Friday, December 1, 2017

የትርምት ሕይወት በቅዱስ ኤፍሬም

ቀን 23/03/2010
በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
መቅድም
ቅዱስ ኤፍሬም በጊዜው ገናናና ጥንታዊ በሆነች ንጽቢን 306-373 ዓ.ም ድረስ የኖረ ሲሆን፤ የሕይወት ዘመኑን ሁሉ በትርምት ሕይወት ያሳለፈ በትርምት ሕይወት ላይም ልዩ የሆነ አስተምህሮ ያለው ቅዱስ አባት ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም የትርምት ሕይወት የብሕትና ሕይወትን ለሚመሩ ብቻ የተሰጠ ሕይወት ሳይሆን ማንኛውም ክርስቲያን ሊኖርበት የሚገባ የሕይወት መንገድ ነው፡፡ ስለ ትርምት ሕይወት ሌሎች የሶርያ አባቶች አስተምረዋል የቅዱስ ኤፍሬም ግን ልዩና ጥልቅ ነው፡፡
በትርምት ሕይወት ላይ የሶርያ ቅዱሳን አባቶችን አስተምህሮ ባነበብሁ ሰዓት እጅግ ከመገረም በላይ እኛ ሕይወት እንዲሆንም ተመኘሁ፡፡ ምክንያት የእነርሱ የትርምት ሕይወት አስተምህሮ ከሥጋዊ ድንግልና ላይ ሳይሆን ውስጣዊ ድንግልና ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነበር፡፡ እንደነርሱ አስተምህሮ አንድ ሰው ራሱን ለእግዚአብሔር ፈቃድና ሕግ ካስገዛና አምላኩ ከመሠለ እርሱ  በእርግጥ ድንግል ነው፡፡ የሥጋ ድንግልና ለእነርሱ ከቁምነገር ውስጥ የሚገባ አይደለም በተለይ ለቅዱስ ኤፍሬም፡፡
ይህን ምልከታቸውን በአመክንዮነ መሠረታችንን መጽሐፍ ቅዱስ አድርገን ስንመለከተው ተገቢ እንደሆነም እናረጋግጣለን፡፡ ውስጣዊ ወይም የነፍስ ድንግልናችንን ጠብቀን ከተገኘን የሥጋ ድንግልናችንን መጠበቅ ይቻለናል፡፡ ጌታችንም ስለ ውስጣዊ ወይም የነፍስ ድንግልና ሲያስተምርም “ አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል እኔ ግን እላችኋለሁ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋ አመነዝሮአል፡፡”(ማቴ.5፡27) ብሎ አስተምሮናል፡፡ ስለዚህም አንድ ሰው ውስጣዊ ድንግልናውን ከኃጢአት ከጠበቀ ድንግል ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ሥጋዊ ድንግልናውን ጠብቶ በልቡ ቢያመነዝር ምንም የሥጋ ድንግልና ቢኖረውም ድንግልናውን እንዳጠፋ ይቆጠርበታል፡፡
እንደ ቅዱስ ኤፍሬም አስተምህሮ ደግሞ የትኛውም ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ ክርስቶስን አርዓያው አድርጎ የተመላለሰ እንደሆነ እርሱ ድንግል ነው፡፡
እንደ ቅዱስ ኤፍሬም አስተምሮ የትርምት ሕይወትን መኖር ለአንድ ክርስቲያን የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታው ነው፡፡ ይህ ነው የትርምት ሕይወትን በተመለከተ የቅዱስ ኤፍሬም ልዩ የሆነ አስተምህሮ አለው ለማለት ያስቻለን፡፡
ምዕራፍ አንድ
እጅግ ትሑት፣ እግዚአብሔርን አፍቃሪ እንዲሁም የቅኔ ደራሲና የሥነ መለኮት ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም በሶርያ በሜሶፖቶሚያዊቱ ንጽቢን በ306 ዓ.ም በሶርያ ተወለደ አንዳንድ ጸሐፊያን የቅዱስ ኤፍሬም አባት የጣዖት ካህን ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ጠቅላላ የቅዱስ ኤፍሬምን ሥራዎች ስንመለከት ወይም እርሱ ስለራሱ የተናገረውን ስናስተውል ወላጆቹ እውነተኞች ክርስቲያኖች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡  
በቅዱስ ኤፍሬም ዘመን የሕጻናት ጥምቀት የተለመደ አልነበረም፡፡ ስለዚህም እስኪጠመቅ ድረስ ወላጆቹ ክርስቲያናዊ ሕይወትን የማስተማር ግዴታ ነበረባቸው፡፡
እርሱ ስለልጅነት ሕይወት ሲጽፍ እንዲህ ብሎ ነበር፡-
“እነዚህ ሁለት ጊዜአት የጌታችን ናቸው እነርሱም እኔን በሥጋ ልደት ወደዚህ ዓለም ያመጣበት ጊዜና ይህን ዓለም መተው ባስፈለገኝ ጊዜ በእውነተኛው መንገድ የተወለድሁበት ጊዜ ነው፡፡ ምንም እንኳ የልጅነቴን ሕይወት ባላስተውለውም ባደግኹ ጊዜ ግን ራሴን በጥምቀት ዐውድ ውስጥ አገኘሁት” ይላል፡፡
“የልጅነቴን ሕይወት ባላስተውለውም ባደግኹ ጊዜ ግን ራሴን በጥምቀት ዐውድ ውስጥ አገኘሁት” የሚለው ቃል የሚያመላክተን አድጎ እስኪጠመቅ ድረስ ወላጆቹ በትክክለኛዋ የእውነት ጎዳና እርሱን ሲያሳድጉት እንደነበረ ነው፡፡ እስኪጠመቅ ድረስ በክርስትና አስተምህሮ ውስጥ ስለማለፉ ሌላም መረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡
በመረዳት የተፈጸመ ጥምቀት ሁለቱ ብርሃናት የሚጋጠሙበትና ከብርሃኑ ጅረት የሚፈልቁ የብርሃን ፍንጣቂዎች በአእምሮ ውስጥ ነግሦ የነበረውን ጨለማ የሚያስወግዱ፤ ነፍስ በሕቡዕ ያለውን የክርስቶስን ክብር የምትመለከትበትና በእርሷ ላይ ከወደቀው የክብሩ ብርሃን የተነሣ የምትጨነቅበት ሲሆን ባለመረዳት የተፈጸመ ጥምቀት ግን ባለጠጋ ሆነው ሳለ ባዶ መሆን፣ ባለጠጋ ሆኖ ደሃ መሆን ማለት ነው፡፡ በዚህ የክብሩ ብርሃን ውስጥ ታላቅ የሆነ የእግዚአብሔር ጸጋ አለ፡፡ እርሱን እጅግ ያላወቀውን ታላቅ ጸጋ ባለመረዳት የሚመላለስ ሰው እርሱ በእውነት ምስኪን ሰው ነው፡፡” ይላል፡፡  
ይህም ቃል የሚያስረዳ ቅዱስ ኤፍሬምን ወላጆቹ ክርስትናን ስላስተማሩት ወይም እንዲማር ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ስለላኩት በመረዳት ጥምቀትን መፈጸሙን ነው፡፡ በእርግጥም ገና ታዳጊ ሳለ በንጽቢኑ ጳጳስ በቅዱስ ያዕቆብ ቅዱሳን መጻሕፍትን አጥንቶአል፡፡ የትርምትንም ሕይወት መለማመድ የጀመረው በዚያን ጊዜ ነበር፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን አርዮስን ለማውገዝ በተጠራው ጉባኤ ላይ ለመገኘት ቅዱስ ኤፍሬም ለእርሱ ጸሐፊ ሆኖ አብሮት እንደሄደ ታሪክ ጽፎልን እናገኛለን፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም  በሶርያ ክርስቲያኖች ዘንድ በሚታወቀው “የቃል ኪዳን ልጆች” በሚለው ኅብረት ውስጥ የኖረ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስንና በጊዜው የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍትን በትጋት የሚያነብና ልዩ በሆነ በመንፈሳዊ ተጠምዶ ውስጥ ያለፈ አባት ነው፡፡ ብስለቱንና መንፈሳዊ ተጠምዶውን የተመለከተ የንጽቢኑ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ያዕቆብ ለአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በድንቁና መንጋውን እንዲያስተምር ሾመው፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ ኤፍሬም ራሱን “እረኛው” በማለት ይጠራ ነበር፡፡
የሮም መንግሥት ኃይል እየተዳከመ ሲመጣ ቄሳር ጁሊያን ጦሩን ለመጠበቅ ሲል ከፋርስ ጋር ሰላምን ለማውረድ ንጽቢንን አሳልፎ ሰጠ፡፡ የፋርስ መንግሥትም በንጽቢን ያሉትን ክርስቲያኖች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ አስገደዱአቸው ቅዱስ ኤፍሬምም ከወገኖቹ ጋር ንጽቢንን ለቅቆ ኢዴሳ ወይም ኡር ተሰደደ፡፡ በኢዲሳም ፍጹም በሆነ የትርምት ሕይወት ኖረ፡፡ በዚህም ሳለ ዘፍጥረትና ዘጸአትን ተረጎመ፡፡ በኤዲሳም ባለ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በመምህርነት ያገለግል ነበር፡፡

በዕድሜው ፍጻሜ ዘመን ቅዱስ ኤፍሬም በግብጽ ያሉትን የመነኩሳትን አኗኗር ሊመለከት ሄዶ እንደነበረ ተጽፎልን እናገኛለን፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በመጽሐፈ ኪዳን ላይ ሰፍሮ እንደምናገኘው ወደ ባሲልዮስ ታሪካዊ ጉዞ አድርጎ እንደነበረ ተጽፎልን እናገኛለን፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በኤዲሳ በመኖር ላይ ሳለ በከተማው በተከሰተው ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዱትን ሲረዳ ቆይቶ ሰኔ 9፡373 እንደ ኤ.አ. ዐረፈ፡፡ በኤዲሳ ዐሥር ዓመታት ኖሮአል፡፡ እስከ ዛሬም የሞቱ መታሰቢያ ክብረ በዓል ይከበራል፡፡

No comments:

Post a Comment