በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
5/12/2004
(አንባቢያን ተጨማሪ
በእናታችን ዙሪያ ጽሑፍ ካለህ ብለው ስለጠየቁኝ በ1996 ካዘጋጀሁት ጽሑፌ እነሆ ብያለሁ)
ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ተወልዶ ዓለምን
ከጥፋት እንደሚያድን እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበረ፡፡” ኢሳ. 1፥14
ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ ዘርን የሚለው ቃል ለጊዜው በእግዚአብሔር ርኅራኄ ጨርሶ ከመጥፋት የዳኑትን ቱሩፋንን ቢሆንም (እነዚህም ከጥፋት
የዳኑ ደጋግ የእስራኤል ሕዝቦች ናቸው) ፍጻሜው ግን ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለክርስቶስ የተነገረ ነው፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም ራሷን በንጽሕናና በቅድስና በማኖር የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ
በመሆንዋ ምክንያት ከራስዋ ቅድስና ጋር ታክሎ መንፈስ ቅዲስ ፍጽምትና ቅድስት እንድትሆን አድርጓታል፡፡ እግዚአብሔር ባወቀ በዚህ
ምክንያት ነው እርሷን ለተዋሕዶ የመረጣት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን አስተውለን ብንመለከት የእግዚአብሔር ማደሪያ ወይም እግዚአብሔር የመረጣቸው
ወይም የእግዚአብሔር ክብር የተገለጠባቸው ቅዱሳን እንዲሁ በከንቱ ቅድስ የተባሉ እንዳልሆኑ እንረዳለን፡፡
ነገር ግን እግዚአብሔርን በመውደድ እርሱ ደስ የሚያሰኘውን ሥራ በመሥራት
ራሳቸውን ከዓለም ጉድፍ በመጠበቅ በትልቅ ተጋድሎ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በእነርሱ እግዚአብሔር ሥራውን ለመሥራት
አያፍርም ስለዚህም ቅዱስ ዳዊት “እግዚአብሔር በጻድቁ እንደተገለጸ እወቁ” መዝ.4፥3 ብሎ በመንፈስ ተሞልቶ መሠከረ፡፡ጌታችን መድኀኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስም “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን”
/ዮሐ.14፥24 ብሎ አስተማረን፡፡ ቅድስት እናታችንንም እግዚአብሔር ለተዋሕዶ ሲመርጣት የንጽሕና የቅድስና ሕይወቷን ተመልክቶ ነው፡፡
ቅድስናዋም ከቅዱሳን ሁሉ ስለሚበልጥ እግዚአብሔር ለአንዴ የሚያደርገውን ወደፊትም ለሌሎች የማያደርገውን ሥራ በእርሷ ለመሥራት የፈቀደው፡፡
እኛም ኦርቶዶክሳውያን የቅድስት ድንግል ማርያምን ንጽሕና እንዲህ በማለት እንመሰክራለን፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም
በሐልዮ በነቢብ በገቢር ከሚሠራ ኃጢአት ሁሉ ንጽሕት ናት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም እንደሚያስረዳን “ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም
የለብሽም” እንዳለ /መኃ.4፥7/፡፡ ይህንን ስንል ኃይለ አርያማዊት ናት ወይም ከሰው ወገን አይደለችም ማለታችን ሳይሆን በአዳምና
በሔዋን በኃጢአት መተላለፍ በሰው ሁሉ ላይ ያለው የውድቀት ባሕርይ /fallen nature/ እርሱም መራብ፣ መጠማት፣መድከም፣ መሞት
እንደማንኛውም ሰው የሚስማማት ሲሆን ነገር ግን ከኃጢአት ሁሉ ራሱዋን ጠብቅ የተገኘች ንጽሕት ናት ማለታችን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት
ነው ቅዱሳን አባቶች ከኃጢአት በቀር ክርስቶስ የሰውን ባሕርይ ባሕርይው አደረገ ብለው ማስተማራቸው፡፡ ራሱም ጌታችን ከቅድስት ድንግል
ማርያም በነሣው ሥጋና ነፍስ ተርቧል፥ ደክሟል፥ መከራ ተቀብሉል፣ ሞቷል፡፡ ራሱንም የሰው ልጅ ብሎ መጥራቱም የሰውን ባሕርያትን
ገንዘቡ እንዳደረገ ለማጠየቅ ነው፡፡ /ዮሐ.3፥14-15/
እግዚአብሔር አምላክ ሰው ሆኖ ሰውን ሊቤዥ በፈለገ ጊዜ በቅድስና፣ በንጽሕና፣ በታማኝነት፣
በትሕትና፣ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግና በፍቅር በመመላለስ የመልካም ነገር ሁሉ ግምጀ ቤት በመሆን እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም
ሌላ ሴት አላገኘም ነበር፡፡ እንዲህም ስለሆነ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ /ሉቃ.1፥28/ ብሎ ቅዱሱ መልአክ መሠከረላት፡፡
ሲራክም “….ብቻዬን በአድማስ ዞርኩ በውቅያኖስም ዞርኩ በባህርም ማዕበል መካከል ተመላለስኩ…. ከዚህም በኋላ ዕረፍትን ፈለግሁ
እንግዲህስ የማንን ሥጋ አዋሐዳለሁ …. በእርሱ ፈቃድ በከበረ በማርያም ማኅፀን ሥጋን ተዋሐድኩ በምኩራብም አስተማርኩ” /ሲራ.24፥1-10/
ብሏል፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው “እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ ምስራቅንና ምዕራብን ሰሜንና ደቡብን ዳርቻዎችን ሁሉ በእውነት
ተመለከተ ተነፈሰ አሸተተም እንደ አንቺ ያለ አላገኘም የአንቺን መዓዛ ወደደ ደም ግባትሽንም ወደደ የሚወደውን ልጁንም ወደ አንቺ
ሰደደ፡፡” ብሎ ከፍጥረታት ሁሉ በቅድስና የሚስተካከላት እንደሌለ መስክሯል፡፡ ስለዚህም እኛም ቅድስት ድንግል ማርያም በእውነት
ንጽሕት ፍጽምት ክብርት ናት ብለን እንመሰክራለን፡፡
ለቅድስት ድንግል ማርያም አክብሮትና እንደሚገባ
ክርስቲያን ነኝ የሚል ሁሉ ለቅድስት ድንግል ማርያም አክብሮት እንደሚገባት አይጠፋውም
በትክክልም ያምንበታል፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ” /ሮሜ.13፥7/ ብሎ እንደሚያዝዝ፡፡ በተለይ
ደግሞ ትክክለኛ ክርስቲያን ከሆነ የእርሱ ድኅነት ከቅድስት ድንግል ማርያም ለመልአኩ ቃል መታዘዝ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ እንደሆነ
ስለሚረዳ በእርሱ ውስጥ ልዩ ሥፍራና ክብር አላት፡፡ ነገር ግን ክርስቲያን ያልሆነ ሰው ለእርሷ ተገቢውን ክብር ላይሰጣት ይችላል፡፡
ምክንያቱም ለሰዎች ሁሉ ከመጣው ድኅነት ውጪ ነውና አያቀውም፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም በመጀመሪያ ራሷን በቅድስናና በንጽሕና በማኖር የመንፈስ ቅዱስ
ማደሪያ አደረገች በኋላም አምላክ ለተዋሕዶ እንደመረጣት ከቅዱስ ገብርኤል በተረደች ጊዜ “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ” /እንደቃልህ ይሁንልኝ/
በማለት በእምነትና በደስታ ተቀብላ አምላክን ፀንሳ በመውለድ እናትና አገልጋዩ ሆነችው፡፡
እዚህ ላይ ለድንግል ማርያም ልዩ ፍቅርና አክብሮት እንዲኖረን የሚያደርገን ነገር አለ፡፡
እርሱም የቅድስናዋ ውጤት ነው፡፡ እግዚአብሔር ያለሰው ፈቃድ በሰዎች ልጆች ላይ በማደር ሥራውን ለመሥራት አይፈቅድም፡፡ “በደጅ
ቆሜ አንኳኳለሁ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል፡፡”
/ራዕይ.3፥20/ እንዲል መጽሐፍ ቅዱስ ቅድስት ድንግል ማርያምም ለመልአኩ ቃል በመታዘዝ የዓለሙን ሁሉ አዳኝ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስን
ወልዳልናለች፡፡ ስለዚህም እናከብራታለን የእርሷ እሺ ማለት ለእኛ መዳን ምክንያት ሆኗልና፡፡ በአንዷ ድንግል ሔዋን አለመታዘዝ ሞት
ወደ ዓለም እንደገባ በአንዷ ቅድስት ድንግል ማርያም መታዘዝ እምነትና ሕይወት ለዓለም ሁሉ ሆነ፡፡ /ዘፍ.3፥1-24፣ ሉቃ.1፥38/
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለድንግል ማርያም አክብሮት ምስጋና አገልግሎት እንደቀረበላት
ተጽፎ እናገኛለን፡፡
1. ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር ጸጋና ሞገስን አግኝታለች እግዚአብሔር ከእርሷ ጋር ሆኗል /ሉቃ.1፥28/ ስለዚህም
ለእርሷ አክብሮት አለን፡፡
2. በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ተመስግናለች፡፡ /ሉቃ.1፥29/ ስለዚህም ይበልጡኑ የእርሷ ታዛዥነት የጠቀመን ሰዎች እናመሰግናታለን፡፡
3. በቅድስት ኤልሳቤጥ ተመስግናለት /ሉቃ.1፥14/ እኛም እርሷን አብነት አድርገን መዳናችን በእርሱዋ እሺታ ምክንያት እኛንም ተፈጽሞልናልና እናመሰግናታለን ከፍከፍ እናደርጋታለን፡፡
4. በማኅፀን የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ የሰላምታዋን ድምፅ በእናቱ ማኅፀን ሳለ በሰማ ጊዜ በደስታ ዘልሏል /ሰግዷል/ እኛም
በጥምቀት የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆንን ክርስቲያኖች ለእርሷ በፍቅር የጸጋ ስግደት እንሰግዳለን፡፡ /ሉቃ.1፥43/
5. ጌታችን በልጅነቱም ይሁን በቃና ዘገሊላ ሠርግ ላይ ለእርሱዋ እንደታዘዛት እናነባለን /ሉቃ.2፥51፣ ዮሐ.2፥4/ እኛም
በስሟ መልካም ምግባሮችን በመሥራት ለክርስቶስ ቃል በመታዘዝ “ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ ደስታ የለኝም” እንዳለ
ሐዋርያው (3ዮሐ.1፡3) እንዲሁ የድንግል ፈቃድ ይኸው ነው፡፡ “የሚላችሁን አድርጉ” (ዮሐ.2፥5) ስለዚህም የሚጠበቅብንን በማድረግ
እንታዘዛት፡፡
6. የፍጥረት መዳን በእርሱዋ ይሁንታ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ በመገንዘቧና ይሁንታዋን ለበግለጽ መድኅን ክርስቶስን በመውለዱዋ የሰው ዘር ሁሉ ምላሽ ምን እንደሆነ የተገነዘበች ድንግል ስለራሱ“ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” ብላ ተናገረችው ፡፡ እኛም በልጁዋ በመዳናችንና ከቀድሞ ከፍታችን በላይ እጅግ ስለከበርን
ብጽእት በማለት እናመሰግናታለን፡፡(ሉቃ.1፥48)
በተጨማሪም አንድ ክርስቲያን እኔ የክርስቶስ ልብ አለኝ /1ኛ ቆሮ.2፥16/ የሚል
ከሆነ ክርስቶስ ለእናቱ ያለውን ፍቅርና አክብሮት በመረዳት ለቅድስት ድንግል ማርያም ተገቢውን አክብሮትና ፍቅር የጸጋ ስግደት ይፈጽማል
ነገር ግን የክርስቶስ ልብ የተባለው መንፈስ ቅዱስ ያላደረበት ሰው እንዴት ስለእርሷ መመረጥና ቅድስና ሊረዳ ይችላል? ቅድስት ኤልሳቤጥ
እንኳ የድንግልን ቅድስና፣ የአምላክ እናትነት፣ የእምነቷን ፍጹምነትና
ክብር የተረዳችው በውስጡዋ ያደረው መንፈስ ቅዱስ ከገለጠላት በኋላ ነው፡፡
ሕፃኑ ዮሐንስ መጥምቅም የስድስት ወር ፅንስ በሆነ ጊዜ ለአምላክን እናት ድምፅ በሰማ ጊዜ በመኅፀን በደስታ መዝለሉ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህም
ቅድስት ድንግል ማርያም አክብሮት ፍቅር አይገባትም የምንል ከሆነ መንፈስ ቅዱስ ከእኛ እንደራቀ ተገንዘበን ከድፍረት ኃጢአታችን
እግዚአብሔር እንዲያርቀን እንለምነው፡፡
No comments:
Post a Comment