Saturday, February 4, 2012

መድኀኒዓለም



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
(ስብከት ወተግሣጽ ለሚባለው መጽሐፌ መታሰቢያ የተጻፈ)
27/07/2003 ተጻፈ
ጌታ ሆይ አንተ የመንፈሳውያንና የምድራውያን ፍጥረታት ገዢ እንደሆንኽ በሰማይም በምድር ያሉ ፍጥረታት ሁሉ ተገንዝበው ለአንተ እንደ ችሎታቸው መጠን በፍቅር በመሆን ምስጋናን ያቀርቡ ዘንድ ሰውን ሰማያዊና ምድራዊ አካል እንዲኖረው አድርገህ በመፍጠር የገዢነትህ ምልክት አደረግኸው ፡፡
 ምድራውያን ለአንተ አርዓያና አምሳል ለሆነው ሰው ሲገዙለት አንተን የሚያገለግሉህ ሰማያውያን መላእክት ደግሞ በፍቅር አገለገሉት ፡፡ ለማይታየው አምላክ ምሳሌ በሆነው በአዳም ተፈጥሮ በኩል መላእክት አንተን አይተው ደስ ተሰኙ ፡፡ እነርሱ በላይ በሰማይ የአንተን ፍቅር እየተመገቡ ፍጹም በሆነ ደስታ ይኖራሉና አርዓያህና አምሳልህ የሆነውን አዳምን ባዩት ጊዜ በደስታ ዘመሩ ፡፡
  መላእክት የፈጣሪነትህና የማንነትህ መለያ የሆነውን በአርዓያህና በአምሳልህ በተፈጠረው ሰው ባሕርይ ውስጥ አይተው ሦስትነትህንና አንድነትህን ተማሩ ፡፡ ጌታ ሆይ “ሰውን በአርዓያችንና በአምሳላችን እንፍጠር” አልኽ ፡፡ “ወንድና ሴት አድርገህም ፈጠርካቸው”፡፡ በአካል የተገለጠው ግን አንድ አዳም ነበር ፡፡ ሔዋን ግን በአካሉ ውስጥ ነበረች ፡፡  በኋላም ከአዳም እርሱዋን በመለየት ገለጥካት፡፡
 በዚህም አብ በመውለዱ፣ ወልድም በመወለዱ፣ ምክንያት በመካከላቸው መቀዳደም እንደሌለ አርዓያህና አምሳልህ በሆነው በሰው ተፈጥሮ በኩል ለመላእክት አስተማርካቸው ፡፡ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ቢሰርጽም በአብም በወልድም ሕልው እንደሆነ እንዲሁ አዳምና ሔዋንም በአንድ አካል በነበሩበት ወቅት አንዲት ነፍስ ነበረቻቸው፡፡ በዚህም መላእክት መንፈስ ቅዱስ ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው እንደሆነ ተረዱ ፡፡ ስለዚህም መላእክት ሥላሴን በምሳሌው አይተውታልና  ሰውን የፈጠረውን እርሱን እጅግ ወደዱት ፡፡


ጌታ ሆይ ለእኛ ለሰዎች በፈቃዳችን ፈቃድህን እንፈጽም ዘንድ በንግሥና ቦታችን በገነት ፈቃድህን አስታወቅኸን ፡፡  በዚያም “ክፉና ደጉን ከሚያሳውቀው ዛፍ ፍሬ አትብሉ ነገር ግን ብትበሉት ሞትን ትሞታላችሁ አልከን ፡፡ እኛ ግን ፈቃድህን በመጥፎ ፈቃዳችን ጥሰነው ለክፉ ሰይጣንና ለፈቃዱ ታዘዝን ፡፡ ፈቅደን በፈጸምነው ኃጢአትም ያለ ፈቃዳችን ጽኑ ስቃይንና መከራን ተቀበልን ሞትም በእኛ ላይሠለጠነብን ፡፡ ነገር ግን ጌታ ሆይ የገዢነትህ ምልክት የሆነውንና በዘለዓለማዊ ፍቅርህ የወደድከውን የሰውን ልጅ ጉስቁልናና ስቃይ ስትመለከት በልዕልና ፀንቶ መቀመጥን አልመረጥክም ፡፡ ስለእኛ ባለህ ወሰን በሌለው ፍቅርህ የተነሣ ከቅድስት ድንገል ማርያም በመወለድ ከፍርድ በታች የነበረውን የባሪያህን አርዓያና አምሳል ይዘህ በትሕትና ተገለጥኽ፡፡ በዚህም ምክንያት አርዓያህንና አምሳልህን በእኛ ስላዩ ሲደነቁ የነበሩት መላእክት ፣ አንተን በእኛ አርዓያና አምሳል ሲያገኙ ይበልጥ መገረም ሞላባቸው ፡፡ 
እኛ የሰው ልጆች ግን ጌታ ሆይ ስለፍቅርህ ጥላቻን ፣ ጸጋን ስላለበስከን የውርደት ልብስን አለበስንህ ፤ ርኩስ ምራቃችንንም በንጹሕ ገጽህ ላይ ተፋን ፡፡ እኛን ወደ ቀደመው ንግሥናችን በመመለስህም ፣ ቅዱስ ኤፍሬም እንዳለው ከወይን እርሻችን የበቀለውን እሾኽ ጎንጉነን አክሊል በማድረግ “ንጉሥ ሆይ ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት በተሳልቆ በራስህ ላይ ደፋንብህ ፣ ለሰይጣን መጫወቻ ፣ ለአጋንንት መሳለቂያ ከመሆን ልታድነን በመጣኸው በአንተ ላይ ስቃይን አበዛንብህ ፤ በአንተም ላይ ዘበትን ፡፡ ይህን ማንም በኃጢአት የታወረ ሁሉ ሊፈጽመው የሚችለው ነው ፡፡ “ከዓለም የሆነ ሁሉ እግዚአብሔርን ይጠላልና” ፡፡
እኛም በኃጢአት ውስጥ ነበርንና ባለማወቅ ሕይወትን ለሰጠኸን ለአንተ ሞትን በብድራት መለስንብህ፡፡ አንተ  ግን ጌታ ሆይ  አንተ ላይ እንዲህ መከራን በማጽናታችን ምክንያት ለእኛ ያለህ ፍቅር አንዲትም ጋት ታክል ስንኳ አልቀነሰም ፡፡ነገር ግን ጌታ ሆይ ስለመተላለፋችና ስለጭካኔአችን እንዳንጠፋ በባሕርይ ውስጥ ያለው ፍቅርህ ስለእኛ አማላጃችን ሆነልን8፡፡
ስለዚህ በሞትህ ሞትን ገደልኽልን ፣ ከሲኦል አውጥተህ መንግሥትህን ሰጠኸን ፤ ከባርነት አላቀህ ልጅነትን አጎናጸፍከን ፤ የውርደት ልብሳችንን ገፍፈህ የጸጋ ልብስን በጥምቀት ደረብክልን፡፡ በጥምቀትም የለበስነው ልብሳችን ጌታ ሆይ አንተው ነህ(ገላ.፫፥፳፯)  ፡፡
ነገር ግን ጌታ ሆይ እኛ ሰዎች ዝንጉዋን ነንና በመስቀልህ ስለእኛ የተቀበልከውን ሕማምና መከራ ሁሉ አስበን ኃጢአትን እንድንጸየፋትና በፍቅርህ ሥጋችንን ፣ ነፍሳችንን ፣ መንፈሳችንን እናስገዛ  ዘንድ ስቅለትህን ሁሌም እንድናስበው እርዳን ፡፡
ጌታ ሆይ አንተ ለሚጠሉህም ለሚያፈቅሩህም ፍቅርህን እንዳሳየሃቸው እኛም ጠላቶቻችንንና ወዳጆቻችንን እኩል እንድናፈቅር የአንተን ልብ ስጠን9 ፤ ደሃውን ከፍ ከፍ እንዳደረኸው ፣ ባለጠጋውንም እንዳልናቅኸው ፣  ሰውን ሁሉ እኩል እንዳከበርካቸው እንዲሁ እኛም ሰውን ሁሉ እኩል እንድናከብር ፣ትሕትናህንና የዋህነትህን አልብሰን ፤ በአንተ ደም ግባት መጥፋት የሰውን ልጅ ሁሉ ልዩ በሆነ ውበት እንዳስጌጥከው ፣ ሰውን ሁሉ በተፈጥሮም ይሁን ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ ጉድለቱ እንዳናቃልለው ጌታ ሆይ በአንተ ዐይን ፍጥረትህን እንድንመለከት አድርገን ፤ ለሰው ሁሉ አንተ ብቻ ጌታው ፣ እርሱም የአንተ ባሪያ እንደሆነ በመገንዘብ በማንም ላይ ፍርድን ከመፍረድ እንድንቆጠብ ፣ ጌታ ሆይ ሁሌም ስቅለትህን እንድናስበው እርዳን ፡፡

No comments:

Post a Comment