በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ቀን23/03/2010
ከላይ ለማስረዳት እንደተሞከረው የሶርያ ክርስቲያኖች የትርምት ሕይወትን አስመልክቶ የጌታችንን አስተምህሮ መሠረት በማድረግ ሐዋርያት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው አምላካቸውን በጦም በጸሎት ሆነው ሲያመልኩ በነበሩበት ሥርዓት ይመላለሱ ነበር፡፡ በአንዳንድ ምሁራን ዘንድም የእነርሱን የትርምት ሕይወት ከገዳማዊ ሕይወት በፊት የነበረ የምንኩስና ሕይወት ይሉታል፡፡ ነገር ግን እንዲህ እንዳንለው ደናግላን ብቻ ሳይሆኑ ያገቡትም ይህን ሕይወት ገንዘባቸው አድርገው ይመላለሱ ነበር፡፡ እነዚህ የቃል ኪዳን ልጆች የተባሉት ጌታችን “ነገር ግን ልባችሁ ... ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ”(ሉቃ.21፡34) እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ “ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ”(1ቆሮ.7፡29) እንዲል የጌታን ምጽአት አስበው በፍጹም ተመስጦ ለመንፈሳዊው ሕይወት ቅድሚያ በመስጠት በጦም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በትጋእ ሌሊት፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማንበብ ጽሙድ ሆነው በተግባራዊ ሕይወታቸውም ከኃጢአት ተጠብቀው ነፍሳቸውን በጽድቅ ሕይወት አስጨንቀው ይመላለሱ ነበር፡፡ ይህ ሕይወት ግን እያንዳንዱ ክርስቲያን ሊኖረው የሚገባው ሕይወት ቢሆንም በዘመኑም ቢሆን በዚህ ሕይወት የሚኖሩት ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ያለ ምርጫ ያገባውም ያላገባውም የሚኖረው ሕይወት ነበር፡፡
የሶርያውያን ቅዱሳን አባቶች የትርምት ሕይወትን አስመልክቶ ውጫዊ ድንግልናን ሳይሆን ውስጣዊ ድንግልና አጉልተውና አጽንዖት ሰጥተው ያስተምሩ ነበር፡፡ ይህ አስተምህሮ ያለ ምርጫ ያገባውም ያላገባውም ይህን የትርምት ሕይወት እንዲኖር አግዞታል፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ምሳሌ አድርጎ ፡-
“ቅዱስ የሆነ እርሱ በሥጋ ከድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ በመንፈስ ደግሞ በነፍሷ አደረ፡፡ ድንግል እናቱ እርሱን ለመውለድ የወንድ ዘር አላስፈለጋትም፤ ስለዚህ ነፍሳችሁ የጌታ ማደሪያ እንዲሆን በልባችሁ አታመንዝሩ ቅድስት ድንግል ማርያም ይህን ሕይወት መርጣለችና ልቡናዋ ውስጥ የወንድ ፈቃድ አልነበረም፡፡ እርሱ ጌታችንም እርሱን በተረዱት ደናግላን ነፍስ ውስጥ ማደርን ይፈቅዳል” ብሎ ጽፎልን እናገኛለን፡፡ በዚህም አስተምህሮው የነፍስ ድንግልናን ማጉላቱን እናስተውላለን፡፡ ይህም በድንግልና ሕይወት የሚኖሩ ስለነፍሳቸው ንጽሕና አብዝተው እንዲጨነቁና ያለዚህ ነፍሳቸው የክርስቶስ ማደሪያ እንደማትሆን ማስረዳቱን ልብ እንላለን፡፡ በዚህ መሠረት እንደ ቅዱስ ኤፍሬም አስተምህሮ አንድ ሰው ድንግል የሚባለው በሕሊናው ኃጢአትን ከማሰብ ድንግል ሲሆን እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
እንዲሁ ይህ ቅዱስ፡- “ ወዮ የጌታ ሰይፍ በዚህ የጥምቀት ውኃ ውስጥ አለ፣ ይህ ሰይፍ አባትን ከልጅ የሚለይ ሰይፍ ነው፡፡ ሕያው የሆነው ይህ ሰይፍ ሙታንን ከሕያዋን የሚለይ ነው፡፡ በዚህ ውኃ የተጠመቁ ጥሙቃን በግልጽ የእርሱ የጌታ ይሆኑ ዘንድ ደናግላንና ቅዱሳን በመሆን አንዱን የእግዚአብሔር ልጅ ይለብሱታል” ይላል፡፡ በዚህም እያንዳንዱ ክርስቲያን በጥምቀት ለክርስቶስ የታጨ ድንግል እንደሚሆን ያስረዳል፡፡ በዚህ መሠረት ለቅዱስ ኤፍሬም “ድንግል” የሚባለው ቃል ትርጉም በጥምቀት ለአንዱ ለእግዚአብሔር ልጅ የታጨ ክርስቲያን ማለት እንደሆነ ከቃሉ መረዳት ይቻላል፡፡
ከቅዱሰ ኤፍሬም በዘመን የሚቀድመው አፍርሃት(ያዕቆብ ዘንጽቢን የሚሉት አሉ) ደግሞ፡- “ሚስቱን ወደ ራሱ ለመውሰድ ሲል አባቱንና እናቱን የሚተው ሰው ማን ነው? ለዚህ ትርጉሙ እንደሚከተለው ነው፡- ወንድ ልጅ ሚስት እስካላገባ ድረስ እንደ አባቱ እግዚአብሔር አብን እንደ እናቱ መንፈስ ቅዱስን ይወድዳል ከእነርሱ ውጪ ሌላ የሚወደው የለም፡፡ ነገር ግን ሚስትን ወደ ራሱ ሲወስድ አባቱንና እናቱን ይተዋል” ይላል፡፡ እንዲህ ሲል እንደ አባቱ የሆነውን እግዚአብሔር አብን እንደ እናቱ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ይተዋል ሲል ሳይሆን በሥላሴ አርአያ ቤተሰቡን የሚመራ ሙሉ ሰው ይሆናል ማለቱ ነው፡፡ በዚያም ላይ ትዳር ምንም መልካም ቢሆን ካለተጠነቀቁበትና ለተዘክሮተ እግዚአብሔር ጊዜ ካልሰጡበት ከፍቅረ እግዚአብሔር እንደሚያወጣ የሚያሳይም አስተምህሮ ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም፡- ስለ ነፍስ ድንግልና “ ጦምና ድንግልና በራሳቸው ጎጂም ጠቃሚም አይደሉም፡፡ እነዚህን ጠቃሚም ጎጂም የሚያደርጋቸው በሚተገብራቸው ሰው ውስጥ ያለው አመለካከት ነው” ይላል፡፡ በዚህ ትምህርቱ አንድ ሰው በሥጋ ድንግል በመሆኑ እንደማይጸድቅም እንደማይኮነንም ያስረዳል፡፡ እርሱን የሚያስኮንነው በሕሊናው ውስጥ የሚያመላልሰው በጎም ይሁን መጥፎ አሳቡ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የሥጋ ድንግልና አያስፈልግም እያለን ሳይሆን ጌታችን “እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል”(ማቴ.5፡28) ብሎ እንዳስተማረን አስቀድመን ልቡናችንን ከምንዝር ማለትም ከኃጢአት ሁሉ ልንጠብቀው እንዲገባን ሲያሳስበን ነው፡፡ የልብ ንጽሕና ለሥጋ ንጽሕና እንደ አጥር ቅጥር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትም በአንድምታ ወንጌል ይህንን የጌታችንን ትምህርት አርቆ ማጠር ይሉታል፡፡ በልቡና ያሰብነውን ነውና ወደ ተግባር መልሰን የምንፈጽመው፡፡ ምንዝርና የሚለው ቃል ትርጉምም በሕሊና ወይም በሥጋ ከሴት ጋር ማመንዘር ማለት ብቻ ሳይሆን ትርጉሙ ሁሉንም ኃጢአቶች መፈጸም ማለት ነው፡፡
ቅዱስ (ማር) ይስሐቅም ወደ አምላኩ እንዲህ ብሎ ይጸልያል፡-
“በኃጢአት የረከሱ በጥምቀት ያለ አንዳች እድፍ ንጹሐን ደናግላን ሆነው ዳግም ይወለዳሉ፤ አመንዝሮችም ለጌታ ምርጥ ዕቃ ሆነው ዳግም ይሠራሉ፡፡ ጌታዬ ሆይ ተፈጥሮዊውን የሥጋ ድንግልና ሳይሆን ነጻ ፈቃድን በሚጠይቀው በእውነተኛ ሕሊና የሆነን ድንግልና እንድትሰጠኝ እለምንሃለሁ” ብሎ ይጸልያል፡፡ እንዲህ ሲል የሥጋ ድንግልናዬ ፈርሶ በሕሊናዬ ድንግል እንድሆን አድርገኝ ብሎ እየጸለየ እንዳልሆነ ሊረዳ ይገባል፡፡ ምክንያቱም አስቀድመን እንደተጋገርነው የሕሊና ድንግልና ለሥጋ ድንግልና አጥር ቅጥር ነውና፡፡
ይህንን በሚያጠናክር መልኩ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “እኛ መና አለን ይህ መና እስራኤላዊውያን በምድረ በዳ የተመገቡት መና አይደለም፡፡ እኛ መንፈሳዊ መጠጥ አለን ይህ መጠጥ እስራኤላውያን ከአለት ውስጥ ፈለቆ የጠጡት መጠጥ አይደለም፡፡ አሁን እኛ የአንድነትን(ገዳማዊ) አኗኗር እየኖርን ነው፡፡ አሁንም ያለነው በገዳም ውስጥ ነው፡፡ በምድረ በዳ ያለ ቅድስና መኖር ማለት በአካል ከሰው ከመነጠል በቀር ምንም ትርጉም የለውም” ይለናል፡፡ በዚህ ትምህርቱ “አሁን እኛ የአንድነትን አኗኗር እየኖርን ነው፡፡ አሁንም ያለነው በገዳም ውስጥ ነው፡፡” ሲል በዓለም ውስጥ ሆነን ነገር ግን ዓለሙን ሳንመስል ክርስትና በምትጠይቀው ሕይወት ውስጥ ከቅዱስ ሥጋውና ከቅዱስ ደሙ እየተቀበልን ከቃሉ ወተት እየጠጣን የምንኖር ሕይወትን ነው፡፡ ይህ ከዚህ ዓለም ተለይቶ በምድረ በዳ ከመኖር ጋር አንድ ነው እያለን ነው፡፡ ይህንንም ከምንባቡ መልእክት በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
ቅዱስ ይስሐቅ ደግሞ ስለ ነፍስ ድንግልና ሲናገር፡- “ ጋብቻ ድንግልናን የሚያፈርስ አይደለም፡፡ በሕግ የሆነ ተራክቦ ድንግልናን አያፈርስም፡፡ ነገር ግን ከሕግ ውጭ የሆነ ተራክቦ ድንግልናን ያፈርሳል” ይለናል፡፡
በዚህ በቅዱስ ይስሐቅ ቃል ውስጥ ድንግልና እየተባለ የተነገረው የነፍስ ድንግልናን መሆኑን ልብ እንላለን፡፡ ስለ ሥጋ ድንግልና ተናግሮ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ማለት ባልተገባው ነበር፡፡ በዚህም የሶርያ ቅዱሳን አባቶች ለነፍስ ድንግልና ቅድሚያ እንደሚሰጡ መረዳት ይቻላል፡፡
በእርግጥ “የትርምት ሕይወት”(Asceticism) የሚለው የቃል በቃል ትርጉሙ “የድንግልና ሕይወት” ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ለሶርያ ቅዱሳን አባቶች በተለይ ለቅዱስ ኤፍሬም፣ ለቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እና ለማር ይስሐቅ የትርምት ሕይወት ማለት ትርጉሙ ክርስቶስን መምሰል ነው፡፡ ስለዚህ የትርምትን ሕይወት ሊኖር የሚሻ ማንኛውም ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” (1ቆሮ.11፡1) እንዲሁም “በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ፡፡ ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም”(ዕብ.12፡3-4) እንዲል በሁሉ ጌታችንን መድኀኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል ማለት ነው፡፡
በዚህም ክርስቶስን በሁሉ መምሰል ለድናግላን ብቻ የተሰጠ ሕይወት አንዳልሆነ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ኤፍሬም የትርምትን ሕይወትን አስመልክቶ የሚሰጠውን ትምህርት ለደናግላን ብቻ ላገቡትም ይሰጥ ነበር፡፡ እንዲህም እንደሆነ ለደናግላን የሚሰጠውን ስያሜ ሁሉ ላገቡትም ላላገቡትም ሲጠቀምበት እናገኛለን፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደናግላን፣ ትጉኃን፣ መላእክት፣ አዳም፣ የሚሉትን ይገኙበታል፡፡
ወደ ኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስንመጣ ጥንት በሶርያውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ሲተገበር የነበረው የትርምት ሕይወት ሳይሆን ጎልቶ የሚታየው መነሻውን ከግብጽ ያደረገው ገዳማዊ ሕይወት ነው፡፡ ምንም እንኳ ገዳማት ለቤተ ክርስቲያናችን ትላልቅ መንፈሳዊ የትምህርት ማዕከላትና(UNIVERSITIES) ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ ትውፊቶቿን ጠብቃ እንድትቆይ ለቅዱሳን መጻሕፍት ተጠብቀው እንደቆዩ ዓይነተኛ ሚናን የተጫወቱ ቢሆኑም በሕዝብ መካከል ስላልሆኑ ሕዝቡ እነርሱን አርአያ በማድረግ ይመላለስ ዘንድ ሲቸገር እናያለን፡፡ በሶርያ ክርስቲያኖች ይተገበር የነበረው የትርምት ሕይወት ግን በሕዝብ መካከል ስለሆነ ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ እለት እለት የእነርሱን መንፈሳዊ ምንድግና ስለሚመለከት ለሕዝቡ አርአያ የሚሆን ታራሚ አይጠፋም ነበር፡፡ በዚያ ላይ የትርምትን ሕይወት ገንዘባቸው አድርገው የሚመላለሱ ቅዱሳኑ በሕዝቡ መካከል ስላሉ የሕዝቡን ጉድለትና ጥንካሬ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ክፍተቱን ለመሞምላት ይታትሩ ነበር፡፡ እነ አፍርሃት፣ የንጽቢኑ ሊቀ ጳጳሰስ ቅዱስ ያዕቆብ፣ እነ ቅዱስ ኤፍሬም፣ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ እነ ቅዱስ ይስሐቅ፣ እነ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ለዚህ አባባላችን ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን በሕዝቡ መካከል ሆነው የትርምትን ሕይወት ይኖሩ የነበሩ አባቶች ሲሆኑ ከሕዝቡ ጋር በመኖራቸው ምክንያት የሕዝቡን ድክመትና ጥንካሬ ተረድተወ በስብከት፣ በትምህርት፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጻፍ በበጎ ምግባራት አርአያ በመሆን ሕዝበ ክርስቲያኑ ዓለሙን ድል የሚነሳበትን ትጥቅን እለት እለት ያስታጥቁት ነበር፡፡ እነዚህ ቅዱሳን አባቶች ሌሊት ሌሊት በባእታቸው በጸሎት በስግደት ቅዱሳን መጻሕፍትን በማንበብ በመማር በማስተማር ለሕዝበ ክርስቲያኑ የሚያቀበሉት በማዘጋጀት ያድሩና ቀን ሕዝቡን በማስተማር ለሕዝቡ የሚሆኑትን ትምህርታዊ ጽሑፎችን በማድረስ ይደክሙ ነበር፡፡ ዙሪያችንን ተመልክተን ከሆነም ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸው አብዛኛዎቹ የአገለግሎት መጻሕፍት የተደረሱት በሶርያ ቅዱሳን አባቶች ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ከሕዝቡ መካከል ስላሉ ሕዝቡን ስለሚረዱ ነው፡፡
ReplyDeleteAn Thái Sơn với website anthaison.vn chuyên sản phẩm máy đưa võng hay máy đưa võng tự động tốt cho bé là địa chỉ bán máy đưa võng giá rẻ tại TP.HCM và giúp bạn tìm máy đưa võng loại nào tốt hiện nay.