በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
23/03/2010
የቅዱስ ኤፍሬም መንፈሳዊው ሕይወት የሚጀምረው የንጽቢኑ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን ከቃል ኪዳን ልጆች ኅብረት ጋር ካቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ ለቅዱስ ኤፍሬም በቃል ኪዳን ልጆች ይተገበር የነበረው የትርምት ሕይወት እርሱን ከእግዚአብሔር አምላኩ ጋር እንዲጣበቅና ልዩ ልዩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥልቀት ለማንበብና ለማጥናት ረድቶታል፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ ኤፍሬም እግዚአብሔርን የሚያፈቅር ክርስቲያን ሆነ፡፡ እስቲ ልዩ የሆኑ የቅዱስ ኤፍሬም መንፈሳዊ ጠባያት የተወሰኑትን እንመልከት፡-
ጸሐፊነቱ
ከስበከት ሥራው ጎን ለጎን መንጋውን በመንፈሳዊው እውቀት የበሰሉ እንዲሆኑ ለማድረግ ቅዱስ ኤፍሬም ስብከቶችን፣ መዝሙራትንና ትርጓሜያትን ለመንጉቹ ይጽፍላቸው ነበር፡፡ ጽሑፎቹ ሁሉ የትርምት ሕይወት ተጽእኖ ስላለባቸው በየጣልቃቸው ጸሎታት አሏቸው፡፡ ወይም ሙሉ ለሙሉ የጸሎት መጽሐፍ ናቸው፡፡ በሚጽፍበትም ጊዜ ራሱን በእግዚአብሔር ፊት እንደቆመ በማሰብ ነው፡፡ መንጎቹን ሳይሰለች የሚጠብቅ ስለሆነ በሕይወቱ ጌታችን ለቅዱስ ጴጥሮስን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው”(ዮሐ.21፡15) የተናገረውን ቃል ያስታውሰናል፡፡ ምክንያቱም በክርስቶስ ፍቅር ሆኖ እግዚአብሔርን በመፍራት መንጋውን ይጠበቅ ስለነበረ ነው፡፡ እርሱ መንጋውን ሲጠብቅ ሁሉን ነገሩን ሰጥቶ ነበር፡፡
የሴቶችን እኅቶቻችን መበት ተሟጋች ነበር
ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ቅዱስ ኤፍሬምን የሴት ልጆች ጠበቃ ይለዋል፡፡ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም አስተምህሮ ሴቶች ከወንዶች ጋር በክርስቶስ እኩል ናቸው፡፡(ይህ ግን ከ አለቦ እምነት(ሴኩላሪዝም) የተለየ የተፈጥሮን ሕግ የማይጥስ ሁሉም በተሰጠው ተፈጥሮዊ ሥርዓት የሚስተካከልበት እኩልነት ነው) እርሱ ሴቶችን ከወንዶች እኩል በቤተ ክርስቲያን ዝማሬን እንዲያቀርቡ ያደርግ ነበር፡፡ መዝሙራትን አዘጋጅቶ ካበቃ በኋላም ዝማሬውን እንዲያቀርቡ እድሉን የሚሰጠው ለሴት ክርስቲያኖች ነበር፡፡
በትርምት ሕይወት አስተምህሮው ከቅዱስ ጳውሎስ ይልቅ ቅድስት ድንግል ማርያምን ምሳሌ አድርጎ ማንሣት ይመርጣል፡፡ ለምሳሌ፡- “ቅዱስ የሆነው እርሱ በሥጋ ከድንግል ማኅፀን አደረ በመንፈስ ከነፍሷ ውስጥ አደረ፡፡ እርሱን ጸንሳ የወለደች ድንግል የጋብቻን አልጋ አልመረጠችም፡፡ ስለዚህ እናንት ደናግላን ሆይ የእርሱ ማደሪያ በሚያደረገው ሥጋችሁና ነፍሳችሁ ኃጢአትን አትፈጽሙ፡፡ ይህን የተረዳች ድንግል ለወንድ መታጨትን አልፈቀደችም፡፡ እርሱ ጌታችን ንጹሐን ደናግላን በሆኑት ሰውነት ማደሪያውን ያድርግ ዘንድ ይፈቅዳልና እነርሱም ይረዱታል” የሚል እናገኛለን፡፡
ሴቶችን ለመዝሙር ለማንቃትም፡- “እናንት የአሕዛብ ደናግላን በተፈጥሮ በምትመስላችሁ ድንግል ማርያም በኩል አዲስ የሆነ ምስጋናን ለአምላካችሁ አቅርቡ አንደበታችሁም ለምስጋና ክፈቱ” ብሎ ጽፎልን እናገኛለን፡፡
ከዚህ የተነሣ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ቅዱስ ኤፍሬምን “ለሴቶች ሁለተኛው ሙሴ” በማለት ይጠራዋል፡፡ ብዙ የዝማሬ ድርሳናቱ ለሴት ዘማርያን የተዘጋጁ ሲሆኑ በቅኔዊ ድርሰቶቹ አብዝቶ የሴትን ተፈጥሮ አብዝቶ ይጠቀማል፡፡
ለምሳሌ፡- “ጌታ ሆይ ያንተ በሆኑት ስለ እኔ ቅናትን ቅና፤ እኔ ለአንተ የታጨው ነኝ ሐዋርያት ለአንተ እሆን ዘንድ አጩን፤ አንተም ስለ እኔ ቀናተኛ እንደሆንህ ነገሩኝ፡፡ የባሎች ቀናተኝነት ለሚስቶች ንጽሕና እንደ ግንብ እንደሆነ የአንተም ቅናት ለእኔ እንዲያ ይሁን” የሚል እናገኛለን፡፡
ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ጠቀሜታ ሲጽፍም በሴት አንቀጽ እንዲህ ይላል፡-
ብሩህ የሆነውን መስታወት(መጽሐፍ ቅዱስ) ከእጅህ ስላልተለየ መልካምን አደረግህ ይህ መስታወት(መጽሐፍ ቅዱስ) ቆነጃጅቶች ቁንጅናቸውን ጠብቀው ይመላለሱና አንድም የቆሻሻ ነቁጥ እንዳይኖርባቸው ያግዛቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተፈጥሮ ከሰጣቻቸው ውበት ላይ እንደ ምርጫቸው ውበት ጨምረው ራሳቸውን ያስጌጡ ዘንድ ይመራቸዋል፡፡ የዚህ መጽሐፍ ማኅፀን እንደ የወገኑ ልዩ ልዩ የሰርግ ቤቶች ያሉት ሲሆን በዚህ ማኅፀን ውስጥ በማይታመን ፍጥነት እያንዳንዱ መገጣጠሚያው በልዩ ልዩ ቅርጾች ይዘው ይፈጠራሉ፡፡
አንድ በቅዱስ ኤፍሬም ሥራዎች ላይ ጠለቅ ያለ ጥናትና መጻሕፍትን የጻፈ ምሁር ስለ ቅዱስ ኤፍሬም ሲናገር እንዲህ ይላል፡- “የቅዱስ ኤፍሬም መዝሙራት በተለይ ለሴት ዘማርያን የተደረሱ ናቸው፡፡ እርሱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር ሲነሣ በሴት አንቀጽ መናገርን ይመርጣል፡፡ በቅኔአዊ ድርሰቶቹም በብዛት በሴት አንቀጽ መጻፍን ይወዳል”
ቅዱስ አፍሬም ለድሆችም ጠበቃ ነው፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም ስለድሆች በእጅጉ የሚቆረቆር አባት ስለሆነ ክርስቲያኖች ድሆችን እንዳይረሱ አጥብቆ ይመክር ነበር፡፡ “የደኃውን ቃል አታቃል እንዲረግምህም ምክንያት አትሁነው፡፡ ልብሱ አድፎ ካየህ እጠብለት በነጻም ገዝተህ ስጠው፡፡ በእርሱ ፊት ማዕድን አዘጋጀህለትን እነሆ እግዚአብሔር አብ ከእርሱ ተመገበ ክርስቶስም ካቀረብከው መጠጥ ጠጥቶ ረካ መንፈስ ቅዱስም በአንተ ሥራ ደስ ተሰኘ” ብሎ ለድሆች ማድረግ ማለት ለሥላሴ ማድረግ እንደሆነ ያስተምራል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ድሆችን ለማገልገል የሚተጋ አባት ነበርና ሕልፈተ ሕይወቱም የተፈጸመው በኤዲሳ (ኡር) በወረረሽን የታመሙትን ሕመምተኞችን ሲረዳ በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም መልእክቱን ለማስተላለፍ የፍልስፍና ቃላትን አይጠቀምም
እርሱ ቅዱስ ኤፍሬም ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ ከመናፍቃንና ከሐዲያን ለመጠበቅ ሲል ፍልስፍናንና ለንግግር የከበዱ የፍልስፍና ቃላትን አይጠቀምም፡፡ ከዚህ ይልቅ በመንፈሳዊው ቅኔ የተዋዛ ትምህርትን በመጠቀም የተቃወመ ሳይመስል የሰውን ሕሊና ማርኮ ወደ ትክክክኛው አስተምህሮ የማምጣት ተሰጥዖ ነበረው፡፡ ቢሆንም ግን በቀጥታ መናፍቃንንና ከሃዲያንን የተቃወመባቸው ድርሰቶች የሉትም ማለት አይቻልም፡፡ እንዲያም ቢሆን ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡
ምዕራፍ ሦስት (ዋናው የትምህርቱ ክፍል)
የትርምት ሕይወት እንደ ቅዱስ ኤፍሬም አስተምህሮ
የቅዱስ ኤፍሬም የትርምት ሕይወት አስተምህሮ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሰጠውን ትምህርት መሠረት ያደረገ ሲሆን በዚህ ከግብጻውያን የምንኩስና ሥርዓት የተለየ ያደርገዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች፡- “ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፥ አንዱ እንደዚህ ሁለተኛውም እንደዚያ፡፡ ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ፦ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው”(1ቆሮ.7፡7-8) ብሎ ጽፎልናል፡፡
እንደ ቅዱስ ጳውሎስ የድንግልና ሕይወት ልብ ሳይከፈል የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ተመራጭ የሆነ ሕይወት ነው፡፡ ቢሆንም ግን የትዳር ሕይወት እግዚአብሔርን ደስ አያሰኘውም እያለን አይደለም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን ለማገለግልና ፈቃዱን ለመፈጸም ብዙ መሰናክሎች አሉት ሲለን እንዲህ እንዳለ አንረዳዋለን፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም አንድ ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ እስከ ጋብቻ ድረስ ክርስቶስን አብነት አድርጎ በድንግልና ሕይወት ሊመላለስ ይገባዋል ብሎ ያስተምራል፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ለመኖር የትርምት ሕይወትን ገንዘቡ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ስለዚህ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮ ለአንድ ክርስቲያን የትርምት ሕይወት አንዱ የሕይወቱ ክፍል እንደሆነ ሊረዳ ይገባዋል፡፡
ይህን ሕይወት ለመረዳት የሕይወታችን መሪ የሆነውን የጌታችንን የመድኀኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መዋዕለ ሥጋዌ መመለክቱ ይረዳናል፡፡ ጌታችን ቤተ ክርስቲያንን በጥምቀት ለራሱ ከማጨቱ በፊት ወይም በመስቀል ላይ በደሙ ዋጅቶ ከጎኑ በፈሰሰው ቅዱስ ውኃ አንጽቶ የራሱ ከማደረጉ በፊት ብቻውን ተመላልሶአል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በደሙ ቤተ ክርስቲያን ለእርሱ ትሆን ዘንድ አጫት፡፡ እርሱ ራሷ ሲሆን እርሷም አካሉ ሆነች፡፡ ይህን አስመልክቶም ዮሐንስ መጥምቅ “ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ፡፡” አለ፡፡(ዮሐ.3፡29)
ቅዱስ ኤፍሬም ደግሞ፡-
“በሙሽራው በፊቱ ይሄዳል ለተባለውና ድምጽ ለተሰኘው ራሱ በገለጠ ጊዜ ዮሐንስ ቦታውን ለእርሱ በማስረከብ እንዲህ አለ፡- ይህ ወደ ጥምቀቱ የመጣው ስለ እርሱ የተነጋገርኩለት ሁሉን የሚያጠምቀው እና ራሱን በዮርዳኖስ ባሕር የሚገልጥ ነው ያልኩለት ነው” ብሎናል፡፡ ሙሽራው ለእርሱ ትሆን ዘንድ ያጫት ሙሽሪት ማን ናት? ለሚለው ጥያቄ ቅዱስ ኤፍሬም ሲመልስ፡-
“የንጉሥ ልጅ ቤተ ክርስቲያንን ደክማ ባያት ጊዜ ለራሱ ትሆን ዘንድ አጫት፤ ፍቅሩንና ታማኝነቱን አቀመሳት፤ ማንም ሊለየው በማይችል የፍቅር ማሠሪያ ከእርሷ ጋር አንድ አካል ሆነ፤ እነሆ ይህቺ ሙሽራ በንጉሥ ቤተ መንግሥት በክብር ተቀመጠች በንጉሥ ማጌጫም አጌጠች፡፡ ይህችን ሙሽሪት የፋሲካ ወር አገለገለቻት በአበቦችም አስጌጣት፡፡ የትንሣኤ ጌታ የሆንህ ጌታችን ሆይ ክብር ላንተ ይሁን” ብሎ ይቀኛል፡፡
ይህችን ሙሽሪት ዮሐንስ መጥምቅ ለጌታ ትሆን ዘንድ በንጽሕና አስጌጣት እርሷም ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ኤፍሬም፡-
“ “ቃል” “ድምጽን” እርሱ የሚሄድበትን ጎዳና ያቀናና ለእርሱ የምትሆነውን ሙሽሪትን ከውኃ ውስጥ ከመውሰዱ በፊት እርሱን ለመቀበል የተዘጋጀች ትሆን ዘንድ ከእርሱ በፊት አዋጅ ነጋሪው አድርጎ ላከው” ይላል፡፡
ከዚህ ተነሥተን ጌታችን ብቻውን የሆነበት ጊዜ ነበር ከቤተ ክርስቲያንም ጋር አንድ አካል የሆነበትም ጊዜ ነበረ፡፡ እንዲህ ስንል ግን በዓለማዊ መረዳት አይደለም፡፡ ከቤተ ክርስቲያንም ጋር የነበረው ጋብቻ መንፈሳዊ ጋብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ በመንፈሳዊ ጋብቻ የሥጋ ድንግልና ከጉዳይ አይገባም፡፡ በመሆኑም እርሱ ጌታችን ቤተ ክርስቲያን የእርሱ ከማድረጉ በፊትም ሆነ በኋላ እንደ እናቱ ድንግል ነው፡፡ ምክንያቱም ጋብቻው መንፈሳዊ ነውና፡፡
እንዲህ ዓይነት ድንግልናን ቅዱስ ይስሐቅ ለአገቡትም ሲሰጥ እናያለን፡፡ እንዲህ ይላል፡- ትዳር የድንግልና ሕይወትን አያጠፋም፡፡ በሕግ የሆነ ተራክቦ የድንግልናን ሕይወት አያጠፋም፡፡ የሕግ ውጪ የሆነ ተራክቦ ግን የድንግለናን ሕይወት ያጠፋል” ይላል፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም አማናዊቱ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ እርሷ ለአብ የታጨች ናት፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ይህን አስመልክቶ “ሙሽሮች ከሙሽሮቻቸው ጋር ደስ ይበላቸው፡፡ እናቱ ቅዱስ ለሆነው የታጨለት ልጅ የሆነው ሕፃን ብሩክ ይሁን፡፡ እርሱ በተገኘበት ወይኑ ድንገት ባለቀ ጊዜ አንደገና ለሁሉ የሚበቃ ወይንን አበርክቶ የሰጠበት ያ የሠርግ ቤት ብሩክ ይሁን” እንዲል፡፡
በዚህ የቅዱስ ኤፍሬም ቃል መሠረት ቅድስት እናታችን ሙሽሪት መሰኘቷን እናስተውላለን፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ለአንዱ ለክርስቶስ የታጭ ሙሽሪት ናት፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታን ከመውለዷም ከወለደችም በኋላ ድንግል እንደሆነች እንዲሁ በጥምቀት መንፈሳዊ ልደትን የተወለዱ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ቢያገቡም ባያገቡም ደናግላን ይባላሉ፡፡ ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ኤፍሬም፡- “ስምዖን በመረቡ አጥምዶ ዓሣትን ወደ ጌታ አቀረባቸው ሊቀ ካህናት የሆነው እርሱ ጌታችንም ከውኃ ያገኛቸውን በስምዖን እጅ ሳሉ ደናግላንና ንጹሐን በማድረግ በጌታ ሠርግ እንዲታደሙ አደረጋቸው”
ስለዚህ የቤተክርስቲን አካል የሆኑና በቅድስና ሕይወት የሚመላለሱ ሁሉ ደናግላን ናቸው፡፡ እንደ ጌታችን ትምሀርትና እንደ ሶርያውያን ቅዱሳን አባቶች አስተምህሮ ድንግልና ማለት ራስን ከኃጢአት መጠበቅ ማለት ነው፡፡ በተለይ ለቅዱስ ኤፍሬም ጌታችንን እንደ ምሳሌ በማድረግ ከኃጢአት ደናግላን ሆነን እንድኖር ያስተምራል፡፡ የእኛም ድንግልና ሊፈርስ የሚችለው በኃጢአት ብቻ ነው፡፡ ይህ መንፈሳዊ ድንግልና ይባላል፡፡
ይቀጥላል……
No comments:
Post a Comment