Friday, December 1, 2017

የትርምት ሕይወት እንደ ቅዱስ ኤፍሬም አስተምህሮ ካለፈው የቀጠለስለጻፋቸው መጻሕፍት


ቀን23/03/2010
በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ምሁራን ቅዱስ ኤፍሬም የተነሣበት ዘመን ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ በስፋት የበለጸገበት ዘመን ነበር ይላሉ፡፡
በቅዱስ ኤፍሬም ሥነ ጽሑፍ ላይ ተጽዕኖአቸውን ያሳደሩ የሥነ ጽሑፍ ስልቶች እነዚህ ናቸው፡፡  
ሥዕላዊ የአገላለጽ ስልት የሚባለው የጥንት ሶርያውያን ክርስቲያኖች የአጻጻፍ ስልት(Mesopotamian mystery of Symbolism)
የአይሁድ የሥነ ጽሑፍ ስልት
የግሪክ ፍልስፍና  ናቸው፡፡
ስለዚህ አንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምሁር ቅዱስ ኤፍሬምን የሜሶፖቶሚያ፣ የአይሁድ እንዲሁም የግሪክ ሥነ ጽሑፍ መገናኛ ይለዋል፡፡ እነዚህ በአንድነት እንደፈለገ የሚጠቀም ቅዱስ አባት ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ለቅዱስ ኤፍሬም ግን ተችሎት ነበር፡፡
የቅዱስ ኤፍሬም ብዙዎቹ ሥራዎች በመዝሙር መልክ የተዘጋጁ ቅኔአዊ ድርሰቶች ሲሆኑ ይህም የሜሶፖቶሚያው ሥዕላዊ የጽሑፍ ስልትን አብዝቶ እንደሚጠቀም ያሳያል፡፡
የቅዱስ ኤፍሬምን ሥራዎችን ለሦስት ልንከፍላቸው እንችላለን፡
የደረሳቸው መዝሙራት
የጌታችን መዋዕለ ሥጋዌ ላይ ያተኮሩ
ስለጥምቀት ክብረ በዓል የሚያወሱ
ስለዕንቍ ሰባት መዝሙራት(በእምነት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው)
ስብከቶች
ስለ ሥጋዌ
ተግሣጽና ስለንስሐ  
ስለ ኃጢአተኛዋ ሴት
ትርጓሜያት
ዘፍጥረት አንድምታ
ዘጸአት አንድምታ
ወንጌላት አንድምታ(አንድ ወጥ ሆኖ 170 ዓ.ም በታትያን የተዘጋጀ)
አንዳንዶች የሐዋርያት ሥራንና መልእክታትን እንደተረጎመ ይናገራሉ፡፡ ግን ማግኘት አልተቻለም፡፡ አንድ በቅዱስ ኤፍሬም ሥራ ላይ ጥናት ያደረገ ሰባስቲያን ብሮክ የሚባል ጸሐፊ  የቅዱስ ኤፍሬም ሥራዎች የሚላቸው አሉ፡፡ እነርሱም፡-
ወደ ፖብሊየስ የተላከ ደብዳቤ (ስለመጨረሻው ፍርድ)
ስለኒቆሞዲያ ስለመሬት መንቀጥቀጥ የሚያወሳ ጽሑፉ ይገኙበታል፡፡
ግሪክ ኤፍሬም
ግሪክ ኤፍሬም የሚባሉ የኤፍሬም አሻራዎች ያረፉባቸው ግን በሶርያ ሊቃውንት ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ጽሑፎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሥራዎች የቅዱስ ኤፍሬም አይደሉም ወይም የእርሱ አሻራዎች የለባቸውም ማለት ግን እጅግ አስቸገሪ ነው፡፡
እነዚህም፡-
በእንተ ብፁዓን(ሃምሳ አምስት ምዕራፎች አሉት)
የብልጽግና ግምጃ ቤት
ስለ ግብጽ መነኩሳት
ስለ ጦም መዝሙር
በአካለ ሥጋ ስለሌሉ ቅዱሳን አባቶች
ስለ ፍቅር
ማኒን ተቃውሞ የጻፈው ጽሑፍ
መርቂያንን ተቃውሞ የደረሰው ድርሰት ይገኙበታል፡፡
በአጠቃላይ ቅዱስ ኤፍሬም ከዐራት መቶ በላይ መዝሙራትን የደረሰ ሲሆን ጥቂቶቹ ጠፍተዋል፡፡ የቅዱስ ኤፍሬም ሥራዎች ለትርጓሜ እጅግ አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ አስቸጋሪ ያደረጋቸው የጽሑፍ አወቃቀሩ የተወሳሰበ በመሆኑና በቃላት ላይ እጅግ ስለሚራቀቅ እንዲሁም ሥዕላዊ ገለጻዎች ስለሚበዙበት ነው፡፡ ስለዚህም የቅዱስ ኤፍሬምን መልእክት ለመረዳት ጥልቅ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀትና ሕይወቱ እንዲሁም ጥናት ይፈልጋል፡፡
ነገር ግን ጽሐፎቹ ወደ አርመን፣ ቅብጥ(ኮፕት)፣ ግሪክ፣ እንዲሁም ወደ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተመልሶአል፡፡
ምዕራፍ ሁለት
የትርምት ሕይወት
የትርምት ሕይወት (Asceticism) ማለት ራስን ማረቅ መግዛት የሚለማመዱበት ሕይወት ማለት ነው፡፡ የትርምት ሕይወት በክርስቲያናዊ ሕይወታችን አንዱ ክፍል ሲሆን ማንኛውም ክርስቲያን ሊያልፍበት የሚገባ ሕይወት ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያን በሕይወቱ ዘመን ሁሉ እርሱን ሊፈትን የሚተጋ ጠላት አለበትና፡፡ ስለዚህ የዲያብሎስን ውጊያ ድል ለመንሣት አንድ ክርስቲያን የጽድቅን ጡሩር ሊለብስ ወይም የጽድቅን ሕይወት ልማድ ሊያደርግ ግድ ነው፡፡
ለዚህ አብነታችን ራሱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ በዕደ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ቀጥታ መንፈሰ ቅዱስ ወደ ምድረ በዳም ነበር የወሰደው፡፡ በዚያም ዲያብሎስን እንዴት እንዋጋው ዘንድ እንዲገባን አስተማረን፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን የመጽሐፍ ክፍል ሲተረጉም አንድ ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ እንደ አዳም እንደ ኢዮብ በዲያብሎስ ይፈተናል፤ ምክንያቱም ሲጠመቅ የእግዚአብሔር ልጅ ሰለሚሆን ነው፡፡ አዳምን ከገነት እንዳስወጣው እንዲሁ እኛንም በክርስቶስ ካገኘነው የልጅነት ሥልጣን ሊያወጣን ዘወትር ይተጋል ብሎ ያስተምራል፡፡ እውነቱም ይህ ነው፡፡ ለክርስቲያን ከነፍስ የሆነ መታዘዝ እንዲኖረው ሰው በመሆን የሰውን ባሕርይ ያከበረውን የጌታችንን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ ሊያከብር ግድ አለበት፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ቃል በሥጋና በደም በመካፈል የእኛ ዘመድ ሆኖናልና፡፡
ሰው ሁሉ በተጋራው አንድ ተፈጥሮ ምክንያት አንድ ባሕርይ ያለው ስለሆነ ሰው በደልኽ ማለት ራስህን እንደመበደል ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም ሕማሙን ሁላችንም እናውቀዋለን በድርጊት ባንሳተፈው ስሜቱን እንጋራዋለን፡፡ ሲታመም እኛም ያመናል፣ ልቡ ሲሰበር የእኛም ልብ ይሰበራል ሲደሰት ደስ ይለናል ሲያዝን እናዝናለን፡፡ ክብር ለእርሱ ይሁንና እግዚአብሔር ቃል ሰው በመሆኑ ተካፈለን፡፡ ይህንንም ታግሠን የትንሣኤውን ሕይወት ጣዕም እንድንቀምስ እርሱ ወደ በለጠው ክፍ ያደርገናል፡፡   
እንደ ቅዱስ ኤፍሬም አስተምህሮ ደግሞ “ጌታችን ሰው ሲሆን ከውድቀት በፊት አዳም የነበረውን የቀደመውን ባሕርይ ገንዘቡ አድርጎ ነው፡፡ ይህም እኛን ወደ ቀደመው በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ወደተፈጠርንበት ባሕርያችን ሊመልስ ሰው እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ይህ ባሕርያችን በአዳም መታላለፍ ምክንያት ልክ ፍሬ እንዳልተገኘባት በለስ መክኖ ነበር፡፡ ክብር ለእርሱ ይሁንና በጥምቀት በእርሱ ዳግም በመፈጠር እግዚአብሔርን ወደ መምሰል እንድናደግና የመንፈስ ፍሬዎችን እንድናፈራ አበቃን፡፡
አሁን ፍሬ በሚጠበቅብን በወይን እርሻ ውስጥ የተተከልን በለሶች ወይም የእውነተኛው ወይራ ግንድ ቅርንጫፎች ነን፡፡ እናም ጌታችን ፍሬ ይፈልግብን ዘንድ እኛን ይጎበኛል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔር እንደ ተፈጠሩት ለነበሩት ቅርንጫፎች የራራላቸው ካልሆነ ለአንተ ደግሞ አይራራልህምና እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ”(ሮሜ.11፡21-22) ብሎ እንዳስጠነቀቀን ምንም እርሱ ጌታችን እጅግ የሚምርና የሚራራ አምላክ ቢሆንም ከጨከነ ጭቃኔውም እንዲሁ ጽኑ ነውና የእርሱ ቁጣ በእኛ ላይ እንዳይነድ በፍርሃት ሆነን ትእዛዛቱን እንደ ችሎታችን መጠን በመፈጸም በቀረው በቸርነቱ ላይ በመደገፍ ልንመላለሰ ይገባናል፡፡
በምሕረቱ መደገፍ ማለት ከእርሱ ዘንድ ይቅርታን የሚያሰጡንን ተግባራትን ፈጽሞ መገኘት ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት እንደ ችሎታችን እንደ ደረስንበት መረዳት መጠን ራሳችንን ከኃጢአት ለመጠበቅ እንተጋለን ሳናውቅ በስህተት ለፈጸምናቸው በደሎች ደግሞ ከእርሱ ዘንድ ይቅርታን እናገኝ ዘንድ ከተሰወረም ኃጢአት ይጠብቀን ዘንድ በጦም ፣በጸሎት፣ በምጽዋት እንዲሁም ቅዱስ ቁርባንን በመቀበልና እርሱን ደስ የሚያሰኙትን ተግባራት ሁሉ በመፈጸም እንመላለሳለን፡፡
ነገር ግን ይህ የትርምት ሕይወት በጥንት ክርስቲያኖች ይተገበር እንደነበረው ክርስትና በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዘመን በመንግሥት ሕጋዊ ሰውነት ያላት የእምነት ተቋም ከሆነች በኋላ መቀጠል አልቻለም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን የገዛ ፖለቲካዊ አጀንዳው እንደመጠቀሚያ መሣሪያ መጠቀም በመጀመሩ ጳጳሳቱና ካህናቱ የመንግሥትን ፈቃድ በሟሟላት ላይ ስለተጠመዱ በፖለቲካው ዓለም የሚታየው ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም እየተንጸባረቀ በመምጣቱ ምዕመኑ ከሥነ ምግባር በመውጣቱ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሕይወት ያልተመቻቸው ከሕዝቡ ተነጥለው ወይም በማኅበር ሆነው ወይም በግል ይህን ክርስቲያናዊ ሕይወት መምራት ጀመሩ፡፡ ከዚህ ተነሥተው የትርምት ሕይወት የተጀመረው በ4ኛው ክፍለ ዘመን ነው የሚሉ ስለ ትርምት ሕይወት ሲናገሩ “ክርስትና ተስፋፍታ በመንግሥት እውቅና ያላት ተቋም ስትሆን በክርስትና ሕይወት ውስጥ የተፈጠረ አንድ ክፍል ነው” ብለው ትርጉም ሲሰጡት እናገኛለን፡፡ እውነታው ግን ይህ አይደለም፡፡ ይህ ለራስ ጊዜ ሰጥቶ ራስን ወደ ውስጥ የሚመለከቱበት ራስን በቅድስና ሕይወትና መረዳት እለት እለት የሚያድጉበት ሕይወት ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን ይህን ከክርስቶስ የማዳን ሥራ ተካፋይ ለመሆን ይህን ሕይወት ይኖሩ የነበሩ ቅዱሳን እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡(ዕብ.11፡37) ይህ በእምነታቸው እርሱን ደስ ካሰኙት ከሄኖክ ከኖኅ ከአብርሃም ከይስሐቅ የሚጀመር ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ይህ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብ.11 ላይ በሠፊው አትቶት እናገኛለን፡፡

No comments:

Post a Comment