Saturday, March 3, 2012

ሴቶች ሊያውቁዋት የምትገባ እውነት!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
24/06/2004
ዛሬ ባነሣሁት ጭብጥ ላይ:- ደግሞ ምን አመጣህ? ትሉኝ ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ ፍጥጥ ያለ እውነትና እውቀት ነው፡፡ ይህቺ እውነት እናቶቻችን፡- "ድሮ አግኝተናት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ይህች ዓለም የአውሬዎች መፈንጫ ባልሆነች ነበር" ብለው የሚቆጩባት እውነት ናት፡፡ ይህቺ እውቀትና እውነት ፡-  ዓለምን ሴቶች ይገዙአትና ይመሩዋት ዘንድ ተፈጠረች የምትል ናት፡፡ መቼም ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ብላችሁ በመገረም ትጠይቁኝ ይሆናል፡፡ እውነቱና ሐቁ ግን ይህ ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሴት ልጅ ገነትን እንደራሱዋ ሃሳብና ጥቅም ትመራትና ትጠቀምባት ዘንድ በዚህም እርፍ ብላ ትኖርባት ዘንድ አዳምን ጨምሮ ሁሉን አደላድሎ ከፈጠረ በኋላ የፍጥረት ሁሉ ዘውድ አድርጎ ከአዳም አስገኛት፡፡ አዳም አስቀድሞ በሥጋ መገለጡ ለእርሱዋ በእግዚአብሔር ፈንታ ሆኖ ገነትን እንዴት መምራትና ማስተዳደር እንደምትችል ያስተምራት ዘንድ ነበር፡፡ በእርግጥም አዳም ይህን ፈጽሞላታል፡፡ ስለዚህም ነው ሰይጣን እርሱዋን በተንኮል “በእውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? ብሎ በጠየቃት ጊዜ “በገነት ካለው ዛፍ ፍሬ እንበላለን ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ እግዚአብሔር አለ፡-እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም”ብላ መመለሱዋ፡፡(ዘፍ.3፡2-3)

ይህ ትእዛዝ ለአዳም እርሷ ሳትገለጥ በፊት ተሰጠው እንጂ ለእርሱዋ እግዚአብሔር አልነገራትም፡፡(ዘፍ.2፡16-17) በዚህም ከእርሱ ያገኘችውን እውቀት ከእግዚአብሔር እንዳገኘችው ቆጥራ ለሰይጣን መልስ መስጠቱዋን ማስተዋል እንችላለን፡፡ ስለዚህ አዳም የራሱን ሓላፊነት በአግባቡ ተወጥቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ከእርሱም ተገቢውን እውቀት ካገኘች በኋላ ሰዎች እርሱዋን መልሰው እንዳይበድሉዋት ተጠንቅቃ ለባሕርይዋ እንዲስማማ አድርጋ ትመራቸውና ቀርጻ ታሳድጋቸው ዘንድ ሓላፊነቱ ለእርሱዋ ተሰጣት፡፡
የሴት ልጅ መሪነት ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ይህ አገዛዙዋ ግን በአዳምና በእርሱዋ ክፉ ምርጫ ምክንያት በገነት ልትተገብረው አልቻለችም፡፡ በእነርሱ ክፉ ምርጫ ምክንያት እኛንም ይዘውን ወደ እዚህች ምድር መጡ፡፡ ቢሆንም የገዢነት ሥልጣኑዋ ተፈጥሮአዊ ነውና ከእርሱዋ አልተነጠቀም ነበር፡፡ አገዛዟ ግን በኃይል ወይም በጉልበት የሚፈጸም ሳይሆን በጥበብና በማስተዋል ነው፡፡ ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለ የአገዛዝ ጥበብ ነው፡፡ “እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና”ይላልና፡፡(ምሳ.3፡19) ነገር ግን እግዚአብሔር ፍጥረትን በጥበብና በማስተዋል መፍጠሩ እርሱን መልሰው እንዳያጠፉት አስቦና ተጨንቆ አይደልም እንደው ጥበብን ስለሚወዳት እንጂ፡፡ ነገር ግን ሴቶች ልጆቻቸውን በጥበብና በማስተዋል ሆነው ባይመሩዋቸው መልሰው እነርሱን ያዋርዱዋቸዋልና፣ ይበድሉዋቸዋልና፣ ያሳዝኑዋቸዋልና ከዚያም ሲያልፍ ያጠፏቸዋልና ጥበብ አስፈለገቻቸው፡፡ ስለዚህም ለሴት ልጅ አገዛዙዋን በጥበብ ማድረጉዋ ውዴታዋም ብቻ ሳይሆን ግዴታዋም ነው፡፡ እንደውም ሴት ልጅ ከጥበብ ስትወጣ ልክ እሪያን እንድትመስል ጠቢቡ ሰሎሞን “የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደሆነ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ(ለማግባት የደረሰች ልጃገረድ ማለቱ ነው) እንዲሁ ናት”ይለናል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? በግብራቸው እንደ እርያ ለሆኑት ማጌጫ ትሆናለች ማለቱ አይደለምን? ስለዚህም ሴት ልጅ ስለራሱዋ ክብር ስትልም ጭምር ጥበብን ገንዘቡዋ ማድረግ ይኖርባታል ማለት ነው፡፡
ይህን ባወቅ እግዚአብሔር አምላክ ልጆቹዋ መልሰው እርሱዋን እንዳያስጨንቁዋት ሲል እንደርሱዋ ፈቃድና ምርጫ ትመራቸውና ቀርጻ ታሳድጋቸው ዘንድ ሰፊውን ሓላፊነት ለእርሱዋ ሰጣት፡፡ እግዚአብሔር እርሱዋን ወንዶችና ሴቶች ልጆቹዋን ከፅንሰት እስከ ክፉና ደጉን እስከሚለዩበት እድሜአቸው ድርስ በብቸኝነት ከዚያም በኋላ ከባሏ ጋር በመተባበር እንድትመራቸው አደረጋት፡፡
የሴት ልጅ ተፈጥሮ የእግዚአብሔር ፈቃድ በእጅጉ ይስማማዋል፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ፍቅር የሚገዛው፣ የዋህና ፣ትሑት፣ የሆነው ሰው እናቱንና እኅቱን የሚወድ ለሴት ልጅ ክብር ያለው፣ በእነርሱ ላይ ጾታዊ ጥቃት ከማድረስ የሚጠበቅ፣ በእነርሱ ላይ መሠልጠንን የማይወድ  ሰው ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ለሴት ልጅ ተፈጥሮ በእጅጉ የሚስማማ ነው፡፡ እንዲህ አድርጎ ቀርጾ የማውጣት ሰፊውን ሓላፊነት የተቀበሉት ሴቶች ናቸው፡፡ እንዲህ አድርገው ትውልዱን ቀርጸው ያሳድጉ ከሆነ ዓለም ጤናማና ለእነርሱ የምትመች እንዲሁም የምትገዛላቸው ትሆናለች፡፡
ነገር ግን ይህን ሴቶች እናቶቻችንና እኅቶቻችን አልተረዱትም ፡፡ እነርሱ ይህን ሓላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ምክንያት የገዢነት ሥልጣናቸውን ለወንዶች አሳልፈው ሰጡ፡፡ ዓለም ወንዶች የሠለጠኑባት፣ ሴቶች ልጆች እንደ ሸቀጥ የሚቆጠሩባት፤ ጾታዊ ጥቃት የሚፈጸምባቸው፣ እንደ ባሪያ የሚገዙባት፣ ጦም ላለማድር ሲሉ አካላቸውን ሽጠው ተዋርደውና ተገፍተው የሚኖሩባት ሆነች፡፡
እግዚአብሔርን እናውቃለን የሚሉት አይሁድ እንኳ በሴቶች ላይ እንዲህ ዓይነት ግፍን ከመፈጸም አልተመለሱም፡፡ ለዚህ እንደማስረጃ የጠቢቡ ሰሎሞንን ቃል ማንሣት ይቻላል፡፡ ተመልከቱ እርሱ “ትልቅ ሥራን ሠራሁ ቤቶችንም አደረግሁ..” ካለ በኃላ “…. ብርንና ወርቅን የከበረውንም የነገሥታትና የአውራጆችን መዝገብ ሰበሰብሁ አዝማሪዎችንንና … የሰው ልጆንም ተድላ እጅግ የበዙ ሴቶችን አከማቸሁ”አለ፡፡(መክ.4፡1-9) እስቲ ተመልከቱ በእነርሱ ዘንድ እንኳ ሴት ልጅ ለወንድ ተድላ እንደተፈጠረች ተደርጎ ይታሰብ እንደነበረ ኃይለ ቃሉ ይነግረናል፡፡ ይህ እስከ ክርስቶስ ልደት ድረስ በሕዝብም በአሕዛብም ዘንድ ሴቶች ሰው መሆናቸው ተዘንግቶ እንደ ማህመዳዊያኑ እንደ እርሻ ተቆጥረው ይኖሩ ነበር፡፡
ይህ ግን ተገቢና ጤናማ ስላልሆነ ዓለምን የመምራት ሓላፊነትን ለሴት ልጅ መልሶ ሊሰጣት እግዚአብሔር ቃል ከወንድ ዘር ያይደለ ከሴት ብቻ ተወለደ፡፡ እርሱም እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሴቶች እንዴት አድርገው ዓለምን መምራትና ማስተዳደር እንደሚችሉ መምህር አድርጎ ሰጣቸው፡፡ እርሱዋም ልጁዋን ኢየሱስ ክርስቶስን በጥበብና በሞገስ በሰውም በእግዚአብሔር ፊት አሳደገችው፡፡ ይህ ግን ለእርሱ የሚነገር ሆኖ ሳይሆን እርሱዋ ለሴቶች ሁሉ አብነት እንደሆነች ለማሳየት ነው፡፡እንዲሁም ሴቶች የመምራት ሓላፊነት እንደተሰጣቸው ሁል ጊዜም ልብ እንዲሉ በሴት አምሳል ቤተ ክርስቲያንን መሠረታት፡፡
እናቶች ወንዶች ልጆቻቸውን ክርስቶስን መስለው እንዲያድጉ ቢቀርጹአቸው፤ ሴቶች ልጆቻቸውን ደግሞ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መስለው እንዲያድጉ ቢያደርጉዋቸው፤ ይህች ዓለም ለሴቶች የማትስማማ የአራዊቶች መመሸጊያ አትሆንም፡፡ የእነርሱም  አገዛዝ ፍጹም ይሆንላቸዋል፡፡ ይህን ባያደርጉ ግን በብሉይ ይፈጸምባቸው የነበረው በደል ተመልሶ ይመጣባቸዋል፡፡
 አሁንም እንኳ ከብሉይ ኪዳን በባሰ መልኩ ሴቶች እናቶቻችንና እኅቶቻችን እግዚአብሔርን በማያውቁ ክርስቶስን መስለው ባላደጉ ወንዶች እየተበደሉ እንደሸቀጥም ገላቸው እየተነገደበት ይገኛል፡፡ ይህ የሚያሳየን ሴቶች አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ የተሰጣቸውን የመሪነት እድል ለወንዶች አሳልፈው መስጠታቸውን ነው፡፡
ይህን ደግሞ በዓይናችን እያየነው ያለ እውነታ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ቀጣዩ ትውልድ ሴቶችን የማያስጨንቅ ትውልድ አድርጎ የመቅረጽ ቁልፉ ያለው በሴቶች እጅ ነው፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔር እነርሱን ብቁዋን ለማድረግ ሲል ሴት ልጅ ሰፊ ጊዜዋን በቤቱዋ እንድታሳልፍ ሥርዐትን መሥራቱ፡፡ እንዲህ ማድረጉም የንባብና የጸሎት ጊዜ እንዲኖራት በማሰብ ነው፡፡ ሴት ልጅ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላኩዋ ልጆቹዋን በአግባቡ የምትመራበትን መንፈስ ከተቀበለች ከተፈጥሮዋ ጋር በሚስማማ የእግዚአብሔር ፈቃድ ልጆቹዋን መምራትና ማስተዳደር ይቻላታል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ የሴት ልጅ ሰቆቃ አከተመ ማለት ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በልጁዋ በወዳጁዋ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳረፈች እንዲሁ እርሱዋም ዓለምም በልጁዋ ያርፋሉ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ይህን ማስተዋል ለሁላችን ያድለን ለዘለዓለሙ አሜን!!!   

1 comment:

  1. bewnu wedmachin tsegawn yabzalh endante aynetu memher le Ethiopian hageri yabzalat.

    ReplyDelete