Tuesday, June 5, 2012

"አባታችን ሆይ"በቅዱስ ዮሐንስ አፈወረርቅ(ክፍል ዐራት)


“በደላችንን ይቅር በለን እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል” 
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/09/2004
ከአእምሮ በላይ የሆነው ምሕረቱን ትመለከታለህን ? እጅግ ታላላቅ የሆኑትን ክፋቶቻችንን ካስወገደልንና የእርሱን ታላቅ የሆነው ስጦታውን ከሰጠን በኋላ ሰው ዳግመኛ ቢበድል እንኳ በደላችንን  ይቅር ሊል ዝግጁ እንደሆነ በዘዚሀህ  ኃይለ ቃል አስታወቀን፡፡ ስለዚህም ይህ ጸሎት የአማኞች ጸሎት ይሆን ዘንድ በቤተክርስቲያን የጸሎት ሥርዐት ላይ መጀመሪያ የሚጸለይ ጸሎት ሆኖ ተሠራ፡፡
 ሰዎች ተጠምቀው ክርስቲያን ካልሆኑ በቀር እግዚአብሔር አብን አባት ብሎ መጥራት አይችሉም፡፡ ይህ ጸሎት እንግዲህ አማኞች ሊፈጽሙትና ሁሌም ሊጸልዩት  የሚገባ ጸሎት ከሆነ ቅዱስ ሥጋውና ቅዱስ ደሙን ከተቀበልን በኋላ ብንበድልና ንስሐ ብንገባ ንስሐችን ዋጋ እንደማያጣ ግልጽ ይሆንልናል፡፡ እንዲህ ባይሆን ኖሮ እንዲህ ብለን እንድንጸልይ  ሥርዐት ባልተሠራለን ነበር፡፡ ስለዚህም እርሱ ኃጢአታችንን እንድናስብና ይቅርታን እንድንጠይቅ እያሳሰበን እንዲሁም እንዴት ምሕረትን ማግኘት እንደምንችል እያስተማረንና ሸክማችንን በቀላሉ እንዴት ማቅለል እንደምንችል እያሳየን በምሕረቱ አጽናናን፡፡




ይህን የጸሎት ሕግ ለእኛ  ፍጹም ግልጽ የታወቀና ከጥምቀት በኋላ ብንበድል እንኳ መተላለፋችንን በንስሐ ሊታጠብ እንደሚችል የሚያስገነዝበን ነው፡፡ እርሱ እኛን ኃጢአታችንን በማሳሰብ፣ የበደሉንን ይቅር እንድንል በማዘዘ፤ ትሑታን እንድንሆን እየመራንና ከበቀል ጸድተን እንድንገኝ ሥርዐት ሠራልን፡፡  እንዳዘዘንም ፈቃዱን ፈጽመን ብንገኝ ፤ ከእርሱ ዘንድ ይቅርታን እንደምናገኝ በማመላከትና ታላቅ የሆነውን ተስፋ በማሰነቅ፤ እርሱ እግዚአብሔር ለሰዎች ያለውን ታላቅ ፍቅር ገለጠልን፡፡….
በእዚህ ብቻ ግን አላበቃም ፤ ነገር ግን ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት እንደሰጠው ለማመላከት ሲል እንዴት መጸለይ እንዳለብን አስተምሮ ካበቃ በኋላ ደግሞ “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም”(ማቴ.፮፥፬-፭) አለን ፡፡ ስለዚህም የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ጀማሪዎቹ እኛው ነን ፡፡ በእኛ ላይ የሚበየነውን ብያኔ የምንወስነውም እኛው ራሳችን ነን ፡፡ጌታችን ማንም ሰው ወደ ፍርድ በመጣ ጊዜ  ትንሽም ይሁን ትልቅ ቅሬታን ማቅረብ እንዳይችል ፍርዱን በራሱ ይቅር ባይነት ላይ እንዲመሠረት አደረገው፡፡
“አንተ በሌላው ላይ በፈረድከው ፍርድ መሠረት” እንዲሁ “የእኔም ፍርድ እንዲሁ ይሆናል” ይለናል ጌታችን፡፡  ምንም እንኳ የአንተ ይቅር ባይነትና የእኔ ይቅር ባይነት የሚወዳደሩ ባይሆኑም ፤ ወንድምህን ይቅር የምትል ከሆነ እንዲሁ እኔም ይቅር እልሃለሁ” አለን፡፡ ነገር ግን ወንድምህን ይቅር ብትል አንተ በብድራት የምትሻውን ለማግኘት ስትል ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ከአንተ ወይም ከወንድምህ እንደምትፈልገው ዐይነት ፍላጎት ለእርሱ የለውም፡፡ …
እርሱ ምንም እንኳ ኃጢአትን የሚጸየፍ  ቢሆንም የአንተን መተላለፍ ይታገሳል፡፡ ነገር ግን ከእርሱ በረከት ተሳታፊ እንድትሆን በሁሉም አቅጣጫ ለሰዎች በምታሳየው ከበሬታና ፍቅር በአንተ ውስጥ ያለውን ነውር ሁሉ አውጥቶ ያስወግድልሃል፤ በአንተም ላይ የነደደውን የቁጣ እሳትን ያጠፋልሃል፡፡ በዚህ ምክንያት በሁሉም መንገድ የአካልህ ክፍል ከሆነው ከወዳጅህ ጋር አንድ ለመሆን ትበቃለህ፡፡…..
በእጃችን  መዳናችንን ተረክበነው ሳለ ይህን መዳን ችላ ብንል ምን ዐይነት የከፋ ቅጣት ይጠብቀን ይሆን ? በራሳችን ላይ በፈረድነው ፍርድ እና በፈቃዳችን ልንፈጽማቸው የተሰጡንን ለመፈጸም ፈቃደኞች ባለመሆናችን ምክንያት ኃላ በእኛ ላይ በተፈረደብን ፍርድ ምን ልንል ይሆን?   
አቤቱ ወደፈተና አታግባን ከክፉ አድነን እንጂ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይል ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን
ጌታችን በዚህ ኃይለ ቃል የእኛን ደካማነት በማሳወቅና መታበያችንን በማጥፋት ፣ ፈተናዎች በእኛ ላይ ከመሠልጠናቸው በፊት በትሕትና በመገኘት ልናርቃቸው እንደሚገባን አስተማረን፡፡ ወደ ፈተና የምንገባው ከአላዋቂነታችንና ከትዕቢታችን የተነሣ ነው፡፡ ትዕቢት ወደ ፈተና ይጥለናል፡፡ 
በዚህ ቦታ ሰይጣንን “ክፉ” እንዳለው እናስተውላለን ፡፡ በዚህም ያለ ዕረፍት እኛን ለመጣል በሚፋጠነው ሰይጣን ላይ ጦርነትን ልንከፍት እንዲገባን አሳሳበን ፡፡ ነገር ግን ሰይጣን ክፉ ሲባል ከፍጥረቱ ክፉ ሆኖ የተፈጠረ ነበር ማለቱ ግን አይደለም ፡፡ በተፈጥሮ ክፉ ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት የለም ፡፡ ነገር ግን  እኛው ክፋትን  በፈቃዳችን ከተፈጥሮችን ጋር የምንደባልቀው ፡፡ ስለዚህም እኛን በኃጢአት ስላሰናከለን ቅድመ ጠላታችን ተባለ ፡፡ እንዲሁም ያለ አንዳች ምክንያት እኛ ላይ ጦርነትን በመክፈቱ ጠላታችን ተሰኝቶአል ፡፡ ስለዚህም “ ከፈተና አድነን” ብለን እንድንጸልይ ሳይሆን “ከክፉ አድነን አንጂ” ብለን እንድንጸልይ አዘዘን ፡፡ እንዲህም ሲል በወዳጆቻችን ክፉ ሥራ ደስ ባንሰኝም ፤ በእነርሱ እጅ ማንኛውንም በደል ብንቀበል ፤ ለክፋታቸው  ምክንያት እርሱ ነውና  እነርሱን ጠላት ከማድረግ ተቆጥበን  ጠላትነታችንን በሰይጣን ላይ ሊሆን ይገባል ሲለን ነው፡፡
ወደ ፈተና እንዳንገባ ጠላታችን ማን እንደሆነ ለይቶ በመጠቆም ፣ በእርሱ ወጥመድ እንዳንያዝ እያስጠነቀቀን ፣ ባለማስተዋል የምንፈጽማቸውን ክፉ ተግባራትን ከእኛ ቆርጦ በመጣል ፣ እንዲሁም መንፈሳችንን በማነቃቃትና በማትጋት የጽድቅ ዕቃ ጦርንን የሚያስታጥቀን ንጉሥ ማን እንደሆነ በማስታወስ እንዲሁም እርሱ ከሁሉ በላይ ኃያል እንደሆነ በማመልከት “መንግሥት የአንተ ናትና ኃይል ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን” እንድንል አዘዘን ፡፡ ይቀጥላል.....


No comments:

Post a Comment