Thursday, December 7, 2017

የትርምት ሕይወት በቅዱስ ኤፍሬም (ክፍል ስምንት)


በመ/ር ሽመልስ መርጊያ
29/03/2010

ለቅዱስ ኤፍሬም ድህነት ማለት ሁሉ የሚገኝባት ሰማያዊ ግምዣ ቤት ናት፡

“በዚህች የከበሩ ነገሮች ሁሉ በሚቀመጡባት ግምዣ ቤተ ተደነቅሁ፤ በውስጧ ያሉ የከበሩ ሀብታት ሁሉ ከሁሉ ይልቅ ክቡራን ናቸው፡፡  ከሀብቶቿ ሊያጎልባት የሚችል አንድም ሰው የለም፡፡ ለዚህች ግምዣ ቤት የብዕሏ ምንጭ ድህነት ናት ፡፡ ነገር ግን ሰዎች በዙሪያዋ ከትመውባታል ከዚህች ግምጃ ቤት ሃብትም ይናጠቃሉ፡፡ ንጥቂያ እንደመሆኑ መጠን ብዙዎች ባለጠጎች ሆኑባት፡፡ በዚች ሕይወት ለጸኑትና አጥብቀው ላሿት ሀብቷ በኃይልና በብዛት ይፈሳል” በማለት ድህነትን የሰማያዊ ሀብት ግምዣ ቤት እንደሆነች ሲሰብክ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ከዚህ ሀብት ይናጠቁ ዘንድ ክርስቲያኖች ክርስቶስን በሁሉ ሊመስሉ ይገባቸዋል፡፡ እርሱ ነውና የጸጋ ሁሉ ግምጃ ቤት ባለቤቱ፡፡ እርሱን ስንመስል ከእርሱ ዘንድ ባለ ሰማያዊ ሀብት ባለጠጎች እንሆናለን፡፡ የዚህንም አላፊ ጠፊ የሆነውን ዓለም ሀብት እንድንንቀው ያደርገናል፡፡ በዚህ ሕይወት ከተገኘንም መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን ይመራዋል፡፡ እንዴት መኖር እንዳለብንም እወቀቱ ከእርሱ እናገኛለን፡፡

 በትርምት ሕይወት ውስጥ በመኖር ሕይወታችንን የምንመራ ከሆነ ራሳችንን፣ ቤተሰባችንን በአግባቡ እንዴት መምራት እንዳለብንና ክርስቶስ ከእኛ የሚሻው ሀብት በዝቶልን እናገኘዋለን፡፡ ይህም ጌታችን “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል”(ማቴ.6፡33) ያለው ቃል በእኛ የሚፈጸምበት ነው፡፡
እንዲሁም በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በመንግሥት አስተዳደር ላይ በመሪነት ሥፍራ ብንቀመጥ የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ከእኛ ስለማይለይ በአግባቡ ሓላፊነታችንን መወጣት እንችላለን፡፡ እንዲህም ስለሆነ ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ በማለት ይመክረናል፡-
“እናንተ ክርስቲያኖች ሆይ ድህነትን የምትወዷት ሁኑ ድሃም ለመሆን ተመኙ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ካሉአችሁ የመንግሥቱ ወራሾች ትሆናላችሁ” ይላል፡፡  ይህ በእርግጥ እውነት ነው፡፡ ድህነት ማለት ክርስቶስን መምሰል ከሆነ ክርስቶስን ለመምሰል ደግሞ የትርምት ሕይወት ያስፈልገናል፡፡ በትርምት ሕይወት የተመላለስን እንደሆነ ደግሞ በላይ ያለውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ወራሾች እንደምንሆን የማያጠራጥር ነው፡፡ ድህነት ማለት ለቅዱስ ኤፍሬም ተመጽዋች መሆን ማለት አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው” የሚለውን ቃል የሕይወት መመሪያ አድርጎ መኖር ማለት ነው እንጂ፡፡ ይህን ሲያጠነክር ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ይላል፡- “ለአንተ በግንባርህ ወዝ የምታገኘው የእለት እንጀራህ በቂ ይሁንህ፡፡ ቀኒቱ የሰጠችህ በረከት የፍላጎትህ  ልኬት ይሁንህ” ይላል፡፡
እንዲሁም “ምንም ባለጠጋ ብትሆን ሥራን ከመሥራት አትለግም ሥራ ፈት ሰው ከስንፍናው የተነሣ  እጅግ ብዙ  ኃጢአቶች ያገኙታልና” ብሎ ይመክራል፡፡ ስለዚህ ለቅዱስ ኤፍሬም ድህነት ማለት ክርስቶስን በውጪም ሆነ በውስጥ የምንለብስበትና ክርስቶስ በውስጥ የጸጋ ሁሉ ግምጃ ቤት እንደሆነ በውጪ ሲታይ ግን ደሃ እንደሚመስል እኛም እርሱን መስለን መኖር ማለት ነው፡፡
የትርምትን ሕይወት ይኖሩ የነበሩ ቅዱሳን በውጪ ሲታዩ ድሆች ይመስላሉ ነገር ግን ከሌሎች በእጅጉ የሚልቅ ሀብት ባለቤቶች ነበሩ፡፡ ይህን ግልጽ ለማድረግ ቅዱስ ኤፍሬም ኤልያስንና አልሳዕ እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“በድህነት ሕይወት የሚኖሩ ኤልያስና ኤልሳዕ በላይ ያለውን ሰማያዊ ሀብት ወደዱ፡፡ ድሃ የሆነው እርሱ ድሃ ለሆነው ወዳጁ ከሁሉ በእጅጉ የሚልቅ ሀብትን ሰጠው፡፡ እናንተም በውጭ ሲታይ ደሃ የሚመስለውን በውስጥ ግን የጸጋ ሁሉ ግምጃ ቤት የሆነውን ክርስቶስን ወዳችሁታልና እርሱ የመንፈስ ቅዱስ በገናዎች ትሆኑና ስለ እርሱ መልካምነት በነፍሳችሁ ምስጋናን ታቀርቡ ዘንድ የቃሉን ጅረት በእናንተ ላይ አፈሰሰ፡፡ እናንተን የጸጋው ግምጃ ቤት ያደርጋችሁ ዘንድ የወደደ እርሱ የተመሰገነ ይሁን” ይላል፡፡
ከዚህም ቃሉ የምንረዳው ድህነት ማለት የትርምት ሕይወት ማለት እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ከትርምት ሕይወት የምናገኘውን ሀብት ጠብቀን እንቆይ ዘንድ እንዲህ በማለት ይመክረናል፡-
“ባለጠጋ ሀብቱ እርሱን ከእንቅልፍ የራቀ እንደሚያደርገው እንዲሁ እናንተም እንደ ባለጠጋው ንቁሃን ሁኑ፡፡ ባለጠጋ ሰው ዉሻው እንኳ ተኝቶ ሲያድር እርሱ ግን ሀብቱን ሲጠብቅ ያድራል” ይላል፡፡ እንዲህ ሲል ሰማያዊው ሀብት (እርሱም ክርስቶስን መስለን የምንኖርበት ነው) ከእኛ እንዳይወሰድ ሁል ጊዜም ቢሆን ንቁሃን ሆነን በትጋት መጠበቅ እንዳለብን ሲያሳስብ ነው፡፡ ይህም በጸሎት፣ በምንባብ፣ በተመስጦ ሕይወት፣ ራስን ወደ ውስጥ በመመልከት የሚፈጸም ነው፡፡

የትርምት ሕይወት ተግባራት በቅዱስ ኤፍሬም ጽሑፎች ውስጥ

ደጋግመን እንዳልነው የቅዱስ ኤፍሬም የትርምት ሕይወት ክርስቲያኖችን እንዴት ክርስቶስን ወደ መምሰል ማምጣት እንደሚቻል የሚያስተምር ነው፡፡ በዚህም ክፍል አንድ ክርስቲያን እንዴት በተግባር ክርስቶስን መምሰል እንደሚችል እንመለከታለን፡፡

ጸሎት

በትርምት ሕይወት ለሚመላለሱ ክርስቲያኖች ጸሎት አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነውን ክርስቶስን ለመመስል ትልቅ ሚና አለው፡፡ ጌታችን ጠባቡና ሰፊው መንገድ ብሎ ያስተማረውን ትምህርት ቅዱስ ኤፍሬም ጸሎት ሰጥቶ ተርጉሞት እናገኘዋለን፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“ወደ ሕይወት የምትወስደዋ ጎዳና ጠባብ ናት ወደ ጥፋት የምትወስደዋ ጎዳና ሰፊ ናት፡፡ ጸሎት አንድን ሰው ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዲገባ የማብቃት አቅም ያላት ጠባቡዋ ጎዳና ናት፡፡ ከኃጢአት ንጹሑ ሆነው የሚቀርቧት ጸሎት ፍጹም ሥራን ትሠራለች” በማለት ይገልጻታል፡፡
ስለዚህም በትርምት ሕይወት ውስጥ ያሉትን በጸሎት እንዲተጉ አጥብቆ ይመክራቸዋል፡፡ የእርሱም ብዙዎቹ መጻሕፍት የጸሎት መጻሕፍት ናቸው፡፡ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም አስተምህሮ ጸሎታችን ከኃጢአት ንጹሕ በመሆን በትጋት፣ በመረዳትና በተመስጦ ሆነን ልናቀርበው ይገባናል፡፡
“ንጹሕ የሆነውን ክርስቶስን የመሰለ ክርስቲያን በጨለማ የነቃና ለጸሎት የሚተጋ ሰውን ይመስላል፡፡ ይህ ሰው በጨለማ ውስጥ ቢሆንም በሰው በዓይን በማይታይ ብርሃን ተከብቦ ይታያል፡፡ ክፉ የሆነ ሰው ግን በሚታየው ብርሃን ውስጥ ሆኖ የጨለማው ልጅ እንደመሆኑ መጠን የእርሱን ግብር ይፈጽማል፡፡ ስለዚህ ይህ ሰው በውጭ ሲታይ በብርሃን ውስጥ ነው በውስጥ ግን የሚዳሰስ ጨለማ ጋርዶታል፡፡ ተወዳጆች ሆይ እንደዚህ ዓለም ልጆች ዓይኖቻችሁ በዚህ ዓለም ብርሃን መመልከት በመቻላችሁ እንዳትታለሉ ተጠንቀቁ፡፡ በዚህ ዓለም ዓይናማ የሆነ ሰው እይታ ወደ ቅድስና የሚያመጣ እይታ አይደለም፡፡ ሲመለከት በጥንቃቄ አይመለከትም፤ ይመለከታል ግን አንቀላፍቶአል፡፡ ምልከታው ጤናማ አይደለም እይታውም ሁሉ ምድራዊ ነው” በማለት ያስተምራል፡፡ እንደውም ቅዱስ ኤፍሬም በወንጌላት ትርጓሜው ላይ ጌታችን “የሰውነት መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ!” የሚለውን ቃል ለጸሎት ለጦም፣ እንዲሁም ለምጽዋት ሰጥቶ እነዚህ ያሉት ዐይኖቹ ብርሃን ናቸው፡፡ በጨለማም አይመላለስም፡፡ እነዚህ የሌሉት በጨለማ ይመላለሳል፡፡ ከዚህ የከፋው ግን በከንቱ ውዳሴ ሆኖ የሚመላለሰው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰው ለሰውነቱ ብርሃን እንዲሆኑ የተሰጡት እነዚህ ምግባራትን ከንቱ ወዳሴን ሽቶ የሚፈጽም ሰው ከጨለማም ወደ ጽኑ ጨለማ የወደቀ ሰውን ይመስላል ብሎ ሲተረጉመው እናገኘዋለን፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ለሥራዎቹ ሁሉ ቁልፉ ጸሎት ነው፡፡ ሁሉም መጻሕፍቶቹ በጸሎት የጣፈጡ ናቸው፡፡

ጦም

በትርምት ሕይወት ውስጥ ለሚኖር ሰው ጦም ከእግዚአብሔር ጋር ላለው ሕይወቱ ትልቅ ሥፍራ አለው፡፡ ለቅዱስ ኤፍሬም ደግሞ ጦም የተለየ ቦታ አለው እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ጦም ነፍስን ታፋፋለች፡፡
እንዲህም ስለሆነ፡- “እርሱ ጌታችን የጠፉትን ነፍሳት ለማጥመድ የመጣ አሣ አሥጋሪ ነበር ፡፡  ቀራጮችና አመንዝሮች ወደ ስካርና ሥርዐት አልበኝነት ሲፋጠኑ ተመለከታቸው ፤ ሥጋንም ከሚያወፍር የማዕድ ቦታ እነርሱን በማሥገር ነፍስን ወደሚያወፍር ጦም ሊያሸጋግራቸው የቃሉን መረብ በማዕዱ ውቅያኖስ ላይ ጣለው” በማለት ይቀኛል፡፡
 የጦምንም አስፈላጊነት ሲነግረን እንዲህ በማለት ይመክረናል፡-“የዳንኤልን ጦም በመሰለ ጦም ስስትን ድል ንሱት፤ የዝሙት ጾርም በዮሴፍ ድል እንደተነሣ እንዲሁ እናንተ (በጦም) በሰውነታችሁ የሚቀጣጠለውን የዝሙት ጦር ድል ንሱት”
ጦም ከምድራዊ ምግብ ተከልክለን ሰማያዊውን ምግብ ከመንፈስ ቅዱስ የምንመገብባት፣ ከውድቀት በፊት አዳም ይኖርባት በነበረችው ሕይወት የምንኖርባት፣ በዚህ ምድር ሳለን የትንሣኤን ሕይወት የምናጣጥምምባት፤ የንስሐ፣ የእንባ፣ የተመስጦ፣ ራስን የመመልከት ሕይወትን ገንዘብ የምናደርግባት፣ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ወደ አእላፍት መላእክት ኅብረት የምታገባ በር ናት፡፡ ጸሎት ደግሞ እንደ ፋኖስ ሆነ የልቡናችንን ዓይኖች የምታበራ፣ በትሕትና በአምላክ ፊት እንድንቆም የምትረዳ፣ የነፍስን ጸጥታ የምትሰጥ፣ በሰው ላይ እንዳንፈርድ የምትከለክለን፣ እንደ ጦም ሁሉ በትሕትና እንድንመላለስ የምታበቃን ናት፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ መጦም ባይችል እንኳ በመጠኑ ተመግቦ በጦም ሰዓትም ከጦም ተጠቃሚ እንዲሆን በማስተዋልና እነዚህን በረከቶች ለማግኘት በማሰብ ሊጦም ይገባዋል፡፡
ይቀጥላል…….

No comments:

Post a Comment