Wednesday, December 13, 2017

የትርምት ሕይወት በቅዱስ ኤፍሬም(ክፍል ዘጠኝ) ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
04/04/2010
ወደ ቅድስና ሕይወት የሚመሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን አድኖ ማንበብ አንዱ በትርምት ሕይወት ውስጥ የሚኖር ክርስቲያን ጠባይ ነው፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች ክርስትናን በሕይወት ስለኖሩባት በጽሑፎቻቸው ሁሉ ክርስቲያናዊ ሕይወት ምን እንደሚመስል ከዲያብሎስ ጋር በምናደርገው ፍልሚያ ምን ማድረግ እንዳለብን በስፋት ጽፈውልን እናገኛለን፡፡
ቅዱስ ኤፍሬምም ከዲያብሎስ ወጥመድ ለማምለጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በጸሎትና ራስን ሰብስቦ በጥንቃቄ ማንበብ እንደሚገባ ያስተምራል፡፡ ቅዱስ አፍሬም እንደህ ማለቱ ዲያብሎስ አንባብያን የሚጠቅማቸውን ሰማያዊ ዕውቀት ከሚያነቡት መንፈሳዊ መጽሐፍ እንዳያገኙ ተግቶ ስለሚሠራና መልእክቱን አዛብተን በመረዳት ወደ ምንፍቅና እንዲንደረደሩ ስለሚያደርጋቸው ነው፡፡ ስለዚህ የንባብ ሕይወታችን እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግና በማስተዋል መፈጸም እንዳለበት ያሳስባል፡፡ እርሱም ሰይጣን እንዲህ አለ ብሎ በጻፈልን ጽሑፍ ላይ ይህንን እናስተውላለን፡፡
“እኔ ሰይጣን ስንፍናቸውን እንደሰንሰለት ተጠቅሜ ሰዎችን አ
ስራቸዋለሁ፡፡ እነርሱም ሥራ ፈት ሆነው ይውላሉ፡፡ አእምሮአቸውንም ለስሜታቸው መልካም ወደሚመስለው እንዲሳብ አደርገዋለሁ፡፡ ዓይናቸውን ከንባብ ከንፈራቸውን ከመዝሙር መረዳቸውንም ከክርስቲያናዊ አስተምህሮ እመልሰዋለሁ፡፡ ለሚያጠፋና ለማይጠቅሙ ከንቱ ተረቶች ጉጉዎች እንዲሆኑ አደርጋቸዋለሁ፤ ለፍላፊዎች አደርጋቸዋለሁ፡፡ በዚህም ተግባሬ ምንም እንኳ እነርሱ የሕይወትን ቃል የተሞሉ ወይም የተጠሙ ቢሆኑ እንኳ ከዚህ ፈቃዳቸው ፈጥነው እንዲለዩ አደርጋቸዋለሁ” በማለት የሰይጣንን ተንኮል ይገልጸዋል፡፡ በዚህም ሰይጣን እኛን ከቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ ለማውጣት እንዴት እንደሚተጋ ማስረዳቱን እናስተውላለን፡፡ ለዚህም ነው ሌሎች መጻሕፍትን ስናነብ ምንም የማንሆነው ፊታችንን ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ዞር ስናደርግ ግን ጦርነቱን የሚበዛብን፡፡
እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ተፈጥሮአችን በራሱ መጽሐፍ ነው፡፡ ነገር ግን ባለመታዘዝ ምክንያት መንፈስ ቅዱስ በልቡናችን ሰሌዳ ላይ የጻፈውን ቃል ስላቃለልን ሁለተኛ እድል ይሆነን ዘንድ ሁለቱን ኪዳናት ለእኛ ተሰጡን ብሎ ያስተምራል፡፡ይህ አገላለጽ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የማቴዎስ ወንጌልን በተረጎመበት መግቢያ ላይ ገልጾልን እናገኘዋለን፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም እግዚአብሔር አምላክ እናነባቸው ዘንድ ሦስት መጻሕፍትን እንደሰጠን ያስተምረናል እነርሱም ተፈጥሮ፣ ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስት መጻሕፍት በአግባቡና ተጠንቀቀን ያልተጠቀምንባቸው ከሆነ በእኛ ላይ ፍርዱ የከፋ ይሆናል፡፡ ወይም በእነዚህ ሦስት መጻሕፍት እኛ እንዳኛለን፡፡ እነዚህን መጻሕፍት አስመልክቶ ድንቅ በሚባል መልኩ እንዲህ ጽፎልን እናገኛለን፡-
“የእናንተ ጭንቀት መጻሕፍትን ለማንበብ ይሁን፤ በእነርሱ ትገሠጹና በእነርሱ ጠንካራ በሆነው እቅፍ ውስጥ ገብታችሁ ከጥፋት ትጠበቁ ዘንድ መጻሐፍትን ለራሳቸው አድርጉ፡፡ መጻሕፍትን ስታነቡ በውስጣቸው  የተጻፈውን መልእክት በማሰላሰል አእምሮአችሁ ጽሙድ ይሁን በእያንዳንዷ ሰዓትም በውስጡ የሰፈሩትን ታሪኮች አስቡ፡፡ ልጄ ሆይ በልቡናህ የተጻፈውን በማቃለልህ ምክንያት ሁለቱ ኪዳናት ለአንተ የተጻፉ ናቸውና በሕይወት ዘመንህ ሁሉ እነዚህን ከማንበብ አትስነፍ፡፡ በንጽሕና ራስህን ጠብቀህ ትመላለስ ዘንድ እነዚህ ሦስት መጻሕፍት ለአንተ ተሰጥተውሃልና፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም መጻሕፍትን ራሳችንን በምንመለከትበት መስታወትና የምንፈጠርበት ማኅጸን መስሎ ያስተምረናል፡፡
“ወዳጄ ሆይ ሰዎች ምስላቸውን እንደሚመለከቱበት ዓይነት ብሩህ መስታወት የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ከእጅ ባለመለየትህ መልካም አደረግህ፡፡ ይህ መስታወት በፊቱ የቆመውን ምስል መልሶ የሚያሳይ ነው፡፡ ቀለማማ ነገር በፊቱ ቢኖር እርሱን አንዳችም ሳይቀይር መልሶ ያሳያል፡፡ በፊቱ ነጭ ነገር ቢቆም ነጩን መልሶ ያሳየዋል፤ ጥቁር የሆነም ነገር በፊቱ ቢቆም መልሶ ጥቁረቱን ያሳያ... ይህ መስታወት ምንም እንኳ ቃል የማያወጣ ቢሆንም በዝምታው አብዝቶ ይጮሃል፤ ምናልባት አንተ ሕይወት አልባ አድርገህ ታስበው ይሆናል ነገር ግን ጮኾ አዋጅ ያውጃል፡፡ ምንም እንኳ በራሱ የማይንቀሳቀስ ቢመሰለም በዝማሬ ያሸበሽባል፡፡ ማኅፀኑ ብዙ ክፍሎች ያሏቸው መሆናቸውን ማንም ባይረዳ በውስጡ ብዙ የሰርግ ቤቶች አሉበት፡፡ በዚያም ሁሉም መገጣጠሚያዎች ይፈጠራሉ ሁሉም የአካል ክፍሎች በቅጽበት ቅርጻቸውን ይዘው ይሠራሉ፡፡ በዓይን ቅጽበት በማይታመን ፍጥነት ወዲያው ይፈጠራሉ፤ በማለት ይገልጸዋል፡፡ ሰው በእግዚአብሔር አርአያ ተፈጥሮአል ብሎ በመግቢያው የሚያስተምረው መጽሐፍ ቅዱስ እኛ ምንም መምሰል እንዳለብን ውበታችንን ጉድፋችንን  እርሱ መስታወት ሆኖን ያሳየናል፡፡ ከእርሱም ተምረን በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት የተወደደ ሰብእናን ገንዘባችን አድርገን እንመላለስበታለን፡፡ እንዲህም ስለሆነ ነው ቅዱስ ኤፍሬም መጽሐፍ ቅዱስን መስታወትና ማኅፀን ማለቱ፡፡  
እንዲሁም በትርምት ሕይወት የሚኖሩ ወገኖች ከተፈጥሮም ይማሩ ዘንድ ያስተምራል፡-
“ተፈጥሮ ለአንተ መጽሐፍህ ትሁንህ፣ ሁሉም ፍጥረታት ለአንተ የመማሪያህ ገበታ ይሁኑህ፤ ከእነርሱ ሕግጋትን ተማር በእነርሱ በመጽሐፍ ያልሰፈሩትን ሕግጋት አስተውል፡፡ ፀሐይ በዙረትዋ ከድካምህ የምታርፍበት ጊዜ እንዳለ ታስተምርሃለች፤ ሌሊትም በጸጥታ በመሆን ለድካምህ ገደብ እንዳለው ጮሃ ትናገራለች፡፡ ምድርና በምድር ላይ የሚበቅሉ ዕፅዋት ሀሉ ለሁሉ ወቅት ወቅት እንዳለው ድምፅ ሳያወጡ ያስተምሩሃል፡፡ በክረምት የምትዘራውን ዘር በበጋ ትሰብስባለህ፡፡ እንዲሁ በዚህ ምድር በጽድቅ ሆነ በክፋት የዘራኸውን ሥራ በትንሣኤ ትሰብስባለህ፡፡ አእዋፋት በቀን ዙረታቸው ስስታሙን ሰው ይገሥጻሉ፡፡ የሌላውንም ጎተራ አስፈራርተው የሚነጥቁትን ይገሥጻሉ፡፡ ሞት በራሱ ለሁሉ ነገር ፍጻሜ እንዳለው የሚገሥጽ አይደለምን?” በማለት ከተፈጥሮ እንማር ዘንድ ያሳስበናል፡፡
በዚህ መሠረት አንድ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ሃሳብና ፈቃድ ምን እንደሆነ ያውቅ ዘንድ በውስጥም ሆነ በውጭ ብዙ አሰተማሪ ነገሮችን በዙሪያው እግዚአብሔር እንዳኖረለት ሊረዳ ይገባዋል፡፡ ይህም አእምሮ ለከንቱ ነገር እንዳይተጋና ለሰይጣን ወጥመድ እንዳይጋለጥ አጥር ቅጥር ሆኖ እንደሚጠብቀው መረዳት እንችላለን፡፡
ፍቅር  
ለቅዱስ ኤፍሬም ፍቅር ማለት ልክ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ “አንድ አካል መሆን” ማለት ነው፡፡ ይህን በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮ ላይ እናገኘዋለን፡፡ ይህም አንዱ የአካል ክፍል ከሌላው የአካል ክፍል ጋር  ፍጹም አንድ እንደሆነ ምንም የተለያየን ብንሆን በልዩነታችን ውስጥ ያለ አንድነትን ፍቅር ይለዋል፡፡ ይህ ዓይነት ፍቅር የሚመጣው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ሥጋ በነፍስ ምክንያት አንድ እንድትሆን ነፍስ ስትለየው እንዲፈርስ እንዲበታተን የአካል ክፍሎቹም ወደ አፈርነት እንዲለወጡ እንዲሁ በክርስቶስ አንድ አካል የምንሆነው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከተለየን እንደ በድን እንቆጠራለን፡፡ በዚህ ስፍራ ቅዱስ ኤፍሬም እያወሳ ያለው ፍቅር በመንፈስ ቅዱስ የምናገኘውን ፍቅር ነው፡፡
ይህን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡-
“በአካል ክፍሎች መካከል ምንም ዓይነት ክፋትና ቅናት የለም፡፡ በፍቅር በመሆን ጆሮአቸውን ወደ እርሱ ያቀቅራሉ፡፡ በእርሱ አስገምጋሚ ድምጽ ይጎበኛሉ፡፡ የአካል ሕዋሳቱ ጠባቂያቸው ራሳቸው ነው፡፡ እርሱም በሁሉ አቅጣጫ ይመለከታል” ይላል፡፡
ስለዚህ አንድ ክርስቲያን የትርምትን ሕይወት እየኖርኩ ነው ካለ የግድ በጥምቀት የክርስቶስ የአካል ክፍል የሆነውን ወንድሙን ሊወድድ ይገባዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም የገዛ አካሉን የማይወድ የለም እንዲል ከእርሱ ጋር አንዱን የክርስቶስን አካል የሚያገለግል ሕዋስ ነውና ሊወድደው ግድ ነው፡፡ ያለበለዚያ ክርስቲያን መሆኑን ዘንግቶታል፡፡ በዚህ ፍቅር ውስጥ ዘር ቀለም ጎሣ ወዘተ ቦታ የላቸውም፡፡ በመላእክት ሥርዓት የሚኖር በክርስቶስ እንደ አንድ ሰው በተቆጠረ ክርስቲያን ዘንድ ፍቅር መጥፋቱ አሳፋሪ ነው፡፡ ስለዚህ በትርምት ሕይወት ውስጥ የሚኖር ክርስቲያን በመንፈስ በመገኘት ወንድሙን እንደራሱ አካል አድርጎ ሊወድደው የሚገባውን ሊያደርግለት ፍቅርና አክብሮት ሊሰጠው ትሕትናን ሊያሳየው ይገባል፡፡
እንዲህም ስለሆነ ቅዱስ ኤፍሬም፡-“እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ እንደ ችሎታህ መጠን ውደደው፡፡ እግዘአብሔርን ስለመውደድህ ምልክቱ ደግሞ ወንድምህን መውደድህ ነው፡፡ ወንድምህን ብትጠላው ጥላቻህ በእግዚአብሔር ላይ ነው፡፡ በቁጣ ውስጥ እያለህ በእግዚአብሔር ፊት ለጸሎት መቆምህ እግዚአብሔርን እንደመሳደብ ይቆጠርብሃል” በማለት ያስተምራል፡፡
ከቁጣና ከጥላቻ ይልቅ ክርስቲያኖች በአንድነትና በፍቅር በመሆን ፍቅርን ላለበሳቸው ክርስቶስ ምስጋናን ያቀርቡ ዘንድ ይመክራል እንዲህ ይላል፡- “ወዳጆቼ ሆይ ኑ ወደዚህ ቅረቡ ፍቅራችሁን እንደ ጥና አድራጋችሁ ራሱን ስለ እኛ የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበውን ክርስቶስን መስላችሁ ምስጋናንና ጸሎትን ለእርሱ አድርሱ” በማለት ይመክራል፡፡



ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment