ሔዋንን ከአዳም ጎኑ አስገኛት፡፡ ስለዚህ ለአዳም አባታችን ሔዋን እውነቱ እንጂ እምነቱ አልነበረችም፡፡ እንዲሁም ሔዋን በአዳም አካል ውስጥ በነበረችበት ወቅት አዳም ፈጽሞ እንደሚወዳትና እንደሚያውቃት መጠን እርሱዋም እርሱን ፈጽማ ትወደውና ታውቀው ነበርና ለእርሱዋ አዳም እምነቷ ብቻ ሳይሆን እውነቷም ነው፡፡

እኛም እንዲሁ ነን፡፡ በእናታችን ማኅፀን ሳለን እንደ እናታችን የምናቀውና እርሱዋ እኛን እንደምትወድ እኛም እርሱዋን እንደምንወዳት እንዲሁም እኛ ሙሉ የሆነውን ውበቱዋን ጠንቅቀን እንደምናቅላት ማንም ሰው አያቅላትም፡፡ ስለዚህ ለእኛ እናታችን እውነት ለእርሱዋም እኛ እውነቶች ነን፡፡ ለአባታችን ግን እንዲህ አይደለንም፡፡ እኛ ለእርሱ እርሱም ለእኛ እምነታችን ነው፡፡ ምክንያቱም በማኀፀን ሳለን ስለአባታችን የምናውቀው በእናታችን በኩል ነውና፡፡
ሴት ልጅ አባቱዋን በእምነት ከእናቱዋ በሕሊናዋ ተስሎ ታየዋለች፡፡ በእምነት ያየችውን አባቱዋን በልደት በዐይኑዋ ስትመለከተው ለእርሱ ያላት ፍቅር ይጨምራል፡፡ በመሆኑም ፍቅሩዋ ወደ አባቱዋ ያዘነብላል፡፡ ይህ ግን ተፈጥሮአዊና እግዚአብሔር ስለፍቅር ሲል ሆን ብሎ በተፈጥሮአችን ውስጥ የሠራው ነው፡፡ እንግዲህ ለዚህች ልጅ አባቱዋ እምነትም እውነትም ሆነ ማለት ነው፡፡ 
በተቀራኒው ደግሞ ለወንዱ እናቱ እውነቱ ናት፡፡ ከእናቱ በላይ የሚያውቃትና የሚወዳት አንድም ሴት የለችም፡፡ ስለዚህ ለአቅመ አዳም ሲደርስ እናቱን የመሰለችውን እንደ እናቱ የምትወደውን እርሱም የሚወዳትን በእናቱ መልክና ጠባይ ያለችውን ሴት ለሚስትነት ይፈልጋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሴቶችም ሆኑ እኛ ወንዶች በማኀፀን ሳለን ያለንን እውቀት ተጠቅመን ይህን እየከወንን መሆናችንን ልብ አንለውም፡፡
ፍቅር እንዲህ ነው አካላት እርስ በእርሳቸው እንደሚተዋወቁና በፍጹም ተዋሕዶ እንደ አንድ አካል ሕዋሳቶች ሆነው ተስማምተው እንዲኖሩ በዚህ ጥልቅ እውቀትና ተዋሕዶ ውስጥ መገኘት ማለት ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ ፍቅር የለም፡፡ ይህ ፍቅር ገና ከማኅፀን ሳለን ከእናታችን ጋር በሥጋ በተቆራኘን ሰዓት የምናውቀው ፍቅር ነው፡፡ ይህ ዐይነት ፍቅር በምድር ላይ እንዲኖርም ክርስቶስ ኢየሱስ አንዱ የአንዱ የአካል ሕዋስ እንዲሆን አድርጎ ዳግም በእርሱ አካል ፈጠረን፡፡ እኛ ለእርሱ ያለን ፍቅርና እውቀት ጥልቅና እውነት እንዲሆን ከአካሉ ጋር በጥምቀትና በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ተዋሐድን፡፡ ስለዚህም በተደጋጋሚ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተዋሕዶአችን “እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተ ቅርንጫፎች ናችሁ፡፡” “እርሱ የቤተክርስቲያን ራስ ነው ቤተክርስቲያን ደግሞ አካሉ ናት፡፡” “እናንተ የክርስቶስ የአካሉ ሕዋሳቶች ናችሁ፡፡” “ራሳችሁ እርሱ ክርስቶስ ነው፡፡” ክርስቶስ የእናንተ ነው እናንተም የክርስቶስ ናችሁ” ተብሎ ተጻፈልን፡፡
 ስለዚህም ለእኛ ለክርስቲያኖች ክርስቶስ እውነት ነው፡፡ እግዚአብሔር አብ ደግሞ እምነታችን ነው፡፡ ምክንያቱም በክርስቶስ አካል ውስጥ ነንና በእርሱ የአባቱን መልክና ጠባይ በእምነት እንረዳለንና ነው፡፡ መረዳቱን የሚሰጠን ግን በባሕርይው ከአብና ከወልድ ጋር የሚስተካከለው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ስለዚህም በእውነትና በእምነት ሥላሴን በማወቃችን እርሱ እኛን እንዲወደን በእውነት ይህን ታላቅ የሆነ ፍቅር ተረድተነውና ቀምሰነው እንደሆነ እኛም ፈጽመን እንወደዋለን፡፡ ፍቅራችንም ፍጹምና እውነተኛ ነው፡፡ 
ነገር ግን እኔ እንደሚመስለኝ ይህን ታላቅ የሆነውን የፍቅር ጥምረትና ውሕደት ልክ ከእናታችን ማኅፀን ሳለን ያለንን ፍቅር በልደት እንድንዘነጋው ዘንግተነዋል፡፡ ከማወቅ ወደ አለማወቅ ተሸጋገረናል፡፡ ተፈጥሮአዊው የሆነውን ከማኅፀን ሳለን ከእናታችን ጋር የነበረው ፍጹም የሆነው የሥጋ ቁርኝት በመወለድ በመንፈስና በመረዳት ስለሚተካ ፍቅሩ ሊዘነጋን ይችላል፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ ነውና ሊሆን ግድ ነው፡፡ የሚደንቀው ግን አሁንም በክርስቶስ አካል ውስጥ ሆነን አካላችን በሆነው ክርስቶስ በኩል በእምነት የምናውቀውን እግዚአብሔር አብን እንዲሁም አብንና ወልድን እንድናውቅ የሚረዳንን በእኛ ውስጥ ሆኖ ለአእምሮአችን ማስተዋልን የሚሰጠንን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን መዘንጋታችን ነው!!!
ስለዚህም በክርስትና ሕይወት ውስጥ ለሚኖር ክርስቲያን ይህን ጥልቅ የሆነ ተዋሕዶ ለመረዳት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን አዘውትሮ ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ በእርሱ ካልሆነ በቀር ወደዚህ የእውቀት ከፍታ መወጣጣትና ወደፍቅሩ ሙላት መድረስ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡ በቅዱስ ሥጋው ወደሙ የምናገኘው ይህ መረዳት በሰው ቋንቋ መግለጥ ፈጽሞ  የማይሞከር ነው፡፡ ለእኛ ግን በልባችን ሞልቶና ተሟልቶ እናውቀዋለን፡፡ ቅዱስ ሥጋው ወደሙ ወንጌልን ያስረጃታል፤ ምክንያቱም በወንጌል የተሰበከውን እውነት በድርጊት ስለምንረዳው ነው፡፡ እንዲያ ከሆነ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ፈንታ ክርስቶስ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ይሆንልናል ማለት ነው፡፡ እኛም ልዩ በሆነ እምነት፣ እውነትና ፍቅር ውስጥ መኖር ይቻለናል ማለት ነው፡፡ አምላካችን ሆይ ይህ መረዳት በሕሊናችን ሞልቶ እንዲፈስና ዘወትር በፍቅርህ ውቅያኖስ ውስጥ እንድንዋኝ በንስሐ ወደ ቅዱስ ሥጋህና ክቡር ደምህ እንድንቀርብና ተቀብለነውም ማስተዋላችን በመንፈስ ቅዱስ ሙሉ እንዲሆን እርዳን ለዘለዓለሙ አሜን!!!    

2 comments:

  1. wedimachin tsega berketin yadlih yekalun deji kezih belay yikifetilhi mekilitachewin 2ena 5 adgewi katerfut tamagni ageligayoch(GEREBIH) kehont Amilak kidusan yidemirih astemro newar yaergih kale hiywet yasemah .AMEN!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

    ReplyDelete
  2. Deacon tsegawn yabizalih yegnanim amiero afikaryachin kirisitosin lemredta wedzignaw ayiten yewiket dreja yashagiren

    ReplyDelete