Friday, December 1, 2017

የትርምት ሕይወት በብሉይ ኪዳን(ካለፈው የቀጠለ)

በዲ/ሽመልስ መርጊያ 
23/03/2010
አባታችን አዳም እግዚአብሔር አምላክ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ከተረዳበት ጊዜ አንስቶ ይህም ማለት “እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ተብሎ በአምላክ ከተነገረው ቃል ተነሥቶ “`ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ሰው በመሆን እርሱን እንደሚያድነው ከተረዳባት ጊዜ አንስቶ ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም በመስጠት የክርስቶስን የማዳን ሥራ ተስፋ አድርጎ ይመላለስ ነበር፡፡ የእርሱን ተስፋ ተስፋቸው አድርገውም የተነሡ በምግባራቸው መላእከት የተሰኙ አርእስተ አበውም ነበሩ፡፡ በኖኅ ዘመን የሴት ልጆች ከዚህ ሕይወት የሥጋ ፍትወታቸውን ተከትለው የወጡ ቢሆኑም ኖኅ ግን በዚህ ሕይወት ጸንቶ ተገኝቶ ነበር፡፡
እግዚአብሔርም በመላእክት ሥርዓት ይኖሩ የነበሩ የሴት ልጆች ከመንገዳቸው በመውጣታቸው በውኃ ሙላት አጠፋቸው፡፡ ከኖኅ ይህ ሕይወት ቢቀጥልም መልሶ በመጥፋቱ እግዚአብሔር አብርሃምን አስነሣው ለሙሴም ይህን የመላእክት ሥርዓት የሆነውን ሕግ ሰጠ፡፡ በዚህም ምክንያትም ዲያቆን እስጢፋኖስ አይሁድን ሲወቅስ “በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም” ማለቱን እናስታውሳለን፡፡(የሐዋ.7፡52-53)
ለዚህ ሕይወት እንደ ማሳያ ከሚሆኑን ቅዱሳን መካከል ሴት፣ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ መልከ ጼዴቅ፣ አብርሃም ፣ ሙሴ፣ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ ነቢዩ ኢሳይያስ ሕዝቅኤል ኤርምያስ ዳንኤል ይገኙበታል፡፡ በተለይ በብሉይ ኪዳን ነቢያት በጋራ ሆነው ይኖሩ እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፤ “የነቢያት ጉባኤ” ተብሎም ይጠራ ነበር፡፡(2ነገ.4፡38፤1ሳሙ.19፡20-24)
ከአይሁድ ወገን የሆኑ ኤሴንስ የተባሉ ወገኖች ራሳቸውን በድንግልና ሕይወት በማጽናት በምድረ በዳ ይኖሩ የነበሩ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱና የመጨረሻው ነቢይ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፡፡ በታሪክ አጥኚዎች እነዚህ ወገኖች በአንድነት አምልኮአቸውን ይፈጽሙ እንደነበር የሚያስረዳ በቁምራን በዋሻ ውስጥ የተገኙ መጻሕፍት ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች በቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ፡፡” ተብሎ የተመሰከረላቸው የክርስቶስን ማዳን ተስፋ አድርገው ራሳቸውን ለጽድቅ አስጨክነው የኖሩ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ከቅዱስ ጳውሎስም ቃል እንደምንረዳው እነዚህ ወገኖች ይህን በመሰለ የትርምት ሕይወት የመኖራቸው ምክንያት ዓለም ለእነርሱ ስላልተገባቻቸው ነው፡፡” ዓለም ሲል የሥጋ ፍትወት፣ የኃጢአት ፈቃድ፣ በዚህ ምድር ያለውን አኗኗር ማለቱ ነው፡፡
ስለዚህም ጌታችን “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ፤ ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። ”(ዮሐ.15፡18-19) በማለት በሥጋ ፈቃዳቸው የሚመላለሱ፣ በዚህ ምድር በሚገኘው ተድላና ደስታ ተጽናንተው ሰማያዊውን ተስፋ ከመቀበል የተመለሱትን ወገኖችን ዓለም ብሎ ሲጠራቸው እንመለከታለን፡፡ እርሱ ዓለም ሲል ሰማይና ምድርን ሳይሆን ከላይ እንደተገለጠው ምድራውያን ስለሆኑት መናገሩ ነው፡፡
የጌታ ወንድም ያዕቆብም “አመንዝሮች ሆይ፡- ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል፡፡”(ያዕ.4፡4) ብሎአል፡፡ በዚህ ደግሞ ቅዱስ ያዕቆብ “የሥጋ ፍትወትንና የኃጢአት ፈቃድን” ዓለም ማለቱን እናስተውላለን፡፡  
በእርግጥም ይህች ዓለም መንፈሳውያንን አትፈልግም፤ ለእነርሱ ቦታ የላትም፡፡ እርሷን ስንመስላት ግን ታቀርበናለች፤ ካልመሰልናት ግን ትጠላናለች፤ በእርሷ ዘንድ ምንም ቦታ አይኖረንም፡፡ ቢሆንም ግን እኛን ለማሰናከልና በድክመታችን ልታጠቃን ዘወትር ዝግጁ ናት፡፡ ስለዚህ ይህቺ ዓለም ምስጋና ስትቸረን አቦ አቦ ስትለን ቆም ብለን ልናስብ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ወይ በእኛ እየተጠቀመችብን ነው ወይም እኛ እርሷን መስለን ተገኝተናል፡፡ እርሷን ከመሰልን የእግዚአብሔር ጠላቶች እየሆንን እንደሆነ ልብ እንበል፡፡
ቢሆንም ግን ለዚህች ዓለም ብርሃን ሆነን ልንመላለስ እንጂ ከዚህች ዓለም እንድንለይ አልታዘዝንም “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም” ብሎ ጌታችን እንደተናገረው፡፡(ዮሐ.17፡15) ይህ ማለት ገዳማዊ ሕይወትን መቃወሙ አይደለም፡፡ ቢሆን ኖሮ ግን አስቀድሞ ሊቃወመው የሚገባው ዮሐንስ መጥምቅ ነበረ፡፡ ይህ የተነገረው ለዓለሙ ብርሃን ሆነን መኖር ለሚገባን ለእኛ ነው፡፡
የትርምት ሕይወት በአዲስ ኪደን
ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ የትርምት ሕይወት ጀማሪው እርሱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ ለሕዝቡ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” ብሎ ለትምህርት ከመውጣቱ በፊት በእደ ዮሐንስ ተጠምቆ ወዲያውኑ ወደ ምድረ በዳ ሄዶአል፡፡ በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጦሞአል፡፡ በዚያም በሰይጣን ተፈትኖአል፡፡ ይህም ለእርሱ ተገብቶት ሳይሆን ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ ነው፡፡ አንድ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ አድሮበት የእግዚአብሔር ልጅነትን ስልጣን ካገኘበት ጊዜ አንስቶ ዘወትር መንፈሳዊ ትጥቅን ታጥቆ የቃሉን ጥሩር ለብሶ የእምነትን ቆብ ደፍቶ ሁል ጊዜም ቢሆን በሰይጣን ለሚመጣበት ጦርነት ዝግጁ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በዚህ ጦርነት ተሸናፊ ከሆነ ከመንግሥት ሰማያት ውጪ ይሆናል ነገር ግን በነገር ሁሉ ክርስቶስን ከመሰለው ለዓለም እንደብርሃን ሆኖ ብዙዎችን ወደ መንግሥቱ የሚያቀርብ ሠላሳም ስሳም መቶም ፍሬ እንሚያፈራ የእግዚአብሔር ታማኝ ባሪያ ይሆናል፡፡
ነገር ግን ይህ ሕይወትን ለገዳማውያን ብቻ መስጠት እጅግ ስህተትና አላዋቂነት ነው፡፡ ክርስቲያን በዚህ ምድር ሳላ ክፉ ባላጋራ እንዳለበት አንድ ቀንም በሞት ወደ አምላኩ እንደሚቀርብ በአምላኩም ፊት ለፍርድ እንደሚቆም አስቦ ሊመላለስ ይገባዋል፡፡ ይህም የትርምት ሕይወት ነው፡፡ ራስን አርሞና አርቆ በጥንቃቄ መጓዝ ማለት የትርምት ሕይወት ማለት ነውና፡፡ ጌታችን ይህን ሕይወት አንድ ጊዜ ብቻ የፈጸመው ሳይሆን የእለት ተእለት ተግባሩ ነበር፡፡ የጌታችን ሕይወት የትርምት ሕይወትን ለምንኖር ለሚሹ በዓለሙ ላለነው ብርሃን ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ይህን የትርምት ሕይወት በመኖሩ ምክንያት ያገኛቸውን ተሞክሮዎች እንደ ጌታው በቃል ወይም በጽሑፍ የዚህ ሕይወት ፍና ለሚከተሉ ሊያቆይላቸው ይገባል፡፡
በአዲስ ኪዳን ራስን በድንግልና ማኖር ራስን ለእግዚአብሔር መንግሥት ጃንደረባ ከማድረግ ጋር አንድ ነው፡፡ ጌታችን ሐዋርያትን ለመምህርነት ሲያዘጋጃቸው ሁል ጊዜም ቢሆን ከማኅበረሰቡ ለይቶ ብቻቸውን የትርምት ሕይወትን እንዲለማመዱ በማድረግም ጭምር ነበር፡፡(ሉቃ.22፡39) በዚህም ጌታችን ለሐዋርያቱ የትርምት ሕይወትን አንዱ የሕይወታቸው አካል አድርገው እንዲይዙት መሻቱን እናስተውለለን፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም ክርስቶስን አብነት አድርጎ የሚኖረውን ሕይወት እኛም እንኖረው ዘንድ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ”(1ቆሮ.11፡1) ብሎ አስተምሮናል፡፡ እንዲሁ ሁሉም ሐዋርያት ጌታችንን መስለው የትርምትን ሕይወት ኖረዋል፡፡(ማቴ.10፡27) ስለዚህ ሐዋርያት  ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ “አቤቱ፥ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት፥ በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው። በልቅሶ ሸለቆ ውስጥ በወሰነው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና።(መዝ.83፡5-7) እንዲል እነርሱም በባሕታቸው(ማለትም ብቻቸውን በጸሎት በሚተጉበት ጊዜ) መዝሙረኛው “በለቅሶ ሸለቆ ውስጥ” ባለው ሥፍራ ከመንፈስ ቅዱስ በጨለማ(በሕቡዕ) የሰሙትን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮ የሰሙትን በሰገነት ላይ ሰበኩልን፡፡ ጌታችንም በተግባር ጸሎትን እንዴት መጸለይ እንዳለበት ካስተማራቸው በኋላ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው”(ማቴ.26፡41) ብሎ እንዳስተማረን ለጦም ለስግደት ለጸሎት ለምንባብ እንዲሁም ለጽሙና ሕይወት ከተጋን መንፈስ ቅዱስ መምህር ሆኖ እኛን ይመራናል፡፡ ያስተምረናልም፡፡
ለሰው ሁለት ሕይወት ተፈቅዶለታል አንዱ በሕግ አንዱ ያለ ሕግ ነው፡፡ በሕግ ጋብቻ ነው፡፡ ያለ ሕግ ግን በፈቃድ ላይ በራስ ምርጫና ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የድንግልና ሕይወት ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን ለማገልገል በድንግልና ጸንቶ መኖር ተመራጭ ነው፡፡ ጌታችንም ይህ የድንግልና ሕይወት ምርጫ ስለሆነ “ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው” ብሎአል፡፡ (ማቴ.19፡12)
አንዳንድ ሰዎች “ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም”(ሉቃ.14፡26) የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በድንግልና ሕይወት ለሚኖሩ ብቻ ሰጥተው ሲያሰተምሩ ይስተወላሉ፡፡ ይህ ግን ክርስቲያን ነኝ ለሚል ሁሉ የተሰጠ መመሪያ ሲሆን እግዚአብሔርን መውደድ እስከ የት ድረስ ደርሰን ገንዘባችን ማድረግ እንዳለብን የሚያሳስብ ኃይለ ቃል ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን “ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል”(ማቴ.10፡39) በማለት ለሁሉ እንደሚናገር ተጽፎልናል፡፡
አንድ ሰው በሥላሴ ስምና ሥልጣን ባለው ካህን ሲጠመቅ ለዚህ ዓለም ሞቶ በክርስቶስ ግን ሕያው ይሆናል፡፡ ስለዚህ ወደፊት ለራሱ ሳይሆን ለተፈጠረበት ለበጎ ሥራ ሊኖር ግዴታ አለበት፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስ እርሱን በሞቱ በአዲስ ተፈጥሮ ወልዶታልና ወደፊት የራሱ አይደለምና፡፡ ስለዚህ ለዚህ ለትንሣኤ ሕይወት መኖር ካለበት እንግዲያውስ የትርምት ሕይወት ለአንድ ክርስቲያን ግዴታው እንጂ በውዴታው የሚኖረው ሕይወት አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሕይወት ለደናግላን ብቻ የተሰጠ ሕይወት ነው ብሎ ማንም አያስብ፡፡ ምክንያቱም የትኛውም ክርስቲያን ለእርሱ ለሞተለት ጌታ ይኖር ዘንድ ክርስቲያን ሆኖአልና፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና። ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።”(ገላ.2፡19-20) ብሎ አስተምሮአል፡፡

ስለዚህ ለዓለም ፈቃድ መሞት ለደናግላን ብቻ የተሰጠ ሕይወት ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር በጥምቀት ለተሰቀለ ክርስቲያን ሁሉ የሚሆን ነው፡፡ ይህ ሰው ወደፊት የሥጋን ሥራ ይሠራ ዘንድ በክርስቶስ ዳግም አልተወለደም፡፡ ስለሆነም ይህን የትርምት ሕይወት ለደናግላን ወይም ለገዳማውያን ለይቶ መስጠት የሚገባ አይደለም፡፡ ክርስቲያን ነኝ ለሚል ሁሉ ግዴታው ነው፡፡ በእርግጥ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በድንግልና ሕይወት መኖር ተመራጭ ነው፡፡ እንዲህ ማለት ግን ይህ ለደናግላን ብቻ የተፈቀደ ሕይወት ነው ብሎ መወሰነ ተገቢ አይደለም፡፡ 

No comments:

Post a Comment