በዲ/ ሽመልስ መርጊያ
21/02/2010
የሁሉ ፈጣሪ የሆነው የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ይህ ነው፡- በእውነት መዳንን ለሚሻ ወገን እንደ ኦሪቱ ጥላውን ሳይሆን ወይም አይሁድ በስደት ሳሉ በሙክራባቸው እንደሚፈጽሙት ዓይነት አምልኮ ሳይሆን በእውነት በእርሱ በክርስቶስ በጎውን ለማድረግ ተፈጥሮ፣ በእርሱ እረኝነት ሥር ሆኖ፣ ግልገል ጠቦት በግ ተሰኝቶ፣ ሰማያዊ ሥፍራ በተባለችው መንግሥቱ ውስጥ በእርሱ መለኮታዊ ብርሃን የቀን ልጅ ተብሎ ከጸጋው እየተመገበ እንዲኖር ነው ፈቃዱ፡፡
ይህች ዓለም ደግሞ ኢአማኒያን ዓሣትን ማጥመጃ ባሕር፤ ሰማያዊ ንግድን ነግደው የሚያተርፉባት ገበያ፣ በእግዚአብሔር እርሻ ውስጥ ንጹሕ ዘርን ዘርተው ሰላሣ ስልሳ መቶ ፍሬ የሚያፈሩባት ምድር ናት፡፡ ሁላችንም ኅብረታችን ከአንዱ እግዚአብሔር ጋር ነው ፍላጎታችንና መፈለጋችን ፈቃዳችንም እርሱ ነው፡፡ እምነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው ጉድፍ ጋር ኅብረት የለውም፡፡
ነገር ግን የገነትን ጣዕም ያስረሱንን አዳምንና ሔዋንን ያሳተ ሰይጣን ከዚህች ረቂቅና ሰማያዊ ሥፍራ እኛን ለማስወጣን ይደክማል፡፡ ይህ የሚጠበቅ ነውና ጌታችን እኛን በሁሉ መስሎ ዲያብሎስን ድል በመንሣት ድል መንሣትን ለእኛ ሰጠን፡፡ የሚያሳዝነው ግን በምድር ያሉ ሁሉ የእርሱ ሲሆኑ እርሱ ቸሩ ፈጣሪ ለሰዎች ሲሰጣቸው ሰዎች ደግሞ የሰጣቸውን መልሰው ለዲያብሎስ በመስጠት ምንም ሳይኖረው ዲያብሎስን የዚህ ዓለም ገዢ ማድረጋቸው ነው፡፡ እርሱ ረቀቅ መንፈስ ነው፡፡ ምድር ደግሞ በዋነኝነት ለሰዎች የተሰጠች ናት፡፡ ምድር ለእኛና ለምድር ፍጥረታት የሚስማማ ተፈጥሮ እንጂ ለዲያብሎስ የሚስማማ ተፈጥሮ የላትም፡፡ ከምድር ፍሬ ዲያብሎስ ለመኖር ሲል አይበላም አይጠጣም አየሩም አያስፈልገውም፡፡ ድካምም የለበትም ዕረፍትም አያሰፈልገውም፡፡ ታዲያ ምን እንዲሆነው ነው የምድርን ገዢነት ለእርሱ የሰጡት?
ይበልጡኑ ግን ሰዎች በስሜ ይመጣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ እንዲል ጻድቃን መስለው የዲያብሎስ ባሪያዎች መሆናቸው ነው የሚያሳዝነው፡፡ ጌታ ብለው የሚሰብኩን ፍጡር ስለሆነው ወደ ፊት ስለሚመጣው እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስለሚለው ነው፡፡ ይህን ከፍሬአቸው ታውቃላችሁ፡፡ በዚህ ዘመን ለሃሳዊው መሲህ ነቢያትና መንገድ ጠራጊዎች የሆኑ ምድሪቱን ሞልተዋታል፡፡ ሁሉም ጌታ ኢየሱስ ስላለ እውነተኛውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እየጠራ በእርሱም ስም እየባረከ አይደለም፡፡ ሰይጣንም እንዲሁ ያደርጋል የእርሱ ብራኬ ታዲያ ምን ያደርግልናል? በዚህ በምናባቸው በተፈጠረው ኢየሱስ ስም ወይም በሃሳዊው መሲህ ስም ቢባርኩንም ቢረግሙንም ያው አንድ ነው፡፡ ሁለቱም ለእኛ የማይጠቅምም የማይጎዳም ነው፡፡ በእኛ ላይ አንዳች ስልጣን የለውምና፡፡ ይልቁኑ እኛ በእርሱ ላይ ስልጣን አለን፡፡
የድንግል ልጅ ባልሆነው ኢየሱስ ስም መባረክ ማለት በእርግጥ እርግማን ነው፡፡ ርግማኑ ግን በራሳቸው ላይ እንጂ በእኛ ላይ አይደለም በጣዖት ስም እየባረኩና እየረገሙ ናቸውና፡፡ ለምን ብትሉኝ አንደኛ የጌታችንን ስም ለፍጡር ያውም ለእርሱ ተቃዋሚ በመስጠታቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ለዚህ ሃሳዊ መሲህ ልባቸውም አንደበታቸውም መገለገያ መሣሪያ ማድጋቸው ነው፡፡ በሦስተኛነት ደግሞ ጻደቅ መስለው ሌሎችን በመሸንገላቸውና ወደ ጥፋት በመጣላቸው ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ደግሞ የድንግል ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ከመልበስ፣ ከመመገብ፣ ከመጠጣት፣ በእርሱ ውስጥ ከመኖር በላይ ምን የተሻለ መባረክ አለና ነው ጌታ ይባርክህ የሚሉን? ነገር ግን በድንግል ማርያም ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ብትባርኩን እሰማችሁ ይሆናል፡፡ እንዲያም ቢሆን ግን በበልዓም ሥፍራ ሆናችሁ ስለሆነ ለእናንተ በእጅጉ አዝናለሁ፡፡
በኋለኞቹ ዘመናት በስሜ ይመጣሉ የተባሉ እነዚያ ሃሳውያን የሰይጣን ሎሌዎች ለሰው ልጆችም ሆነ ለራሳቸው እንደ አባታቸው ዲያብሎስ ጭላጭ ፍቅር የላቸውም፡፡ ግን እኛ እነርሱ ለዲያብሎስ መሳሪያ በመሆናቸው ብናዝንም እንድንጠላቸው አልታዘዝንም፤ ጠላትህን ውደድ ማለት እንዲህ ነውና፡፡ እነርሱ በዲያብሎስ ታውረው ይጠሉናል እኛ ግን እንዲሁ እንወዳቸው ዘንድ ታዘናል፡፡ ሰይጣንንም ቢሆን በእግዚአብሔር ፍጥረትነቱ አንጠላውም፡፡ ነገር ግን ተግባሩን እንጠላለን፡፡
እርሱ የፍቅር ጠላት ነውና ፍቅር የቀዘቀዘው እርሱ የጥል አባት ስለሆነ መለያየትን በሰዎች ላይ በመዝራቱ ነው፡፡ ጌታችንም “አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር ስምህ ይቀደስ መንግሥት ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን የእለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ በደላችንን ይቅር በለን እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል” እያልን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ እንድንጸልይ አዞናል፡፡ ይህ ጸሎት ልመናም ምልጃም ነው፡፡ ጸሎቱ፣ ምልጃውና ልመናው በምድር ላሉ ሁሉ ነው፡፡ “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን” እንዲል፡፡
“የሚጠሉዋችሁን ብትጠሉ አሕዛብም ይኸንኑ ያደርጋሉና ምን ዋጋ አላችሁ?” እንዳለ ጌታችን መንግሥቱም በፍቅር የምትገለጥ ናት፡፡ እርስ በእርሳችሁ ብትዋደዱ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደሆናችሁ ሰው ሁሉ ያውቃል ይለናል፡፡ ግን እርስ በእርስ ብትነካከሱ የክርስቶስ አይደላችሁም፡፡ የክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ፍቅር አለ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ “አንድ እግዚአብሔር፣ አንድ ጌታ ፣አንዲት ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ብሎ በአንድ አካል ያሉ እርስ በእርስ ፍጹም እንዲዋሐዱ ማድረጉ ስለምን ይመስላችኋል? እንዲህ አድርጎ ጌታችን እኛን በአዲስ ተፈጥሮ መፍጠሩ አምላክ መለያየትን በሚዘሩና ፍቅርን በሚያጠፉ ወገኖች ደስ እንደማይሰኝ ያሳየናል፡፡ በመስቀሉ አንድ ሊያደርገን ስለእኛ በመስቀል ላይ ዋለ፡፡ በስቅለቱም እኛን ወደ ላይ ወደ ሰማይ ሳበን ከቅዱሳን መላእክትና ከቅዱሳን ነፍሳት ጉባኤ ደመረን፡፡ ምድር ሰማይ ሆነች ሰማያውያንም በምድር በክርስቶስ ካሉ ጋር ኅብረትን ፈጠሩ፡፡ ይህ የሆነው ስለ ፍቅር ነው፡፡ እናም ዘመዴ ጌታ ያደረግኸውን ሳታውቅና ሳትለይ ጌታ ይባርክህ አትበለን፡፡ እኛ በእርሱ ያጣነው የጎለብን አንዳች ነገር የለምና፡፡
No comments:
Post a Comment