Saturday, February 4, 2012

ቀዳሚት ሰንበት በቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
27/05/2004
ይህ ጽሑፍ የደማስቆው ቅዱስ ዮሐንስ የአይሁድን የሰንበት አከባበር በመቃወም ከጻፈው ጽሑፍ የተመለሰ ነው፡፡ 
አይሁድ ሰባተኛዋ ቀን ሰንበት ትባላለች እኛ ደግሞ ቀዳሚት ሰንበት እንላታለን፡፡ ትርጉሙም ዕረፍት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ እንዲል እግዚአብሔር በዚህች ቀን ከሥራው ሁሉ ዐርፎባታልና፡፡(ዘፍ.2፡2)ከዚህም የተነሣ ቀናት ሲቆጠሩ እስከ ሰባት ቀን ተቆጥረው ካበቁ በኋላ እንደገና አንድ ተብለው ይቆጠራሉ፡፡ ሰባተኛዋ ዕለት በአይሁድ ዘንድ ልዩ ስፍራ አላት፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰባተኛዋን ቀን ትከበር ዘንድ አዞአቸው ነበርና፡፡ ይህ ሕግ እንዳው ያለምክንያት የተሰጣቸው ሕግ አልነበረም፡፡ስለአይሁድ አመፅ የተሠራላቸው ሕግ ነው እንጂ፡፡ ይህን የመጻሕፍትን ምሥጢር መለየት ሀብቱ የተሰጣቸው መምህራን ይረዱታል፡፡
በሰሚዎቹ ዘንድ ያልተለመደ ነገር ግን ጠቃሚ የሆነ ሕይወትን ለማለማመድ ከተፈለገ ቀላል በሆነ ልምምድ መጀመር መልካም ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እስራኤላውያን ሥጋውያንና ለምድራዊ ብልጥግና ብቻ የሚተጉ እንዲሁም ከመንፈሳዊ እውቀት የራቁ እንደሆኑ ሲረዳ አስቀድሞ “ሰባተኛው ቀን ሰንበት ነው፤ አንተ እንደምታርፍ… ሎሌህም ገረድህም በሬህም አህያህም ከብትህም ሁሉ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፡፡”ብሎ ትእዛዝን ሰጣቸው፡፡



እንዲህ የማለቱ ምክንያት “ጻድቅ ስለ እንስሳው ነፍስ ይራራል” የሚለው በእነርሱ ይፈጸም ዘንድ ነበር፡፡  መንፈሳዊው ግቡ ግን ስለምድራዊ ነገር ከመትጋት ወጥተው ሰባቱንም ዕለታት ለእግዚአብሔር እንዲቀድሱ ማለማመድ ነው፡፡ ሕግና መንፈሳዊ መጻሕፍት ባተልሰጡበት ጊዜ ሰንበት ለእግዚአብሔር የተቀደሰች ቀን አልነበረችም፡፡ ነገር ግን ሕጉ ለሙሴ በተሰጠ ጊዜ ሰንበትም ለእግዚአብሔር የተቀደሰች ቀን ሆነች፡፡ ለምን ቢባል ገና ከምድራዊ አስተሰሳሰብ ያልተላቀቁ አይሁድን ለማስተማር ሲባል ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ወገኖች ቅጣትን በመፍራት በዚህች ቀን ብቻ ተቀድሰው እንዲታዩ ሲሉ ያከብሩዋት ነበር እንጂ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ዘመናቸውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ለመቀደስ የሚለማመዱባት ቀን አድርገው አይመለከቷትም ነበር፡፡ ቢሆንም ይህቺን ሕግ በማክበራቸው ምክንያት ያንቺን ቀን ብቻ ከአመፃ ይርቁ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “ሕግ የተሠራው ለኃጥአን እንጂ ለጻድቃን አይደለም”ማለቱ፡፡ (1ጢሞ.1፡9)
እንዲያ ባይሆን ነቢዩ ሙሴ አርባ ቀንና ሌሊት ከአንዴም ሁለቴ ጦሞአል፡፡(ዘፀአ.24፡18፤34፡28) ምንም እንኳ ሕጉ በሰንበት እንዳይጦም ቢከለክልም እርሱ ግን በሰማንያዎቹ ቀናት ውስጥ ባሉት ሰንበታት ጦሞ ነበር፡፡ እነዚህ ወገኖች ምናልባት ይህ እኮ የተፈጸመው ሕጉ ከመሰጠቱ በፊት ነው ሊሉ ይችላሉ፤  እንዲያ ከሆነ ስለቴስቢያዊው ኤልያስስ ምን ሊሉ ይሆን? ምክንያቱም እርሱ አንዴ ተመግቦ አርባ ቀን ሙሉ ተጉዞአልና፡፡ ይህ ነቢይ ሥጋውን በጦም በመጎሰም ብቻ አልነበረም የሰንበትን ሕግ የተላለፈው በሰንበት ረጅም መንገድንም በመጓዙ ሰንበትን ሽሮአል፡፡ ነገር ግን ሕጉን የሠራው እግዚአብሔር በእርሱ አልተቆጣበትም ነበር፡፡ በተቃራኒው ግን ለቅድስና ሕይወቱ ዋጋ ይሆነው ዘንድ በሆሬብ ተራራ ተገለጠለት፡፡ እነዚህ ወገኖች ስለ ነቢዩ ዳንኤልስ ምን ይሉ ይሆን? እርሱ ያለ ምግብና ያለመጠጥ ሦስት ሳምንታት ተጉዞአልና(ዳን10፡2፣3) ስለራሳቸውስ ምን ይመልሳሉ? ምክንያቱም የልጆቻቸው የግርዝት ቀን ሰንበት ላይ ቢውልባቸው ልጆቻቸውን ሰንበት ነው ብለው ከመግረዝ አይመለሱምና፡፡ ካህናት በቤተ መቅደስ ሰንበትን ይሽራሉ፤ ነገር ግን ሕጉን በመተላለፋቸው ምንም የሚመጣባቸው ቅጣት የለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጌታችን እንዳስተማረው አንድ ሰው በሰንበት በጉ ወደ ጉድጓድ የገባበት እንደሆነ በሰንበት በጉን ከጉድጓድ ውስጥ በማውጣቱ ሕግን እንደተላለፈ አይቆጠርበትም፡፡
እነርሱስ የቃል ኪዳን ታቦቷን ተሸክመው የኢያሪኮን ቅጥር ሰባት ቀን ሙሉ አልዞሩምን? ከእነዚህ ቀናት ውስጥ አንዷ ቀዳሚት ሰንበት ናት፡፡ ስለዚህም ሰባተኛይቱን ቀን በመሻራቸው አንዳች ቅጣት መጣባቸውን? ስለዚህም ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት በዚህች የዕረፍት ሰዓታቸው ለእግዚአብሔር ጊዜ እንዲሰጡ ለማድረግና አገልጋይ ባሮቻቸውንና እንስሳቶቻቸው በዚህች ቀን እንዲያርፉ በዚያውም ከእግዚአብሔር ጋር የመኖርን ጣዕም እንዲቀምሱና አስከትለው መላ የሕይወት ዘመናቸው ለእርሱ እንዲቀድሱ ለማድረግ ሲባል ሰንበት እንደተሠራላቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ቢሆንም እነርሱ “ገና ሕፃናትና ከዓለም የመጀመሪያ ትምህርት በታች በመሆናቸው ከቃሉ በስተጀርባ ያለውን የእግዚአብሔርን አሳብ አልተረዱትም ነበር፡፡(ገላ.4፡3)“ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የሆነውን ልጁን ላከ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ”(ገላ.4.4-5) እንዲል በእርሱ ያመንን እንደተሰጠን የጸጋ መጠን የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ሥልጣኑን በጥምቀት አግኝተናል፡፡ አሁን ከእንግዲህ እኛ ከጸጋው በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደለንም፡፡ስለዚህም ለእግዚአብሔር እርሱን በመፍራት ከጊዜአችን አንዲት ቀን ብቻ ለይተን የምንሰጥ አይደለንም፤ ነገር ግን መላ ሕይወታችንን ለእርሱ ልንሰጥ ተጠርተናል፡፡ … ስለዚህ “ለክርስቲያን ጊዜዎች ሁሉ የበዓል ቀናት ናቸው” እንዲል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘመናችንን ሁሉ ለክርስቶስ ልንቀድስ ይገባናል፡፡ ሰንበት ማለት ከኃጢአት መከልከል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ከኃጢአት ተከልክለን የኖርን እንደሆነ በሰንበት ዕረፍት ውስጥ ነን፡፡ አምላክ ይህን ማስተዋል ለሁላችን ያድለን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment